ፖሊስ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሕይወቱ ያለፈበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ አስታወቀ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ሕይወቱ ያለፈበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እያደረገ ሲሆን አስከሬኑም በባለሙያዎች ምርመራ ሊደረግበት መሆኑን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፣ ማዲንጎ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 17/2015 ዓ.ም. ጠዋት 1፡30 አካባቢ ለሐኪሙ ስልክ እንደደወለና ወደ ክሊኒክ መሄዱን ፖሊስ መረዳቱን ገልጸዋል።

ከዚያም በኋላ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወደሚገኘው አንድ የግል ክሊኒክ በመሄድ የህመም ማስታገሻዎችን እና ሌሎች መድኃኒቶችን መውሰዱንና 3፡00 ላይ ሕይወቱ ማለፉን እስካሁን ፖሊስ አገኘው ያሉት መረጃ ጠቅሰው ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ የድምጻዊ ማዲንጎ አስክሬን ሕይወቱ ካለፈበት የግል ክሊኒክ ወደ አቤት ሆስፒታል ተወስዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፖሊስ በቀረበለት አቤቱታ መሠረት የድምጻዊውን ሞት መንስኤ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ እንደሆነ የገለጹት ኮማንደር ማርቆስ፣ ምርመራው እንደተጠናቀቀ ውጤቱን ፖሊስ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ሲሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተወዳጁ ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ማንነበር ?

– ማዲንጎ የተወለደው ጎንደር አዘዞ ሲሆን ልክ በ3 ወሩ ወላጆቹ ደብረ ታቦር መግባታቸውን ተከትሎ በደ/ታቦር ነው ያደገው።

– ማዲንጎ አፈወርቅ ያደገው በጦር ቤት ውስጥ ነው፤ እናት እና አባቱ “ተገኔ” /የኔ ጠበቃ/ ነበር የሚሉት፤ ወላጆቹ ያወጡለት ስም “ተገኔ” ነው። ማዲንጎ የሚለውን ስም ያገኘው በወታደር ቤት ውስጥ እየሰራ እያለ ነው፤ ከዛ በኃላ መጠሪያው ሆኖ ቀጥሏል።

– በልጅነቱ የሙዚቃ ፍቅር ያደረገበት ማዲንጎ ከደብረ ታቦር ወደ አዘዞ በተመለሰበት ወቅት በ7ኛ ክፍለ ጦር ካምፕ ውስጥ በ603ኛ ኮር ውስጥ ያለ የሙዚቃ ቡድን ልምምድ ሲያደርግ በመግባት ዘፈን እንደሚችል በመግለፅ እድል እንዲሰጠው ይጠይቃል፤በኃላም እድል ተሰጥቶ የኤፍሬም ታምሩን ሙዚቃ ከተጫወተ በኃላ አድናቆት በማግኘቱ ተቀባይነት አግኝቶ በዛው ሊቀጥል ችሏል።

– ማዲንጎ ከጦሩ ከወጣ በኃላ በ1982 ዓ/ም አካባቢ ገና በ12 ዓመቱ በባህር ዳር የሙዚቃ ስራዎችን በማቅረብ አንድም ድምፃዊ የመሆን ህልሙን መስመር ያስያዘበት በሌላ በኩል ገቢ በማግኘት እራሱንና ቤተሰቦቹን ማገዝ የቻለበትን ሁኔታ መፍጠር ችሏል።

– ማዲንጎ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኃላ በተለያዩ የሙዚቃ ክበቦች የተለያዩ አንጋፋ ድምፃዊያንን ስራዎች ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን በኃላም የራሱን ስራዎች (ነጠላና የአልበም ስራዎች) ለአድናቂዎቹ አቅርቧል።

– ማዲንጎን በስራዎቹ የሚያውቁት ወዳጆቹን ዜማ በመያዝ ችሎታ፣ ሙዚቃን አሳምሮ በመጫወትና የአድናቂዎቹን ቀልብ በመሳብ የተካነ በማህበራዊ ህይወቱም ተግባቢ፣ ቅንና ተጫዋች እንደሆነ ይመሰክሩለታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe