ለመጀመሪያ ጊዜ ትዘታ ዘፈንን በመዘፈን መድረክ ላይ የወጣችው የያኔዋ እሌኒ ሰብስቤ የዛሬዋ ኩኩ ሰብስቤ በ1970ዎቹ አጋማሽ ነበር በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀ የተማሪዎች የምረቃ ፕሮግራም ላይ በአጋጣሚ በጓደኞቿ ገፋፊነት መድረክ ላይ ወጥታ የተጫወተችው፡፡ ኩኩ በፍርድ ቤት ስሟን ወደ ኩኩ እስክትለውጥ ድረስ ስሟ እሌኒ ነበር፡፡ ኩኩ ወደመድረክ ላይ ስትወጣ ባወጣችው ድምፅና በተጫወተችው ትዝታ ዜማ ያልገተገረመ አልነበረም፡፡ኩኩ ትዝታን በማንጎራጎር ወደ መድረክ መጥታ ከ30 ዓመታት በላይ የሙዚቃ አፍቃሪያንን አስደስታለች፡፡ ሰሞኑን 8ኛ ዓልበሟን ለአድማጭ ያቀረበችው ኩኩ ከ7 ዓመት በላይ የተለፋበትን ሙዚቃ 8 ዘፈኖችን ተወዳጁ አርቲስት ቴዲ አፍሮ ነው የሰራላት፡፡ እርግጥ ኩኩ የቴዲ ምርጫ መሆኗን የዛሬ 20 ዓመት ‹‹ጊዜ ስጠኝ›› የተሰኘውን አልበሟን ስታወጣም ቴዲ ሶስት ዜማዎችን ሰርቶላታል፡፡
ልጅነት
ኩኩ በልጅነቷ በጣም ተጫዋች፤ ረባሽና ሙዚቃ የምትወድ ልጅ ነበረች፡፡በትምህርት ቤት ቆይታዋም በየክፍሉ እየዞረች ስትዘፍን በተማሪዎችና በመምህሮቿ ይሰጣት የነበረው አድናቆት በዘፋኝነት ህይወቷን እንደምትመራ አመላክቷታል፡፡ በልጅነቷ የራዲዮ የዘፈን ምርጫና የቴሌቪዥን የህብረ ትርዒት ፕሮግራሞች ላይ የሚቀርቡ ዘፈኖች አያመልጧትም ነበር፡፡ከሰማች ደግሞ በአንድ ግዜ ቀብ ታደርግ ነበር ግጥምና ዜማቸውን፡፡ ኩኩ ከሚዲያ ክትትሏ በተጨማሪ ታላላቅ እህቶቿ አዳዲስ ካሴቶች ሲወጡ ከጓደኞቻቸው ጋር ተውሰው ሲያመጡ ዋነኛዋ አዳማጭ ኩኩ ነበረች፡፡ሙዚቃውን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ግጥሞቹን ገልብጣ ታጠና ነበር፡፡ያጠናችውንም ዘፈን ትምህርት ቤት ስትሄድ ለጓደኞቹ ታንጎራጉር እንደ ነበር ታስታውሳለች፡፡
የእነ ብዙነሽ በቀለ፤ አለማየሁ እሸቴ፤ ጥላሁን ገሠሠ፤ ታምራት ሞላ ማህሙድ አህመድ፤ጌታቸው ካሳ ፤ ሂሩት በቀለንና አስናቀች ወርቁን ዘፈኖች የወንዱንም የሴቷንም እያፈራረቀች ትዘፍን ነበር፡፡አጋጣሚው ጥሩ የሆነላት ታዲያ በልጅነቷ ዘፈኑን ከምትዘፍነው ከአንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ጋር በአንድ መድረክ ከመዝፈንም አልፋ እየተቀባበሉ ‹‹እንግዳዬ ነሽ፤ የእኔ እንግዳ በበሩ ገብተሽ አረፍ በይ ጓዳ›› የተሰኘውን ዘፈን አብራ ለማቀንቀን እድል ማግኘቷ ነበር፡፡ ኩኩ ይህንን አጋጣሚ በልዩ ሁኔታ ታስታውሰዋለች፡፡‹‹የዛን ጊዜ ገና የመጀመሪያ ካሴቴን አላወጣሁም ነበር፡፡ ካሴት ከመስራቴ በፊት ከአለማየሁ ጋር ተገናኝቼ እስኪ አብራው ትዝፈንና ትታይ ተብየ ነው አብሬው የዘፈንኩት፡፡›
‹‹እንግዳዬ ነሽ›› የተሰኘው የአለማየሁና የኩኩ ዘፈን በቴሌቪዥን ተቀርፆ ሲቀርብ ኩኩ ከፍተኛ አድናቆት አገኘች፡፡ ‹‹ደግሞ ይህቺን የመሰለች ድንቡሽ ቡሽ ልጅ ከየት ነው የመጣችው ?›› ያላለ አልነበረም፡፡ ‹‹እንግዳዩ ነሽ ›› ዘፈን በቴሌቪዥን የተቀረፀው ደብረ ዘይት ሆራ ሀይቅ ዳርቻ ነው፡፡ አይን አፋሯ ኩኩ የመጀመሪያ የቴሌቪዥን ቀረፃ ላይ ለካሜራ ባለሙያዎች በጣም አስቸግራቸው እንደነበር ትናገራለች፡፡ ለምን?
‹‹የመጀመሪያ ጊዜዬ ስለነበረ ብዙ ጊዜ ይቀረፅ ነበር፡፡ ከዘፈኑ ጋር የአፌ እንቅስቃሴ አብሮ አልሄድ እያለ ያስቸግራቸው ነበር፡፡ በወቅቱ ዳይሬክተሯ የአርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ባለቤት አምሳለ ገነት ይመር ስለነበረችና በጣም እየመከረችኝ ነው ቀረፃውን የጨረስኩት›
ኩኩ የመጀመሪያ የመድረክ እይታዋ በተማሪዎች ምረቃ ላይ ሂልተን ሆቴል ስትዘፍን የተመለከቷት በወቅቱ ታዋቂ የነበሩት ዋሊያስና አይቤክስ ባንዶች ‹‹ለምን እኛ ጋር አትሰሪም?› የሚል ግብዣ ያቀረቡላት ወዲያውኑ ከመድረክ ሳትወርድ ነበር፡፡ኩኩ ግን ከመድረክ እንደወረደች ምላሽ አልሰጠችም ነበር፡፡‹ምክንያቱም› ትላለች ኩኩ ‹‹ምክንያቱም አባቴን ማስፈቀድ ነበረብኝና መዝፈን እፈልጋለሁ ፍቀድልኝ ብዬ ጠየቅሁት›› ትላለች፡፡ የአባቷ ምላሽ ግን አሉታዊ ነበር ‹‹ ለምን ዩኒቨርሲቲ ገብተሽ ትምህርትሽን አትቀጥይም? ግን ፍላጎትሽ ሙዚቃ ከሆነ ምን አደርጋለሁ፤ እኔ ግን መድረክ ላይ ስትዘፍኚ መጥቼ አላሽም ›› አሏት፤ እውነትም ደጃዝማች ሰብስቤ ኩኩ በመድረክ ላይ ስትዘፍን አንድም ቀን ሳያዩዋት ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡ በመሆኑም አሁን ያወጣችውን አዲስ አልበም ርዕስ ለአባቷ መታሰቢያ ያደረገች ሲሆን ስያሜውንም ‹ደጃዝማች› ብላዋለች፡፡የዚህ ዘፈን የግጥምና ዜማ ደራሲው ቴዲ አፍሮ ሲሆን በድምፅም ያጅባታል፡፡
የዘፈን ግጥም መፃፍ ብቻ ሳይሆን ሙዚቃ መስማት ራሱ እንደ ነውር በሚታይበት በዚያ ዘመን አባቷ ደጃዝማች ሰብስቤ የሙዚቃ ወዳጅ ነበሩ፡፡ ወዳጅ ብቻ ሳይሆኑ የዘፈን ግጥሞችን ይፅፉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከሙሉቀን መለሰ ቀደምት ስራዎች መሀከል የደጃዝማች ሰብስቤ ግጥሞች ይገኙበታል ትላለች ኩኩ ሁኔታውን ስታስታውስ፡፡‹‹አባቴ ሙሉቀን መለሰን በጣም ነበር የሚወደው፤ እናም የዘፈን ግጥሞችን እየፃፈ ወስደሽ ስጭው ይለኝ ነበር፡፡ ሙሉቀንም ግሩም አድርጎ ነበር የሚጫወታቸው፡፡ ግጥሞቹን አባቴ ቢፅፋቸውም የአባቴ መሆናቸው አይታወቁም ነበር፡፡እንዲገለፅም አባቴ አይፈልግም ነበር፡፡› ያም ሆኖ ግን ደጃዝማች ሰብስቤ ምንም እንኳን ሙዚቃ ወዳጅ ቢሆኑም ኩኩ ወደ ሙዚቃው ዓለም እንዳትገባ ነበር ፍላጎታቸው፡፡
ኩኩ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሙዚቃው ዓለም እንደገባቸው የምሽት ክለብ መስራት የጀመረችው ራስ ሆቴል ከአይቤክስ ባንድ ጋር ነበር፡፡ኩኩ በሳምንት ሁለት ቀናት አርብና ቅዳሜ መስራት ስትጀምር ባንዱ ማስታወቂያ አስነግሮ ነበር፤ እንዲህ የሚል‹ Ibex band is proud to presnt Kuku Sebsebe!› ይህ እድል ለእኔ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ገና ካሴት ሳላወጣ ነበር አይቤክሶች ይህንን እድል የሰጡኝ የምትለው ኩኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዋሊያስ ባንድ በከፍተኛ የክፍያ ወደ ሂልተን ሆቴል አዛወራት፡፡‹‹በወቅቱ ራስ ሆቴል 150 ብር ነበር የማገኘው ፤ ወደ ሂልተን ስዛወር ግን ዋሊያስ ባንዶች በሳምንት አራት ቀን ዝፈኚልኝ ብለው 600 መቶ ብር እንክፈልሽ ሲሉኝ አይኔን አላሸሁም›› ትላለች፡፡ ኩኩ በወቅቱ ብሩ ሳይሆን ያጓጓት በሳምንት ሁለት ቀን ከምትዘፍንበት ወደ አራት ቀን ከፍ መደረጉ ነበር፡፡ በዛ ላይ በወቅቱ በሂልተን ሆቴል የምትዘፍን ሴት ዘፋኝ ስላልነበረች የመጀመሪያዋ ሆና ነው ከዋሊያስ ጋር ስራ የጀመረችው፡፡ ከዚያም ወደ ካሴት ስራና ከሮሃ ባንድ ጋር መስራት ስትጀምር የሙዚቃ አድማጩን ጆሮ በድምፃ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን በጸጉር ስታይሏ በቁጥርጥርና ዶቃ ጌጧ የከተማው ሴቶች ፋሽን መሪ ሆነች፡፡ ኩኩ ስታይል አሁንም ድረስ የምትታወቅበት ስታይሏ ነው፡፡
ኩኩ ከተለያዩ ድምፃውያን ጋር በጋራ በማቀንቀን ትታወቃለች፡፡ ከአለማየሁ እሸቴ ሌላ ከዳምጠው አየለ፤ ከቴዎድሮስ ታደሰና ቴዲ አፍሮ ጋር፤ እንዲሁም ከተወዳጁ ኤፍሬም ታምሩ ጋር ዘፈኖችን ተጫውታለች፡፡ ከሁሉም ዘፈኖች በተለየ ሁኔታ ከኤፍሬም ታምሩ ጋር የተጫወተችው ‹ዛልዬ ና ዛሌዋ› የተሰኘው ዘፈን የተለየ ትዝታ አላት፡፡‹ በወቅቱ ዘፈኑ በወጣበት ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሰፈራ ቤት ለመስራት ወደ ገጠር የሄዱበት ወቅት ነበር፡፡ እናም ዘፈኑን ለማቅረብ ከሮሃ ባንድ ጋር መተከል ጣቢያ ድረስ ሄደን ነበር፡፡ያ ሁሉ ተማሪ ዘፈኑን ስናቀርብ አብሮን ነበር በጋራ ይጨፍር የነበረው፡፡›
ለመሆኑ ኩኩ ዘፋኝ ባትሆን ኖሮ ምን ትሆን ነበር? ኩኩ ለዚህ ጥያቄ ፈጣን ነበር መልሷ፡፡ ‹‹ዘፋን ባልሆን ኖሮ ዘፋኝ ነበር የምሆነው›› ትላለች በተለመደው ሳቋ አጅባ፡፡ ‹የፍቅር ሰው ነኝ!› የምትለው ፍልቅልቋ አርቲስት ኩኩ ሀገሯን የምትወድ፤ በሰው ጉዳይ ጣልቃ የማትገባና ብድር የማትወድ አርቲስት ነች፡፡ ጨዋታ አዋቂና ሳቂታ የሆነችው ኩኩ ከሙዚቃ ችሎታዋ በተጨማሪ ወግ አዋቂ መሆኗን በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳይታለች፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊትም ‹ከኩኩ ጋር ጨዋታ› የተሰኘ የቴሌቪዥን ቶክ ሾው በአባይ ቲቪ ላይ ማቅረብ ጀምራ በታላቅ እህቷ ሞት ሳቢያ ማቋረጧ ይታወሳል፡፡
ደጃዝማች አልበሟ
ተወዳጇ ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ ከዚህ በፊት ሰባት ያህል አልበሞችን ለአድማጮች ያቀረበች ሲሆን የመጨረሻዬ ነው ያለችውንና 7 ዓመት የፈጀውን አልበም ሰሞኑን አውጥታለች፡፡
ኩኩ ሰብስቤ ደጃዝማች የተሰኘው አልበም ሲሰራ ያለቀሰችበት አጋጣሚዎች እንደነበሩም ገልጻለች፡፡ ሰባት ዓመት ፈጅቷል የተባለው ደጃዝማች አልበም ቴዲ አፍሮ 8 ሙዚቃዎችን በዜማና ግጥም እንዲሁም በአጃቢነት እንደተሳተፈም ታውቋል፡፡
‹ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ስራ ለሌላ ሙዚቀኛ ሲሰጥ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደራሱ አድርጎ፤ሌሊት ሳይቀር እያደረ የሚሰራ ነው፤ይህንንም በዚህ አልበም ላይ አሳይቷል ነው ያለችው ኩኩ አልበሙ በጥሩ ስሜት የተሰራ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በተደጋጋሚ ቀጠሮ ምክንያት ከአቀናባሪው አቤል ጳውሎስ ጋር ልትጣላበት የነበረበት እና የሙዚቃውን ስራንም ከእርሱ ጋር ለመስራት የገባችውን ውል ልታቋርጥ ሁላ እንደነበረ ኋላ ግን በህመም ምክንያት እንደሆነ ስትረዳ ሁሉንም ነገር እንደተወችውና እርሱንም ስታስታምም እራሷን እንዳገኘችው ስለ ስራው አጋጣሚ ስታወራ ገልጻለች፡፡
8ተኛዋ የሆነው ደጃዝማች አልበም የተለየ እንደሆነም ገልጻለች፡፡አንጋፋው የግጥም ደራሲ ይልማ ገብረዓብ፡ቴዲ አፍሮ፡ናትናኤል ግርማቸው፡መሠለ ጌታሁን፡መሠለ አስማማው እና ፍሬዜር አበበወርቅ በግጥምና ዜማ ተሳትፈውበታል፡፡
ከዚህ በኋላ በነጠላ ዜማ ካልሆነ በአልበም ደረጃ እንደማትመጣ አስታውቃለች፡፡ ኩኩ ሰብስቤ በቀደመው ጊዜ አልበም ሰርቶ ለማጠናቀቅ አስራምስት የስራ ቀናት ብቻ እንደሚበቃ አስታውሳ፤ የአሁኑ ደጃዝማች አልበም ግን 7 ዓመት እንደፈጀባት ተናግራለች፡፡
ታዋቂው ሙዚቃ አቀናባሪ አቤል ጳውሎስ የአልበሙን አብዛኞቹን ሙዚቃዎች እንዳቀናበረ እና አሬንጅመንቱንም እንደሰራው ተነግሯል፡:
ለዓለም አቀፍ አድናቂዎቿ በላከችው ሞቅ ያለ እና ልባዊ መልእክት ኩኩ እንዲህ ብላለች፤“ሰላም ለምወዳችሁ አድናቂዎቼ እና ወዳጆቼ በሙሉ በዓለም ዙሪያ! ከረጅም እረፍት በኋላ፣ አዲሱ አልበሜ “ደጃዝማች” ሚያዝያ 24 ቀን 2017 እንደሚለቀቅ ስገልጽላችሁ በታላቅ ደስታ ነው።”
“ደጃዝማች” የሚለው ርዕስ በታሪክ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ እና የመኳንንት ማዕረግ ሲሆን ጥንካሬን፣ አመራርን እና የባህል ቅርስን የሚያመለክት ሲሆን እነዚህም በአልበሙ ውስጥ በዋናነት የተንጸባረቁ ጭብጦች ናቸው።›› ብላለች፡፡ የኩኩ አልበም በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ በጥልቅ ስር የሰደደ የግል እና የጥበብ መገለጫ ሲሆን ዘመናዊ የሙዚቃ ድባብን ያካትታል።
አድማጮች የኩኩን ልዩ የድምፅ አገላለጽ እና የግጥም ጥልቀት ባካተተ መልኩ በባህላዊ የኢትዮጵያ ዜማዎች እና በዘመናዊ የሙዚቃ ተጽዕኖዎች የበለፀገ ውህደት እያጣጣሙ ነው። “ደጃዝማች” ለረጅም ጊዜ የቆዩ አድናቂዎችን እና አዲስ ትውልድን ለማስተጋባት እና በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የባህል ምዕራፍ ለመሆን ተዘጋጅቷል።
አልበሙ ቀድሞውንም ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው ሲሆን፣ መለቀቁም በሙዚቃ አፍቃሪዎች፣ በባህል ወዳዶች እና በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ በቅርብ እየተደመጠ ነው። በአመቱ ከሚደመጡ በጣም ተወዳጅ አልበሞች መካከል አንዱ እንደሚሆን በሰፊው ይነገራል።
ኩኩና ቦብ ማርሊ
አንጋፋዋ ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ መድረክ ላይ ሲዘፍን ባለማወቄ እስከ ዛሬ ድረስ የማዝንበት አጋጣሚ ነበር ስትል ትቆጫለች፡፡
ለኢትዮጽያ የተለየ ፍቅር የነበረው እንዲሁም የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታይ የነበረው ቦብ ማርሌይ በህይወት እያለ በ1971 ዓ.ም ኢትዮጽያን ጎብኝቷል፡፡
ወደ ኢትዮጽያ በመጣበት ጊዜ ‹በጊዮን ሆቴል የኢትዮጵያንን ሰንደቅ አላማ ለብሶ አይቼዋለሁ ነገር ግን በወቅቱ ባለማወቄ እስከ ዛሬ ድረስ ይቆጨኛል› ነው ያለችው፡፡
የሙዚቃ ስራውን በመድረክ ላይ ሲያቀርብም ‹ይህን ሰውዬ አስወርዳችሁ ሙሉቀን መለሠ ይዝፈንልን ብለን ነበር፤ በዚህም እቆጫለሁ› ብላለች፡፡
የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ በ1971 ዓ.ም ወደ ኢትዮጽያ መጥቶ በነበረብ ስዓት ብዙ ሰው አላወቀውም ነበር፡፡ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት ኢትዮጽያዊያን ለቦብ ማርሊ ትኩረት እንዳይሰጡት አድርጎት እንደነበር ይነገራል፡፡ ኩኩ ሰብስቤም ካላወቁት ሰዎች ውስጥ አንዷ እንደነበረች ነው አዲሱን ደጃዝማች አልበሟን ለማስተዋወቅ በጠራችው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያነሳችው፡፡

