ፍርድ ቤት ቅርስነቱን አረጋግጦ እንዳይፈርስ ውሳኔ ያሳለፈበት የ90 ዓመቱ ሎምባርዲያ ሬስቶራንት ፈረሰ

  • ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ሕንፃው በቅርስነት የተመዘገበ አይደልም ብሏል

ፍርድ ቤት በቅርስነት እንዲቆይ ውሳኔ የሰጠበት፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘውና በአዲስ አበባ ከተማ አሻራን ከያዙ ታሪካዊ ቤቶች መካከል ባለ 90 ዓመቱ ዕድሜ ጠገቡ ሎሞባርዲያ ሬስቶራንት ፈረሰ፡፡

የቅርስነት መሥፈርቱን አሟልቶ ከተመዘገበ በኋላ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ኪነ ጥበባት ቢሮ፣ ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንና ለሌሎች ተቋማት ‹‹የሕንፃው ከቅርስነት ተሰርዟል›› በሚል የቀረበው በሕገወጥ መንገድ መሆኑን ጠቅሶ ውሳኔው መሻሩን የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወስኖ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በ1926 ዓ.ም. እንደተገነባ የሚገርለትና ዋቤ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው ሎምባርዲያ ሬስቶራንት ከሰሞኑ በግልጽ ባልተብረራ መልኩ ‹‹ለልማት ይፈለጋል›› በሚል በግሬደር እየፈረሰ ሲሆን፣ ሊቆጣጠር የሚገባው የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ግን ‹‹ሕንፃው ቅርስ አይደለም›› ብሏል፡፡

ሕንፃውን ከዚህ ቀደም የልደታ ክፍል ከተማ ሊያፈርሰው በተነሳበት ወቅት፣ የቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከመንግሥት ተቋማትና የሕንፃው ወራሾች ጋር በመሆን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ እንዳይፈርስ ክርክር ማድጉን ሪፖርተር ከዚህ ቀደም ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል፡፡

የሕንፃውን ቅርስነት በተመለከተ ሪፖርተር ማብራሪያ የጠየቃቸው የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ‹‹ውሳኔ ከሰጠንበት ዓመት አልፏል፡፡ አንበሳ ፋርማሲን፣ ሎምባርዲያንና ሌሎች አጨቃጫቂ ሕንፃዎችን/ቅርሶችን በተመለከተ ‹‹የሚገዛና የከተማ ቅርስ ምንድነው›› የሚል ስድስት መሥፈርት በማውጣት መዝነናል›› ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት አንድ የከተማ ሥነ ሕንፃ ለመባል ማሟላት ያለበት ጉዳይ በመኖሩ፣ ‹‹ይህ ሕንፃ ያን አያሟላም፣ የቅርስ እሴት ይዞ መመዝገብ አይችልም›› በሚል መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ሕንፃው ከዚህ በፊት በቅርስነት ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም፣ በተደረገው ጥናት መሥፈርቱን የማያሟላ በመሆኑ ከቅርስነት ወጥቷል ብለዋል፡፡ የሕንፃ ዕድሜ አንድ የመለኪያ መሥፈርት ቢሆንም ዝም ብሎ 100 ወይም 200 ዓመት ስለሞላው ብቻ ቅርስ ሊባል አይቻልም ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ የቅርስ ሁኔታንና ቁመናን በተመለከተ ከሁሉም ወገኖች የሚነሱት ጉዳዮች ፈታኝ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከሰሞኑ በተመሳሳይ በቅርስነት የተመዘገበ ያሉትን ኢየሩሳሌም ሕንፃ የተሰኘ የቀድሞ ቅርስ ፈረሰ ሲባል የነበረው በትክክለኛ መረጃ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በአዲስ የቅርስ ምዝገባ መሥፈርት አዲስ አበባ ከተማ እንደ አዲስ ምዝገባ እንዲጀመር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው በቃ ይሁን ወይም አይሁን በሚል እንጂ ቅርስ መሆን ሲገባው ያልሆነ፣ መሆን ያልነበረበት ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህን ለመፍታት በሚያግዝ መልክ መመርያውን መሠረት አድርገን ሥራውን በትክክል እንዲሠራ ይደረጋል ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe