ልክ የዛሬ 20 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ድግሪ በፋርማሲ ተመርቋል።
ተመስገን መምህሩ በሞያው ፋርማሲስት ነው። ዛሬ ላይ ህዝብና ሀገርን በማገልገል ላይም ይገኛል።
የዛሬው ቀን ለተመራቂው ተመስገን ልዩ ናት። በዛሬው ዕለት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ህግ 3 ነጥብ 97 እና በሎጅስቲክ እና በአቅርቦት አስተዳደር 3 ነጥብ 6 ውጤት በማስመዝገብ በሁለት ማስተርስ ድግሪ ተመርቋል።
ሁለቱንም የማስተርስ ድግሪውን በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ በመጀመር በተመሳሳይ ቀን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ያጠናቀቀው ተመስገን፤ በሁለቱም ትምህርቶች የጥናት እና ምርምር ውጤቱን እጅግ በጣም ጥሩ በማስመዝገብ ነው የተመረቀው።
ሁለቱንም ጥናቶች በሀገራቱ በመድሃኒት ምርትና አቅርቦት ላይ በማተኮር ያከናወነ ሲሆን፤ ተመራቂው ተመስገን ቤተሰብ እና የሙሉ ቀን ስራ ቢኖረውም በአንድ ጊዜ ሁለት ማስተርስ ከመማር አላገደውም።
“ለዛሬ ስኬቴ በተለይም በክፍል ትምህርቴን ለመማርና ለማጥናት በማደርገው ጥረት ባለቤቴ ከጎኔ ሆና የሰጠችኝ የጊዜ ነፃነት ትልቁን ስፍራ ይዛል” በማለት ባለቤቱ ያደረገችለትን ድጋፍ ይናገራል።
የጊዜ ገደብ ሳይኖር ረጅም ሌሊቶችን በስራና በንባብ በማሳለፍ ለዛሬ መብቃቱን የሚገልጸው ተመራቂው፤ ጊዜውን በአግባቡ በስራ ላይ ለማዋል እንዲያመቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙ በእጅጉ መቀነሱን ያወሳል።
እንዲሁም እጅጉን አስፈላጊ ካልሆኑ እና ጊዜን በከንቱ ከሚያባክኑ ማህበራዊ መስተጋብሮች በመታቀብ በሙያዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ተሳትፎ በማድረግ ጉልበቱንና ጊዜውን በአግባቡ ሲጠቀም እንደነበር ይናገራል።
በቀጣይም ባገኘው ተጨማሪ እውቀት እና ክህሎት ህዝብና ሀገርን ለማገልገል ቆርጦ ስለመነሳቱ ገልጿል።

