ከአደጋዉ ስድስት ሰዎችን መታደግ ተችሏል ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 9:05 ሰዓት ላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 6 ሳሪስ በአንድ ፔንሲዮን በተነሳ የእሳት አደጋ ሁለት ሰዎች በጪስ ታፍነዉ ህይወታቸዉ አልፏል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአደረጉት ርብርብ በፔንሲዮን በክፍል ዉስጥ ተኝተዉ የነበሩ ስድስት ሰዎችን መታደግ የቻሉ ሲሆን የእሳት አደጋዉ ሳይስፋፋ በፍጥነት መቆጣጠርም ችለዋል። በጪስ ታፍነዉ በአንድ ክፍል ዉስጥ ህይወታቸን ያጡት የ30 ዓመት ወንድና የ25 ሴት ናቸዉ። ፔኔሲዮኑ የዉስጥ ክፍሉ እሳትን መቋቋም ከማይቹሉና አደጋን አባባሽ ከሆኑ በቺፑድ እና በጣዉላ የተከፋፈሉ መሆናቸዉ እሳቱ እንዲባባስና ጪስ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ፔንሲዮኖችና የሆቴል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ወይም ባለንብረቶች እንግዶች የሚያርፉባቸዉን ክፍሎች የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ያሟሉና የተጠበቁ በማድረግ የደንበኞቻቸዉ ደህንነት በመጠበቅ አስፈላጊዉን ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸዉ ሲሆን ኮሚሽኑ የአደጋ ደህንንነት መስፈርትን በማያሟሉ አገልግሎት መስጫዎች ላይ አስፈላጊዉን ዕርምጃ እንደሚወስድ ያሳስባል።

