ሐሰተኛ ዲግሪዎች መዘዝ

 ‹ የትምህርት ማስረጃን በተመለከተ ሀገሩ የደላላ ሆኗል፤› ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ከዓመታት በፊት ራሱን ‹ዶክተር ኢንጂነር› ሲል የሰየመው አቶ ሳሙኤል ዘ ሚካኤል የተባለ ግለሰብ በየትኛውም የዩኒቨርሲቲ ተቋም ገብቶ ሳይማር የዲግሪዎች መአት ለራሱ ሰጥቶ በየመድረኩ በዚሁ ስም ሲጠራና ሰዎችን ሲያሳስት እንደነበር እናስታውሳለን፤

አቶ ሳሙኤልን ክስተት ልዩ ያደረገው ግለሰቡ ለራሱ የሰጠውን ዲግሪ ‹እናንተ ጋር ተምሬ ነው በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቄ ያገኘሁት› በማለት ራሳቸውን ዩኒቪርሲቲዎቹን  ስልጠና ልስጣችሁ እያለ ሲያጃጅላቸው ወደ መዝገብ ቤታቸው ጎራ ብለው ግለሰቡ መቼ እንደገባ? ምን ትምህርት እንደተማረና መቼ እንዳጠናቀቀ? የሚገልፀውን ማስረጃ ከመፈለግ ይልቅ ቀላል የማይባል የስልጠና በጀት በጅተውለት የዩኒቨረሲቲውን ማህበረሰብ ‘ ሲያሰለጥንላቸው ’ መታየቱ ነገሩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድረጎት ሰንብቷል፤

 አቶ ሳሙኤል ይህ ድርጊቱ ሲነቃበት በኬኒያ በኩል አድርጎ ከሀገ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም በፖሊስ ተይዞ ወደ ሀገር ቤት በመግባት በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ የሶስት ዓመታት እስሩን አጠናቆ ወጥቷል፤

አሁንም በተመሳሳይ የሐሰተኛ ዲግሪዎች በየመንግስት መስሪያ ቤቱ ከመቀጠርም አልፈው የመንግስት ከፍተኛ ስልጣንን የያዙ ግለሰቦች ስለመኖራቸው በሰፊው ይነገራል፤  የሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት አልያም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አይነት የትምህርት ተቋማት ምላሽ ባይሰጡም የሀሰተኛ ዲፕሎማና ዲግሪ ችግር ከተራ የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጣሪ አልፎ ቤተመንግስት ድረስ ስለመግባቱ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፤

በቅርቡም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የዶክተሬት ዲግሪን ሊያሰርዝ የሚችል በቂ የጥናት “ስርቆት” ማስረጃ ማግኘቱን የዓለም ሰላም ፋውንዴሽን አስታውቋል፡፡ ፋውንዴሽኑ ከዚህ በፊት ጥያቄ ሲነሳበት የነበረውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የዶክተሬት ድግሪ ላይ ሰፊ ማጣራት በማድረግ ያገኘው ማስረጃ ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥናት እንደገና ሊመረምር የሚችልበት በቂ ማስረጃ ማግኘቱን ጠቁሟል፡፡

ተቋሙ የዶክትሬት ዲግሪውን ለማገድ ወይም ለመሻር በቂ ነው ያለውን ማስረጃ ሲያቀርብ፤ በሌሎች ጥናቶች ላይ የተጠቀሱ ጽሑፎች በቀጥታና በጥቂት ማሻሻያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥናት ላይ ተደግመው መገኘታቸው በማስረጃ አስደግፎ አብራርቷል፡፡

በዚህም ዩኒቨርስቲው ፕላጂያሪዝምን ወይም የሰው ጥናት ስርቆትን በሚከለክለው አሰራር እንደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን መሰረዝ እንደሚል ተጠቁሟል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ እንደ አማራጭ የተጠቆመው፤ ጥናቱ እንደገና ተሻሽሎ ድጋሚ እንዲሰራ በማድረግ እሰከዚያው የዶክተሬት ዲግሪ ማገድ  ነመሆኑን እንደ አማራጭ ይፋ አድርጓል፤ በጉዳዩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የሰጠው ማረጋገጫ ወይም ማስተባባያ የለም፡፡

ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ9 ወራት የስራ እቅድ አፈጻፀሙን ያቀረበው ትምህርት ሚኒስቴር ግን  “ከቀረቡልኝ የማስረጃ ይረጋገጥልን ጥያቄ 40 በመቶ የትምህርት ማስረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ” ብሏል፤

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 18 ሽህ የትምህር ማስረጃዎች ትክክለኛ ተፈትሾ 921 (አምስት በመቶዎቹ) ህገ-ወጥ ሆነው እንዳገኛቸው ሚንስቴሩ ጨምሮ አስታውቋ

Minstry of Education

ቀጣሪ ተቋማት ለሚንስቴሩ ይረጋገጥልን ብለው ባቀረቡት ጥያቄ ደግሞ 225 የትምህርት ማስረጃዎች ደግሞ ተመርምረው 40 በመቶዎቹ ሀሰተኛ ሆነው ተግኝተዋል።

ትምህርት ሚንስቴር የዘጠኝ ወር ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፥ አባላቱ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በስፋት መሰራጨት እንዳሳሰበው ተናግረዋል።

ገዙ ምናዬ የተባሉ የምክር ቤት አባል “በአንዳንድ የግል የትምህርት ተቋማት የሚወጡ የሀሰት የትምህርት ማስረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ ስለሆነና ይህም በሀገር አሉታዊ ጫና ስላለው እነዚህን ተቋማት እውቅና ከማሳጣት አንፃር ምን እየተሰራ ይገኛል?” ሲሉ ጠይቀዋል።

የትምህርት ማስረጃ ማጣራትን ከራሳችን ጀምረናል ያሉት የትምህርት ሚንስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፥ በዚህ ዓመት ሁሉም የፌደራል ተቋማት ሰራተኞች ማስረጃ እንደሚጣራ ገልጸዋል።

“በሁሉም የፌደራል ተቋማት የሰራተኞችን ማህደር መመርመር ጀምረና፤ ምን ያህሉ እውነተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዞ ነው? ምን ያህሉ አይደለም የሚል ምርመራ እያካሄድን ነው፥ ከራሳችን ጀምረን። ማህበረሰቡ ልክ እንደፈተናው (የ12ተኛ ክፍል ፈተና) እንዲያውቅልን የምንፈልገው ከአሁን በኋላ በተጭበረበረ ድግሪ፣ በተጭበረበረ ዲፕሎማ የሚሰራ ስራ አይኖርም የሚለውን ለማሳወቅ ነዉ። በዚህ ዓመት እሱን እንጨርሳለን ብለን እናስባለን” ብለዋል።

ይህን ለማድረግ ችግሩን ያልደበቁት ሚንስትሩ “ችግሩ ግን የሚታወቅ ነው፥ ሀገሩ የደላላ ሆኗል፤ ቀጥተኛ የሆነ የግብይት ስርዓትና ንፁህ የሆነ ስራን ለመስራት በጣም ብዙ ስራ ይቀረናል” በማለት መናገራቸው ተዘግቧል።

በ2015 ዓመት የሁሉም የፊደራል ተቋማት ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት እንደሚረጋገጥ ሚንስትሩ አስታውቋል።

ችግሩ ስር የሰደደና ከትምህርት ጥራት ጋር የሚያይዙት ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከታች ጀምሮ በአግባቡ ተኮትኩቶ ጥራት ባለው ትምህርት ያልተገራ ተማሪ በአቋራጭ ዩኒቨርሲቲ ቢገባም በአግባቡ ተምሮ ማጠናቀቅ ስለሚያቅተው ሐሰተኛ ዲግሪ ገዝቶ ወደ ስራ ዓለም እንደሚሰማራ ፀሐይ የሚቀው ሀቅ ነው፡፡ ይህንን ችግር ከስረ መሠረቱ ለመፍታት ይመስላል ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከኩረጃ ነፃ በሆነ መልኩ አከናውናለሁ ብሎ ስርዓት የዘረጋው፤ በ2014ለ2015 ዓ ም በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከተፈተኑት 908,520 ተማሪዎች ውስጥ 29909(3.3%) ብቻ የማለፊያ ነጥብ ማምጣታቸው ሲታይ ከየዩኒቨረሲቲው ተመረቅሁ እያሉ ዲግሪና ዲፕሎማ የያዙ ሰዎች ሰነድ ምን ያህል ችግር እንዳለበት ለመገመት አያስቸግርም፤

ለመሆኑ በ2014ለ2015 ዓ ም በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከተፈተኑት 908,520 ተማሪዎች ውስጥ 29909(3.3%) ብቻ የማለፊያ ነጥብ ያመጡበት መነሻ ምክንያቱ ምንድን ነው? አለሙ ፋንታሁን የተባሉ መምህር ይህንን ትውልድ የዚህ አይነት ስብራት ላይ የጣለውን መነሻ ምክንያቱ በዝርዝር ያስረዳሉ፤

1. የትምህርት ስርዓቱ በፓለቲካ አመራሮች የሚመራና ከ8ኛ ወደ 9ኛ ክፍል እንዲያልፍ የማለፊያ ነጥብ የሚወሰነው የትምህርትን ስነ ባህሪ በማያውቅ ከገጠር በተሰባሰቡ የምክር ቤት አባላት ወይም በፓለቲካ አመራሮች መሆኑ።እንዲሁም አንዳንድ በትምህርት ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለመሙላት ሲፈለግ የፓለቲካ አመራሮች ካልፈቀዱ በስተቀር የማይፈፀም መሆኑ።

2. ጆሮውን ወይም አይኑን መለየት ከቻለ ከክፍል ክፍል አሳልፉት የሚል በበላይ አመራሮች ጫና መደረጉ።

3. በሴሚስተሩ መጨረሻ በወረዳ፣በዞን እና በክልል ደረጃ የተማሪ ማለፍና መደገም ላይ ተመስርተው የትምህርት አመራሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ግምገማ ማካሄድ፤ በተለይ ብዙ ተማሪ የደገመበት ትምህርት ቤት ያለ ር/መ/ር እስከ አባርርሃለሁ የሚል ዛቻ መደረጉና ለቀጣይ በውሸትም ቢሆን የተማሪዎች ውጤት እየሞሉ እንዲያሳልፉ ጫና መፍጠር፣የአቋራጭ ተማሪዎች ቁጥር እንዳይበዛ በሚል ያልተማሩ ተማሪዎች ውጤት እንዲሟላላቸው መደረጉ።

4. ካለው የኢኮኖሚ ድሽቀት አኳያ መምህርነት በማህበረሰቡ ዘንድ የተናቀ መሆኑንና ምንም ፋይዳ የሌለው ሆኖ መቆጠር፣ ክብሩ ዝቅ ያለ በመሆኑና ተማሪዎች በትምህርት ላይ ያላቸው የተነሳሸነት ስሜት በመቀነስ ወደ ትምህርት ቤት አዘውትሮ አለመምጣትና የሚጠበቅባቸውን እውቀት አለመጨበጥ።

5. የሰለጠነ የሰው ሀይል በወቅቱ ባለመመደብና አንድ መምህር በአንድ ትምህርት በጀት ዓመት የሚመዝናቸው የተማሪ ቁጥር ከፍተኛ መሆን።

6. መምህሩ ከስራው ጫናና ልፋት አኳያ በቂ ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም ባለማግኘቱ ምከንያት በተጓዳኝ ስራ በመጠመዱ በሙሉ ስሜትና ተነሳሽነት ወደ መደበኛ ስራው አለመግባቱ፣የሚመዝናቸውን ተማሪውች እኔ ምን አገባኝ በሚል ስሜት በግምት አሰስመንት መተግበርና ተማሪዎች በቂ እውቀት ሳይጨብጡ ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ እንዲያልፉ ማድረጉ፣በክፍል ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎች ከጉረጃ ያልፀዳ መሆኑ። ምዘና ያለፋቸውን ተማሪዎች ያለምንም በቂ ምክንያት ላለመጠይቅ ሲባል ተማሪዎችን” ፈልጎ”ና ለምኖ ማሰራት ወይም መፈተን፣ከዚህ ተግባር ተነስተው ተማሪዎች መምህሩን <ስትፈልግ ለምነህ ፣ፈልገህ ትፈተነኛለህ ወይም ትሞላልኛለህ› የሚል ልምድ ማዳበራቸው።

7. ለመማር ማስተማር ተግባር የሚያገለግሉ ግባቶች ለምሳሌ፣የተማሪ መማሪያ መፅሃፍ፣አጋዥ መፅሀፍ ፣ የቤተ_መፅሃፍ ምቹነት፣የመብራት አገልግሎት፣የቤተ_ሙከራ ኬሚካሎችና አፓራተሶች እንዲሁም በሙያው የሠለጠነ የቤተ-ሙከራ ባለሙያ አለመሟላቱ።

8. በየወቅቱ የስራ ላይ ስልጠና ለመምህራን አለመሰጠቱ።

9. ማህበረሰቡ ወይም የተማሪ ወላጆች በትምህርት ላይ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑ፤ ልጁን አዘወትሮ ወደ ትምህርት ከመላክ ይልቅ አዘወትሮ በማስቅረት የጉልበት ስራ እንዲያግዟቸው ጫና መፍጠር፣አልፎ አልፎም ትዳር እንዲይዙ ጫና መፍጠር።

10. ተማሪዎች መምህራንን አለማክበር እንዲሁም አለመፍራት በመሆኑም ከማንጓጠጥ በዘለለ የተሰጣቸውን ተግባራት በትኩረት አለመስራት፤የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ በወቅቱና በስርዓቱ አለመፈፀም ።

11. የወረዳ፣የዞን፣የክልል እና የፌደራል የትምህርት ባለድርሻ አካላት የትምህርት ተቋማት ያሉበትን የትምህርት እንቅስቃሴ በወቅቱ በመፈተሽ ፈጣን መፍትሄ አለመስጠት።

12. ሌሎች የመንግስት ሴክተሮች ትምህርት የመምህሩ ተግባር ብቻ ነው ብለው በማሰብ ጥሩ ወጤት እንዲመዘገብ እገዛ እና ትብብር አለማድረግ።አልፎ አልፎም የትምህርትን ተግባር በማንቋሸሸ ለማህበረሰቡ ማድርስ።

13. የመንግስትና የህዝብ የወይይት ኮንፈረንሶች ሲካሄድ የትምህርት ጉዳይ በመጨረሻ ከ”አጀንዳነት”ም ወርዶ በማሳሰቢያ ላይ የሚቀርብ ጉዳይ መሆኑ።

14. 2012 ለ2013 ዓ ም በኮረና ምክንያት ተማሪዎች በነበሩበት የክፍል ደረጃ በቂ እውቀትና ክህሎት ሳይጨብጡ ነፃ ዝውውር መፈቀዱ ለ2014/2015 ዓ ም ለፈተና ወድቀት መንስኤ መሆኑ።

15. በየደረጃው የተጠያቂነት ስርዓት አለመኖሩ ቢኖርም አለመተግበሩ።በአብዛኛው የተጠያቂነትን ስርዓት ለመተግበር የሚሞከረው ትምህርት ቤት ውስጥ ባሉ አካላት ብቻ ነው።

16. ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት በትምህርት ላይ የሚሰራቸው ስራዎች ስራው ለእኔ ለራሴ ነው ብሎ በሙሉ ስሜት አለመተግበሩ።

17. ከሌሎች የትምህርት አመታት በተለየ መልኩ ዘንድሮ አብዛኛው ተማሪ የማለፊያ ነጥብ ያላመጡበት ምክንያት

ሀ. መቀዳዳት አለመቻላቸው?

ለ. 12ኛ ክፍል የሚያደርስ እውቀት፣ክህሎትና አመለካክት አለማዳበራቸው?

ሐ. ከዚህ በፊት በተለየ መልኩ ከ9_12 ክፍል የ4 የክፍል ደረጃ መፈተናቸው?

መ. በክፋል ውስጥ በሚተገበሩ የምዘናው አተገባብር ችግር 12ኛ ክፍል መድረስ የማይችሉ ተማሪዎች በገፍ 12ኛ ክፍል መድረሳቸው?

ሠ.ተማሪዎች የተፈተኑበት ቦታ ከለመዱት አካባቢ የራቀ በመሆኑ የስሜት መረበሽ?

ረ. በአንዳንድ የፈተና ቦታውች የፓለቲካ ተለዕኮ በያዙ አካላት(መከላከያ፣ፈታኝና ተማሪ) የተፈጠሩ እረብሻዎች ተማሪዎች በጥሩ ስሜት ተረጋግተው መፈተን አለመቻላቸው?

 ምክንያቱ ምንድን ነው የሚለውን ትምህር ሚኒስቴር አሁንም በያዘው አቋም ከመፅናቱ በፊት ጥናት ማድረግና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይገባል፤ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በዓለም ላይ ሀሰተኛ  ዲግሪ የይረጋገጥልኝ ጥያቄ የሚያቀርቡት መስሪያ ቤቶች  ከስምንቱ ሁለቱ ብቻ ናቸው፤

ይህንን ሁሉ ሂደት አልፈው ዩኒቨርሲቲ ሳይገቡ ወይም አቋርጠው ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ አለኝ የሚሉ ግለሰቦችን ዩኒቨርሲቲዎች ማስረጃቸውን የሚያመክኑበት የተለያዩ መንገዶች ይጠቀማሉ፤ አንዳንዶቹ ከቀጣሪ መስሪያ ቤቶች ጋር ጥብቅ የሰራ ግንኙነት በመፍጠር ተቀጣሪ ሰራተኞች ያቀረቧቸውን የትምህርት ማስረጃዎች አስቀድመው ያረጋግጣሉ፤ ሌሎች ደግሞ ግልፅና ቀላል የጥቆማ መቀበያ ዘዴ በመፍጠር ሀሰተኛ ዲግሪ እንዳለ ያወቀ ማንኛውም ግለሰብ እንዲጠቁምና ዲግሪው እንዲጣራ ሊያደረግ ይችላል፤ ለጠቋሚዎችም ተገቢ የሆነ ወሮታ በመመደብ፤እንደአስፈላጊነቱ በየመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ ሰዎችን ቃለ ምልልስን በመከታተልም ግለሰቦች የሚሰጧቸው አስተያየቶች ተማርን ካሏቸው የትምህርት አይነት ጋር አብሮ መሄድ አለመሄዱን፤ እንዲሁም ያዝነው ከሚሉት የትምህርት ደረጃ ጋር የማይሄድ መሆኑን በመከታተል የትምህርት ማስረጃውን ማጣራት ውስጥ ሊገባ ይችላል፤ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች  ደግሞ ዲግሪና ዲፕሎማ በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጡ ሳይቀር በየድረገጾቻቸው ጭምር የሚያስተዋውቁ በመሆኑ በተለይ በተልእኮና ኦፕን ከሚባሉ ዪኒቨርሲቲዎች የሚመጡ ዲግሪዎችን በጥንቃቄ መመልክት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይመክራሉ፤

በሀገራችን የትኛን መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር  እንዳቀደ ይፋ ባያደርግም በተያዘው ኣመት የመንግስት ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ  እንደሚጣራ ይፋ አድርጓል፡፡ ነፃ ገለልተኛና ፍትሃዊ ውሳኔ የሚያስፈልገው ይህ የማጣራት ሂደት ሙያተኛውን ባሳተፈና የተገኘውን ውጤትም ለህዝብ ይፋ ማድረግን ሊያካትት ይገባል፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe