ህወሓት ንብረትነቱ የመከላከያ ሰራዊት ባልሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተፈጽሞብኛል የሚለው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው – ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

ስግብግቡ የህወሃት ጁንታ ንብረትነቱ የመከላከያ ሰራዊት ባልሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተፈጽሞብኛል የሚለው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአየር ሀይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።

ሜጀር ጀኔራል ይልማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የኢፌዴሪ አየር ሀይል የሀገርን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ በሚያስችል ደረጃ ቴክኖሎጂ የታጠቀ መሆኑን አንስተዋል።

አየር ሀይሉ የሀገሪቱን አየር ክልል ከጥቃት በብቃት የመጠበቅ እና እንዳሁኑ ደግሞ የከረሩ ነገሮች ሲፈጠሩ ለሰራዊቱ የቅርብ ድጋፍ የማድረግ ተግባሩን እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።

የጠላት ኢላማዎችን ያለምንም ርህራሄ እንዳልነበር ማድረግ ለሰራዊቱ ማነቆ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በማፍረስ መንገዱን ቀና የማድረግ ተግባርም ይከውናልም ነው ያሉት፡፡

ሜጀር ጄኔራል ይልማ ከዚሁ ጋር በተያያዘ፥ ስግብግቡ የህወሓት ጁንታ ተቆጣጠርኩ ብሎት የነበረው መሳሪያ ክህደቱ ሳይሰማው ድንፋታውን በጎላበት ማግስት በአየር ሀይሉ ወደ አመድነት ተቀይሯል።

ኃላፊነት በማይሰማው ቡድን በዱር በገደሉ የኮንትሮባንድን መንገድ ተከትሎም ክልሉ የደረሰው የጦር መሳሪያ እጣ ፈንታም ቢሆን በአብዛኛው ተመሳሰይ እድል ገጥሞታል ብለዋል።

በመቐለ አቅራቢያ ክዊሃ እና አዲግራት ጭምር የነበሩ የነዳጅ ዴፖዎችም በጁንታው ቡድን ጥቅም ላይ ሳይውሉ መውደማቸውንም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን የተዋጣላት ሀገርንም ያኮራ ስራ እና እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፥ በዚህ ሁሉ ውስጥ ህገ ወጡ ቡድን የአየር ድብደባው ንጹሃንን እና የተለያዩ የእምነት ተቋማትን እንዲሁም የህዝብ መገልገያ ፕሮጀክቶችን ኢላማ ስለማድረጉ ክስ ያቀርባል።

የአየር ሀይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፥ ውንጀላው ከእውነት የራቀ መሆኑን እና ይህ የቡድኑ የኖረ የውሸት እና የውንብድና ትርክቶች መሆናቸውን አውስተዋል።

የጦር አውሮፕላን መትተን ጥለናል የሚለው የህገ ወጡ ቡድን ወሬም ቢሆን የበሬ ወለደ እንጂ የአቅም እና የመሳሪያ ሁኔታው አልፈቀደለትም ይላሉ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ።

የትግራይ ወንድም እና እህቶችን ህይወት እና ሀብት ባላስገበረ መልኩ የተለዩ ኢላማዎችን የማጥቃት እርምጃው እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

“ይህን ስናደርግ ደግሞ በራሳችን በገነባነው የቴክኖሎጂ ልክ እንጂ የማንንም እርዳታ እና ድጋፍ አንጠይቅም” ብለዋል ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ።

ስግብግቡ ቡድን ሀገር እና ህዝብ ማለት ለርሱ እሱን እስከጠቀመ ብቻ መሆኑን በቅርብ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ባወደመበት አይተናል ብለዋል።

ስለዚህ ዜጎች ይህን ቡድን ለመንቀል በሚደረገው ጥረት ተባባሪ ይሆኑ ዘንድም ጥሪ አቅርበዋል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe