ሊዮኔል ሜሲ የዓለም ምርጥ ተጫዋችነት ሽልማትን ለ7ተኛ ጊዜ አሸነፈ

የ34 አመቱ ሜሲ ከአገሩ አርጀንቲና ጋር የመጀመሪያውን ዋንጫ ኮፓ አሜሪካን በማሸነፍ አሳክቷል።በ2021 ለባርሴሎና 28፣ ለፓሪስ ሴንት ዠርሜይን 4 እና ለብሔራዊ ቡድኑ 8 ጎሎችን በማስቆጠር የጎል መጠኑን 40 አድርሷል። የባየር ሙኒክ እና የፖላንድ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የሆነው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ ሁለተኛ ሆኗል።

የቼልሲ እና የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ጆርጊንሆ ሦስተኛ ሲባል የሪያል ማድሪዱ ፈረንሳዊ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ አራተኛ ሆነው አጠናቀዋል።በኮሮናቫይረስ ምክንያት የ2020 ሽልማት በአካል ባይካሄድም የዘንድሮውን የባሎንዶር ሽልማት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 180 ጋዜጠኞች በመራጭነት ተሳትፈዋል።

ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ (የአምስት ጊዜ የሽልማቱ አሸናፊ) በአውሮፓውያኑ ከ2008 ጀምሮ እስከ 2019 ሽልማቱን በየተራ መሰብሰብ ችለዋል።በአውሮፓውያኑ 2018 የክሮሺያው አማካይ ሉካ ሞድሪች ሽልማቱን በመሃል አንስቷል።ሜሲ መጀመሪያውኑም ሽልማቱን በማግኘት ቀዳሚ የነበረ ሲሆን ሰባተኛው ሽልማቱ በአውሮፓውያኑ የ2009፣ 2010፣ 2011፣ 2012፣ 2015 እና 2019 ድሎችን ተከትሎ የመጣ ነው።

በፓሪስ ቲያትር ዱ ቻቴሌት በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ “እዚህ በድጋሚ መገኘት በጣም አስደናቂ ነገር ነው” ብሏል።”ከሁለት ዓመት በፊት የመጨረሻው ሽልማቴ እንደሆነ አስቤ ነበር። ሰዎች መቼ ጫማ እንደምሰቅል ይጠይቁኝ ጀመር። አሁን ግን እዚህ ፓሪስ ስሆን በጣም ደስተኛም ነኝ።” ሲል ተናግሯል።

“በኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ምክንያት ለእኔ ዓመቱ ልዩ ነው። በፍጻሜው (ብራዚልን 1-0) በማራካና ስታዲየም ማሸነፍ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ከአርጀንቲናዊያን ጋር ድሉን በማክበሬ ደስ ብሎኛል” ብሏል።”በሕይወቴ ውስጥ ምርጡ ዓመት ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን ከአስቸጋሪ ጊዜያት እና ትችት በኋላ ከአርጀንቲና ጋር ዋንጫ ማንሳት ልዩ ነበር” ሲል ገልጿል።

ሜሲ ሁለተኛ ሆኖ ላጠናቀቀው ለ 33 ዓመቱ የፖላንድ አምበል ሌዋንዶውስኪ ልብ የሚያሞቁ ቃላትን ሰንዝሯል።”ከእሱ ጋር መነሳት ክብር እንደሆነ ለሮበርት ልነግረው ፈልጌ ነበር። ባለፈው ዓመት [ሽልማቱን] ማሸነፍ ይገባው ነበር” ሲል ሜሲ ተናግሯል።

ሌዋንዶውስኪ በ2021 በሁሉም ውድድሮች ለባየር ሙኒክ 53 ጎሎችን አስቆጥሯል። ሽልማቱ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት ይፋ የሆነውን አዲሱን የዓመቱ ምርጥ አጥቂነት ሽልማት አግኝቷል።ጣሊያን የዩሮ 2020 እንድታሸንፍ የረዳው የፓሪስ ሴንት ዠርሜኑ ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ዶናሩማ የያሺን ዋንጫን በምርጥ ግብ ጠባቂነት አንስቷል።

የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ቼልሲ የዓመቱ ምርጥ ክለብ ተብሎ ተመርጧል።የ19 አመቱ የባርሴሎና አማካይ ፔድሪ ከ21 ዓመት በታች ምርጥ ተጫዋች በመባል የኮፓ ዋንጫን አሸንፏል። ለባሎንዶር ሽልማት በእጩነት ከተመረጡት 30 ተጫዋቾች 14ቱ በፕሪሚየር ሊጉ ይጫወታሉ።

ቼልሲ በአምስት ተጫዋቾች ተወክሏል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ጆርጊንሆ በተጨማሪ ንጎሎ ካንቴ (5ኛ)፣ ሮሜሉ ሉካኩ (12ኛ)፣ ማሰን ማውንት (19ኛ) እና ሴሳር አዝፒልኩዌታ (29ኛ) ናቸው።የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸውን ተጫዋቾች አስመርቷል። ከኬቨን ደብሩይን (8ኛ)፣ ራሂም ስተርሊንግ (15ኛ)፣ሪያድ ማህሬዝ (20ኛ)፣ ፊል ፎደን (25ኛ) እና ሩበን ዲያስ (26ኛ) ናቸው።

ከማንቸስተር ዩናይትድ ሮናልዶ (6ኛ) እና ብሩኖ ፈርናንዴዝ (21ኛ) ሲሆኑ የሊቨርፑሉ መሀመድ ሳላህ (7ኛ) እና የቶተንሃሙ ሃሪ ኬን (23ኛ) ደረጃን ይዘዋል።

SourceBBC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe