ሕወሓትንና ሻዕቢያን ለማስታረቅ ጥረት ተጀመረ

የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኤርትራ ገዥ ፓርቲ ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራን (ሻዕቢያ) ማስታረቅ የተጀመረውን ሰላም ዘላቂ ያደርገዋል በሚል ዕሳቤ፣ ሴሊብሪቲ ኢቨንትስ የተባለ ተቋም የማስታረቅ ጥረት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የሁለቱን ፓርቲዎች ዕርቅ ‹‹ዳስ ዕርቂ አሕዋት ወድባት›› ወይም የሁለቱ እህትማማች ፓርቲዎች የዕርቅ ዳስ በሚል መሪ ቃል ዕውን ለማድረግ ጥናት ተጠንቶ ለትግበራ በዝግጅት ላይ መሆኑን የገለጹት፣ የሴሌብሪቲ ኢቨንስት ዋና ሥራ አስፈጻሚና መሥራች ወንድማማቾች አቶ አብርሃም ገብረ ሊባኖስና አቶ ሀብቶም ገብረ ሊባኖስ ዓርብ ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐርመኒ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት፣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተባባሪነት በመጣው ሰላም ትልቅ ዕድል መፈጠሩንና ለዚህም መሪዎቹን እንደሚያመሠግኑ የገለጹት አዘጋጆቹ፣ ይኼ ዕርቅ ግን ከላይ ተንጠልጥሎ ቀረ እንጂ መሬት አልወረደም ብለዋል፡፡ ይኼም የሆነው በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ባለው አለመተማመን፣ መጣላለፍና መጠራጠር ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም መደምደሚያ የሚረዳ ጥናት በኤርትራና በትግራይ ክልል የተደረገ መሆኑን፣ በኤርትራ የተደረገው የመረጃ መሰብሰብና ማጠናቀር ተግባር ከሁለት ወራት በላይ እንደፈጀ ተነግሯል፡፡ ጥናቱን ያከናወኑት ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደሆኑ የገለጹት የሴሌብሪቲ ባለቤቶች፣ የጥናቱ ውጤት ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይፋ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ይኼ ጥናት በዋናነት ያመለከተው የተፈጠረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ፣ የሁለቱ ፓርቲዎች ዕርቅ መምጣት እንዳለበትና መተማመን መፈጠር ይገባዋል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ለዚህ ጥረት የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን፣ ሕወሓት ግማሽ መንገድ ድረስ ሄዶ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኝነቱን እንደገለጸ አስረድተዋል፡፡ ለኤርትራው ገዥ ፓርቲ የቀረበው ጥያቄም ተቀባይነት አግኝቶ ይፋዊ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ለጥናቱና ለተለያዩ ወጪዎች መሸፈኛ ከሴሌብሪቲ ኢቨንስት ተጓዳኝ የንግድ ዘርፎች (ለምሳሌ ሎጅ) እንደሚሸፈን የገለጹት ባለቤቶቹ፣ ከታዋቂው ነጋዴና ባለሀብት አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኙም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ በመቀሌና በአስመራ የምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe