ፍቅረኛን በቢሮ ውስጥ ገድሎ ለ6 ዓመታት ተሰውሮ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ተከሳሹ በሌለበት በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈርዶበት እንደነበርም ተገልጻል፡፡
ተከሳሽ ጌታቸው አለምፀሃይ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ጥር 2/2011 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ሳባ ህንጻ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መረጃ እንደሚያሳየው ተከሳሹ በህንጻው 6ኛ ፎቅ ወደሚገኘው የክፍለ ከተማው የፋይናስና ኢኮኖሚ ልማት ፅ/ቤት ቢሮ ፍቅረኛየ በሚላት መዓዛ ከሳ ላይ የግድያ ወንጀል ፈጽሟል፡፡
አልፈልግህም ብላኛለች በሚል ምክኒያት ነው ቢሮዋ ድረስ በመሄድ ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረገው ተብሏል፡፡
ተከሳሹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶታል፡፡
ግለሰቡ በፖሊስ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ ቤት በነበረበት ወቅት በህመም ምክኒያት ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ የካቲት 19/2011 ዓ.ም ጥያቄ አቅርቦ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ በዚያው ሊጠፋ ችሏል፡፡
በአቃቢ ህግ ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በሌለበት በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱን ፖሊስ ገልጻል፡፡
በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተደራጅቶ የቀረበለትን የክስ መዝገብ ሲመለከት የቆው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በነሃሴ3/2014 ዓ.ም ውሎው ጌታቸው አልፀሐይ በሌለበት በእድሜልክ እስራት እንዲቀጣ እና ከህዝባዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻር ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
የፍርድ ቤቱን የቅጣት ውሳኔ ተፈጻሚ ለማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ የክትትልና ኦፕሬሽን ክፍል ፍርደኛውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ እሁድ እለት መጋቢት 21/2017 ዓ.ም ሆለታ ከተማ ውስጥ ከተደበቀበት ስፍራ ወንጀሉ ከተፈጸመ ከ6 ዓመታት በኋላ በድጋሚ ተይዟል፡፡

