ሃይንከን  ኢትዮጵያ ውጤታማ ለሆኑ የአርሲ ገብስ አምራች አርሶ አደሮች የእውቅና መርሃ ግብር አካሄደ

በአርሲ ዞን ደመናብ ወረዳ በገብስ እርሻ ስራ ላይ የተሰማሩት አርሶ አደር  ሲሳይ መካሻ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ዴንሲ አብዲ ከሰባት  ዓመታት  ጀምሮ ለአሰላ ብቅል ፋብሪካ የሚቀርብ የቢራ ገብስ በማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ነበሩ፤ አቶ ሲሳይ እንደሚሉት ሃይንከን ኢትዮጵያ ወደ ዞናቸው መጥቶ ምርጥ ዘር እንዲጠቀሙና የእርሻ ስራቸውን እንዲያዘምኑ ስልጠና ካገኙ በኋላ በሄክታር ቀደም ሲል ያገኙ የነበረውን 25 ኩንታል ከእጥፍ በላይ ማሳደጋቸውን ይናገራሉ፤ ምርጥ ዘሩን አየሩ እንደወደደውና የተሻለ ምርት እንዲሰበስቡ እንዳደረጋቸው በማከል፤

Farmers award

አቶ ሲሳይና ባለቤታቸው እንደሚሉት ከሆነ የቢራ ገብስ ላለፉት ሰባት ዓመታት በሄክታር ከ60 እስከ 70 ኩንታል ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን የገበያ ችግራቸውንም በሃይንከን መቀረፉ ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉና ልጆቻቸውንም በተሻለ ሁኔታ ለማስተማር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹የእኛ ቡና ገብሳችን ነው› የሚሉት ተሸላሚው አርሶ አደር አቶ ሲሳይ በቅርቡ ገብሳችንን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ እንደ ቡና የውጭ ምንዛሬ እናገኛለን› ይላሉ በልበ ሙሉነት፤

የምዕራብ አሩሲ ዞን ሻሸመኔ ወረዳ ሙርሳ ቀበሌ  ነዋሪ የሆኑት ሌላው ተሸላሚ አርሶ አደር አቶ መርጋ ገመዳ  ደግሞ ሃይንከን ኢትዮጵያ ባቀረበው የምርጥ ዘር፤ የፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል  ስልጠና ታግዘው የቢራ ገብስ በማምረታቸው ውጤታማ አርሶ አደር መባላቸውን ይናገራሉ፡፡ አቶ መርጋ  እንደሚሉት በስልጠናውና በግብርና ባለሙያዎች ያተቋረጠ ክትትል ታግዘው በሄክታር የሚያገኙትን የቢራ ገብስ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችለዋል፤

Farmer Ato Merga Gemeda

‹ማየት ማመን ነው› የሚሉት አቶ መርጋ በቅርቡ ምርቱን ለመሰብሰብ እየተዘጋጁ ያሉበትን የገብስ ማሳ እያሳዩ ‹ምንም አልተገኘም ከተባለ ከዚህ እርሻ በሄክታር ከ70 ኩንታል በታች አይገኝም ብዬ አስባለሁ› ይላሉ ከሰባት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ማሳ ከፍተኛ የተባለውን በሄክታር 30 ኩንታል ብቻ  ማግኘታቸውን እያስታወሱ፡፡ አቶ መርጋ ሞዴል አርሶ አደር በመሆናቸው ሰልጥነው በተግባር ያገኙትን ለውጥ በመስመር ስለ መዝራትና ስለ ፀረ አረም መድሃኒት አጠቃቀምን ጨምሮ ልምዳቸውን በስራቸው ለታቀፉ ለሌሎች አርሶ አደር ማህበራት ማካፈል ጀምረዋል፤

ኢትዮጵያ ለቢራ ምርት የሚሆን ገብስ በበቂ ሁኔታ ማምረት ባለመቻሏ ለዓመታት ብቸኛ የነበሩት የአሰላ እና የጎንደር ብቅል ፋብሪካዎች ከውጭ ሀገር ገብስ በብዛት  ያስገቡ ነበር፤ ሃይንከን ኢትዮጵያ ይህንን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ከገብስ አምራች አርሶ አደሮች ጋር በነደፈውና ተግባራዊ ባደረግው የቢራ ገብስን በሀገር ውስጥ የመተካት ፕሮጀክት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የቢራ ገብስ ፍላጎቷን ከማሟላት አልፋ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት በሚያችል አቅም ላይ መድረሷ ተገልፃል፤ የብቅል ፋብሪካዎችም ከሁለት ወደ አራት አድገዋል፤

ሃይንከን ኢትዮጵያ ‹Going Local, Growing with Ethiopia› በሚል መርሕ በአርሲ፤ ባሌና ሸዋ የሚገኙ 70 ሺ ያህል በማህበር የተደራጁ ገብስ አምራች አርሶ አደሮችን በማቀፍ ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የሻሻሉ የገብስ ዝርያዎችና ምርጥ ዘር፤ ስልጠና፤ ፀረ አረም መድሃኒትና ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን  በማቅረብ በኢትዮጵያ የገብስ ፍላጎትን በማሟት እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2022  ብቻ የገብስ ምርትን ከ2.4 ቶን ወደ 4 ቶን ለማሳደግ ተችሏል፤ ይህንኑ ተከትሎም ለገብስ ግዢ ሊወጣ የነበረን 788 ሚሊዮን ዶላር ( 32 ቢሊዮን ብር) የውጭ ምንዛሪም ማስቀረት መቻሉን የሃይንከን ኢትዮጵያ የሰፕላይ ቼን ማናጀር አቶ አንተነህ ምትኩ ተናግረዋል፤

Heineken Award

ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት ሃይንከን ኢትዮጵያ ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆነውን ገብስ ከሀገር ውስጥ የሚያገኘው 25 ከመቶ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አንተነህ ከገብስ አምራች አርሶ አደሮች ጋር ተቀራርቦ መስራት በመቻሉ አሁን ላይ እስከ 80 ከመቶ የሚሆነው የፋብሪካውን ፍላጎት ከሀገር ውስጥ አምራች አርሶ አደሮች ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፤ በቀጣዮ የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያ ስንዴ ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብ መንግስት መግለፁን የጠቀሱት ሀላፊው የቢራ ገብስ ፍላጎትን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከሀገር ውስጥ ምርት በማሟላት ከውጭ ሀገር የሚገባውን ገብስ እናስቀራለን የሚል እቅድ ይዘናል ብለዋል፤

ሃይንከን በዓለም ዙሪያ በ70 ሀገራት ከ160 በላይ ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን በፋብሪካዎቹ  መሀከል በተካሄደ 200 በላይ  የምርጥ ተሞክሮ ውድድር የቢራ ገብስን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሂደቱ ውጤታማ በመሆኑ   ሃይንከን ኢትዮጵያ በቅርቡ በኣለም አቀፍ ደረጃ በአንደኝነት ተሸላሚ ሆኗል፤ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ሃይንከን ኢትዮጵያ ለዚህ ውጤት አስተዋረፅኦ ላደረጉ አርሶ አደሮች ፤ የግብርና ባለሙያዎች፤ለግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችና ግብዓት አቅራቢዎች  የእውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል፤

ሰሞኑን በአርሲ ዞን ዋና ከተማ አሰላ በተካሄደው የእውና መርሃ ግብር ላይ በሃይንክን ኢትዮጵያ አማካይነት በተሰጠ ስልጠናና ምርጥ ዘር እንዲሁም ማዳበሪያና ፀረ አረም መከላከያን በመጠቀም በሄክታር እስከ 70 ኩንታል ገብስ ያመረቱ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ሽልማትና እውቅና ተቀብለዋል፤

በዚህ የእውና መርሃ ግበር ላይ የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንተርፕራይዝ፤የቦሳ ኮኖፋ ማይክሮ ፋይናንስ፤የአርሲ ዞን አስተዳርና የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የገብስ ምርት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፤

Barley farm

በሃይንከን ኢትዮጵያ አማካይነት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በገብስ ምርት ለውጥ ማምጣት የተቻለው በአርሶ አደሮችና በግብርና ባለሙዎች ጥረት መሆኑን መነሻ በማድረግ ለእቅዱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ ወገኖች ልዩ ልዩ ሽልማቶችንና የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe