ሀብት ባላስመዘገቡ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ምርመራ እንዲደረግባቸው ዝርዝራቸው ተላለፈ

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁሉም ሚኒስትሮች ሀብታቸውን አስመዝግበዋል

ሀብት ለማሳወቅና ለማስመዝገብ ከአሥር ዓመታት በፊት ተግባራዊ የተደረገውን አዋጅ ቁጥር 668/2002 ድንጋጌ መሠረት አድርገው፣ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ አሥር ሚኒስትር ዴኤታዎችና 174 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ምርመራ እንዲደረግባቸው፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዝርዝራቸው መተላለፉ ታወቀ፡፡

አዋጁን የማስፈጸም ሥልጣን ከተሰጠው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአዋጁ ድንጋጌ መሠረት ሀብታቸውን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንዲያስመዘግቡ የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸው ነበር፡፡

በኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመንግሥትን አሠራር በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ መመሥረት አስፈላጊ ነው፡፡ ሀብትን ማሳወቅና ማስመዝገብ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመከላከልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው አዋጁ መውጣቱን አስታውሰው፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት (ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞችን ያካትታል) ኃላፊነትንና የግል ጥቅምን ሳይቀላቅሉ፣ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት መዘርጋት ሊፈጥር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስወገድ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ ላለፉት አሥር ዓመታት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ሀብት የማሳወቅ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፣ ተቋሙ እየተገበረ ያለውን የሪፎርም ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ማለትም ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ እንዲሁም ከክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስከ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ ያሉ ባለሥልጣናት ሀብታቸውን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ እንዲያስመዘግቡ ጊዜ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በሰኔ መጨረሻው ሳምንት አካባቢ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሀብት ማስመዝገቢያውን ጊዜ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ መራዘሙንም አክለዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉም ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሙሉ በሙሉ ሀብታቸውን ማሳወቃቸውንና ማስመዝገባቸውን (ከአንድ በሚኒስትር ማዕረግ ካሉ ባለሥልጣን በስተቀር) የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አሥር ሚኒስትር ዴኤታዎችና ከከተማ አስተዳደሩ ደግሞ 174 ባለሥልጣናት የአዋጁን ድንጋጌና የአስፈጻሚውን ተቋም የዕለት ከዕለት ውትወታ ቸል ብለው በማለፋቸው፣ የአዋጁን ድንጋጌ በመከተል ምርመራ እንዲደረግባቸውና እንዳስፈላጊነቱ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ፣ ዝርዝራቸው ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ መተላለፉን አስታውቀዋል፡፡

በክፍላተ ከተማ ከአፈ ጉባዔ እስከ ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ፣ እንዲሁም በ121 ወረዳዎች ያሉ አመራሮችን በሚመለከት ከክፍለ ከተማ ካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ፣ ከሥራ አስፈጻሚና ከሥነ ምግባር መኮንኖች በማውጣጣት መድረክ በመፍጠር ሀብታቸውን ከማሳወቅና ከማስመዝገብ ጋር በተያያዘ፣ ሁለት አማራጮችን ማስቀመጣቸውን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡ ይኼም በተቀመጠው ቀነ ገደብ ያላሳወቀና ያላስመዘገበ አመራር (ኃላፊ) በአምስት ቀናት ውስጥ 1,000 ብር እየተቀጣ እንዲያስመዘግብ፣ ያንን ሳያደርግ ከቀረ ደግሞ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ለፖሊስ ስም ዝርዝራቸው ተላልፎ ምርመራ እንዲጀመር የሚል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም የተጠቀሱ ኃላፊዎች ከመስከረም 18 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 1,000 ብር እየተቀጡ እንዲያስመዘግቡና እንዲያሳውቁ ጊዜ ገደብ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡ ቀነ ገደቡ እስከ መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የነበረ ቢሆንም፣ በኢሬቻ በዓል ምክንያት ተጨማሪ ቀናት በማስፈለጉ መራዘሙንም አክለዋል፡፡

ማስታወቂያው ከተነገረበት ዕለት አንስቶ በጣም በርካታ ኃላፊዎች እየተቀጡ እየተመዘገቡ መሆናቸውን፣ እስከ ቀነ ገደቡ ማብቂያ ድረስ ሁሉም ይመዘገባሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ሥራ በፌዴራልና በከተማ አስተዳደሩ የበታች ሠራተኛ ድረስ እንዲቀጥል መደረጉን፣ በ2013 በጀት ዓመት ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሠራተኞችን ሀብትና ንብረት ለመመዝገብ ዕቅድ መያዙን አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe