“ልዩ ነዳጅ መኖሩን አልደረስንበትም” የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

ትናንት ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በትግራይ ክልል በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነዳጅ መኖሩ በጥናት መረጋጋጡን አስታውቃዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚገኘው ኬይ ፒ አር የተሰኘው የህንድ ኩባንያ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል በሚገኙ እምባ አላጀ፣ ነበለት እና ዓዲ ግራት ባሉት ተራራማ አካባቢዎች በዓይነቱ ልዩ የሆነው የነዳጅ ክምችት እንደሚገኝ መናገራቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በአውሮፓውያኑ 2018 ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲና ተቋማት የተውጣጡ የአጥኝዎች ቡድን ‘Economic geology value of oil shale deposits: Ethiopia Tigray and Jordan’ በሚል ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሁፋቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሼል ኦይል ክምችት እንደሚገኝ ፅፈዋል።

ከእነዚህ ቦታዎች አንዱ ትግራይ ክልል፤ ከፍተኛ የሆነ የሼል ኦይል ክምችት እንደሚገኝበትም በጥናታዊ ፅሁፉ ላይ ተመላክቷል።

በጥናቱ እንደተገለፀው ይህ የነዳጅ ዘይትም ብዙውን የክልሉን ቦታ የሚሸፍነውን – በአዲግራት አሸዋማ አለት ሥር በስፋት የተሰራጨ ነው። በመሆኑም ብዘት፣ ዕዳጋ ዓርቢ፣ ነበለት እና አጽቢ የሚባሉ አካባቢዎች መገኘቱንም ጥናቱ አትቷል።

በትግራይ ክልል ይገኛል የተባለው የነዳጅ ክምችትም ወደ 3.89 ቢሊየን ቶን የሚጠጋ እንደሆነ በጥናታቸው አመላክተዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኘው የኦይል ሼል ክምችትም ከ55-60 በመቶው የካርቦን ይዘት እንዳላቸው ጥናቱ በዝርዝር አስቀምጧል።

ጉዱዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው በኢፌዲሪ የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ ዶ/ር ቀጸላ ታደሰ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነዳጅ ዘይት ክምችት እንዳሉ የሚያመላክቱ ጥናቶች መኖራቸውን ያስታውሳሉ።

ነገር ግን አሁን በትግራይ ክልል ተገኘ የተባለው ሼል ኦይል ተገኘ ስለመባሉ “ይህ መግለጫ ተጨባጭና አስተማማኝ የሚሆነው የቁፋሮ ሥራና በቤተሙከራው ውጤቶች ተደግፎ ሲቀርብ ነው” ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት የተለያዩ የነዳጅ አይነቶች ያሉ ሲሆን ሼል ኦይል የአለት ዓይነቱ በተለያዩ ዘዴዎች በመሰነጣጠቅና ጋዝ እንዲያመነጭ በማድረግ የሚመረት የተፈጥሮ ጋዝ ነው ይላሉ።

የዚህ ዓይነት የተፈጥሮ ነዳጅም በሰሜን አሜሪካ በስፋት እንደሚጠቀሙበት ይጠቅሳሉ።

ይሁን እንጂ በአካባቢው የተለመደ ‘ሼል ሮክ’ አለት እንዳለ የሚናገሩት ባለሙያው አሁን በትግራይ ክልል ተገኘ የተባለው ‘ሼል ኦይል’ መሆኑን በጥናት እንዳልተደረሰበት ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህንንም ‘ሼል ኦይል’ ለማጥናት የመጣ ኩባንያ እንደሌለም አክለዋል።

የአጥኚዎች ቡድን ነዳጁ ስለመገኘቱ ብቻም ሳይሆን ትግራይ ውስጥ ያለው ክምችት ወደ 4 ቢሊዮን ቶን አካባቢ መሆኑን እንደሚጠቁም ያነሳንላቸው ዶ/ር ቀጸላ፤ የአጥኚዎች ቡድን ስለመኖሩ እንደማያውቁ በመግለፅ “አንደኛ በላብራቶሪ መደገፍ አለበት፤ የተካሄዱ ሥራዎችም የሉም፤ በመሆኑም በግምት እንዲህ ነው ማለት አይቻልም፤ በመሆኑም ተዓማኒነት እንዲኖረው መተመንና በማስረጃ መደገፍ አለበት” ሲሉ መልሰዋል።

“ባይጋነን ጥሩ ነው፤ ተጨባጭ ነገር ሲኖር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግልፅ የሆነ መግለጫ ይሰጣል፤ የሕዝብን ልብ ትርታ ለመጨመር ጥረት ባይደረግ ” ሲሉም ይመክራሉ።

ከዚህ ቀደምም በመቀሌ ተፋሰስ በተባለው አካባቢ የነዳጅ ክምችት መኖሩን የሚያውቁ ሲሆን ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ለተለያዩ ባለሃብቶች በማስተዋወቅ ጥናቶች እየተካሄዱ መቆየታቸውን ነግረውናል።

የነዳጅ ክምችቱ እንዳለ የታወቀውም በግምት የዛሬ ሃያ ወይም ሰላሳ ዓመት ገደማ ይሆነዋል ብለዋል። በእነዚህ ጊዜያትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በፍለጋው ላይ ለማፍሰስ የሚፈቅዱ ባለሃብቶችን ሲፈለግ እንደቆየ ያስረዳሉ።

በጥናቱም በአገሪቱ ካሉ ስድስት የነዳጅ መፈለግ የሚያስችል ተፋሰሶች አንዱ መቀሌ ተፋሰስ እንደሆነም አስታውሰዋል።

የመሥሪያ ቤቱ ዋና ሥራም ቢፈለግ ሊገኝበት እንደሚችል ማስተዋወቅና ማሳየት እንደሆነም አክለዋል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ አሁንም በጥናት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት ሰባ ዓመታት በአገሪቱ በተደረጉ የነዳጅ ፍለጋ ጥናቶችም አመርቂ የሆነ ውጤት የተገኘበት የኦጋዴኑ መሆኑን ይገልፃሉ።

ማንኛውንም የሥነ ምድር ሐብት የሚያጠናው ተቋም የኢትዮጵያ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ በጉዳዩ ላይ ጥናት ስለመኖሩ ጠይቀናቸው ነበር።

የተቋሙ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ መርሻ ከሰላሳ ዓመታት በፊት በተደረገው ጥናት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያለው የነዳጅ ክምችት እንደሚኖር ከሌሎች አገራት ኩባንያዎች ጋር በመሆን ጥናት ተካሂዶ እንደነበር ያስታውሳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ከሰላሳ ዓመት በፊት በተጠና ጥናት ከፍተኛ ክምችት የሚገኝበት የኦጋዴን ቤንዚን ፣ አባይ ሸለቆ፣ በስምጥ ሸለቆ (ከአፋር እስከ ደቡብ ኦሞ)፣ በጋምቤላ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በመቀሌ እና መተማ ተፋሰስ የተለያየ መጠን ያለው የነዳጅ ክምችት መኖሩን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

መሥሪያ ቤቱ የመንግሥት ፖሊሲ ከመቀየሩ ጋር ተያይዞ የሕዝቡን ፍላጎት የሚያሟሉና የሕዝቡን ችግር የሚፈቱ ሌሎች ማዕድኖች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደጀመረ በመግለፅ አሁን ይፋ የተደረገው የነዳጅ ዓይነት ጥናት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ምንጭ፡ ቢቢሲ

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe