ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ትግራይ ክልል ዕርዳታ ጭነው ከሄዱ 1,317 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 1,010 አለመመለሳቸውን መንግስት ይፋ ቢያደርግም የተባባሩት መንገስታት ድርጅት ግን ተሸከርካሪዎቹ እንዲመለሱ በወራሪው ሃይል ላይ ተፅእኖ ከማሳረፍ ይልቅ አዳዲስ ተሸከርካሪዎችን ለመግዛዢያ የሚሆን ገንዘብ እያፈላላገ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፤
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተወካይ ካትሪን ሶሲ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ዕርዳታ ጭኖ ለመላክ ክልሉን እንመራለን ከሚሉ የሕወሓት ሰዎችና መቀሌ አካባቢ ከሚገኙ አካላት ጋር ተሽከርካሪዎች እንዲመለሱ ለመጠየቅና ለመስማማት የተሞከረ ቢሆንም፣ ውጤቱ በተፈለገው ልክ ባለመሆኑ ተመድ ለዜጎች ዕርዳታ መግዣ ገንዘብ በማፈላለግ ፋንታ፣ የዕርዳታ እህል የሚጭኑ ተሽከርካዎችን መግዣ ገንዘብ ለማፈላለግ ተገዷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ እንኳ ከኅዳር 14 እስከ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ተከታታይ አሥር ቀናት ብቻ ወደ ትግራይ ከስምንት ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ጭነቶችን ይዘው የሄዱ 203 ተሸከርካሪዎች፣ በተላኩ በሦስት ቀናት ውስጥ መመለስ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም አንድም የጭነት ተሽከርካሪ አለመመለሱን የኢትዮጵያ መንገስት አስታውቋል፡፡
ተሽከርካሪዎቻቸው በትግራይ ክልል ዕርዳታ ጭነው ከሄዱ በኋላ ያልተመለሱላቸው የተወሰኑ ባለንብረቶች ለትራንስፖርት ሚኒስቴር አቤት እያሉ ሲሆን ፣ ጉዳያቸው ካልተፈታ በቀጣይ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚሄዱ ተነግሯል፡፡
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ከመጣ ወዲህ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ማመላለስ የነበረባቸው ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ገብተው መመለስ ሲጠበቅባቸው ሕወሓት ለጦርነት የሚማግዳቸውን ወጣቶችና ወታደሮች ጭኖ ማመላለሻ ማድረጉን መንግስት ሲከስ ከርሟል፤
ከዚህ ባለፈም፣ የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራና አፋር ክልሎች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ዘረፋ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ በዝምታ ማለፉ የኢትዮጵያ መንገስትን ማሳዘኑ ተነግሯል፤
በሰሜኑ ጦርነት የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ከሚያደርሱት ዕርዳታ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው በጦር ቀጣና ውስጥ በመሆኑ የፀጥታው ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት እንደሆነባቸው፣ የሚናገሩት ዶ/ር ካትሪን በዚህም ላለፉት 12 ወራት 23 የረድኤት ሠራተኞች እንደተገደሉ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 20 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡

