በ97 ምርጫ ምክንያት ተጠሪነታቸው ለፌዴራል የተደረጉት የትራንስፖርት ቢሮዎች ለከተሞቹ ይመለሳሉ ተብሏል፤ ዝርዝር አለን፤
የቀድሞው ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ በአዲስ አበባ ከተሸነፈ በኋላ፣ አዲሱ ፓርላማ ከመግባቱ በፊት ካወጣቸው ሕጎች መሀከል አንዱ የትራንፖርት አዋጅ ሲሆን በዚህ አዋጅ ላይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የትራንፖርት ቢሮ ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግሥት ሆኖ፣ ራሳቸውን የቻሉ ቢሮዎች ሳይሆን ቅርንጫፍ እንዲሆኑ የሚያዝ ነበር፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በምርጫ 97 ምክንያት ተጠሪነታቸው ለፌዴራል የተደረጉት የትራንስፖርት ቢሮዎች ለከተሞቹ እንደሚመለሱ የሚደነግግ የመንገድ ትራንፖርት አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለፖርላማ መምራቱ ታውቋል፤፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሁን ያዘጋጀው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ፣በተመለከተ በሚኒስቴሩ የሕግ አማካሪ የሆኑትን አቶ አበጀ ማሞ ሪፖርተር ጋዜጣ ጠቅሶ እንደዘገበው አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በምርጫ 97 ማግስት የወጣውን ሕግ ሽሮ የከተማ አስተዳሮቹ ትራንስፖርት ቢሮዎች ራሳቸውን ችለው የከተማ አስተዳደሩ አንድ መዋቅር እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ትራንፖርት ቢሮ አሁንም የፌዴራሉ ቅርንጫፍ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ግን ሕጉ ሳይሻሻልም የራሱን ትራንስፖርት ቢሮ ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን የሚኒስቴሩ የሕግ አማካሪ አስረድተዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ሲፀድቅ ለአዲስ አበባ ትራንፖርት ቢሮ ሕጋዊ መሠረት ይሰጠዋል ተብሏል፡፡
ምክር ቤቱ የተወያየበት ረቂቅ አዋጅ ከተሽከርካሪ መለያ፣ መመርመርያና መመዝገቢያ አዋጅ ጋር በአባሪነት ተያይዞ ያለውን ሰንጠረዥ የሚሽር ተጨማሪ አንቀፆችን የያዘ ሲሆን የክልል መለያ በተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ላይ እንዲነሳ እንደሚደረግም ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል ተብሏል፤

