መሠረት ‹የህፃናት ልብ ህሙማን› መብራት

መሠረት ማራኪ መልክና ቁመና ያላት ከሰዎች ጋር ተግባባና ተጫዋች የሆነች የጥበብ ፈርጥ ናት፤የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችብት ወቅት እንደሷ ያለ  ልቅም ያለ ቆንጆ የለም› የምትባል የእድሜ እኩዮቿ አይን ማረፊና ስለነበረች በቁንጅና ውድድር ላይ ሁሉ እንድትካፈል ይወተውቷል ነበር፤ መሰረት ግን እግዚአብሔር በፈጠረው መልክና ቁመና ብዙም የምትመካ አልነበረችምና መድረክ ላይ ሳትወጣ  ቀርታለች፤ የጥላሁን ገሠሠ ጭልጥ ያለች አድረናቀ የሆነቸው መሠረት ከምግብ ክትፎ ፤ከመጠጥ ውሃ አዘውታሪ ናት፤ድብርት ሲሰማት  ብቻዋን ከራሷ ጋር እያወራች ረዥም መንገድ ወክ ማድረግ ያስደስታታል፤ ለቤት እንስሳት የተለየ ፍቅር አላት፤

መሠረት መብራቴ  በኢትዮጵያ የፊልምና የቴአትር  ጥበብ ውስጥ የገነነ ስም ካላቸው አርቲስቶች መሀከል የምትመደብ ናት፤ መሠረት ስሟ እየገነነ የመጣው በትወና ችሎታዋ፤ በትህትናዋ፤ በስነ ምግባሯና ለሰዎች በተለይም ለህጻናት ባላት ርህራሔ ነው፤ ከሀገራችን የቴአትርና የድራማ ተመልካቸች ጋር የተዋወቀችው ገና የ16 ዓመት ወጣት እያለች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ በነበረው ‹የሻማ እምባ› በተሰኘው ድራማ ነው፤ እንደዛሬው በርካታ የቴሌቪዥን አማራጮች ባልነበሩበት ወቅት መሠረት የወከለቻት ገፀ ባህሪ እንደ ሻማ ስታነባ ብዙዎች አብረዋት ያነቡ ነበር፤

መሠረትን በተከለያዩ ጊዜያት ከተወነችባቸው ፊልሞችና ቴአትሮች ሌላ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ተመልካቾች ቤት ውስጥ ሰተት ብላ እንድትገባና ቤተሰብ እንድትሆን ያስቻላት ሌላው የቴሌቪዥን ድራማ ገመና ነው፤ ከአንጋፋው የቴአትር ፈርጥ ፈቃዱ ተክለማርያም ጋር በጥምረት በመሪ ገፀባህሪነት የተወነችበት ገመና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በተለየ ቅርፅ የመጣና ከደላላ ወስደን ስለምንቀጥራቸው የቤት ሰራተኞች ጉዳይ አጥብቀን እንድናስብ በር የከፈተች በጥናትና ምርምር ስነ ዘዴ ላይም አዲስ እይታን ያስተዋወቀች ገፀባህሪ ሆኖ ተውናለች፤

በዚሁ ድራማዋ የትውና ብቃቷ ሳቢያም በድራማው ማጠናቀቂያ ማግስት በሸራተን ሆቴል በተዘጋጀ የሽልማት ፕሮግራም ላይ መሠረት በህዝብ ምርጫ የ20 ግራም ወርቅና የ50 ሺ ብር ተሸላሚ ነበረች፤

መሠረት ብዙ አርቲስቶች ለሽልማት መድረክ ላይ ሲወጡ ሊከውኑት የማይሆንላቸው ልዩ የንግግር ብቃት ያላት አርቲስት መሆኗን የገመና ሽልማት ዕለት በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ባደረገች ንግግር አሳይታለች፤ ስሟ ተጠርቶ ወደ መድረኩ የወጣችው በፍጹም ራስ መተማመን ነበር፤ ብዙ አርቲስቶች በተመሳሳይ ሽልማት መድረኮች ላይ የደስታ ስሜቱ በሚፈጥረው መረበሽ ግራ ሲጋቡ ይታያል፤ መሠረት ግን ለሌሎች አርኣያ ሊሆን በሚችል በራስ መተማመንና ጥንካሬ ብቃቷን አሳይታለች፤ሽልማቷን ከተቀበለች በኋላም ህዝቡ ለሰጣት  ፍቅር አክብሮትና ማበረታቻ ሁሉ አመስግና ክብርን ሁሉ የሰጠችው ለአምላኳ ነበር፤‹ሁሉን ያከናወነ የረዳኝን ልዑል እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በምልጃ ያተለየችኝ ቅድስት ድንግል ማርያም እመቤቴን አመሰግናለሁ› በማለት፡፡

በክርስቲያናዊ ቤተሰብ በግብረ ገብና በስነ ስርዓት ተኮትኩታ ያደገችው መሠረት በንግግሯ ውስጥ ትህትና ነግሶ ይታያል፤ አንድ ወንድምና በሁለት እህቶቿ መሀል ያደገችው መሠረት በልጅነቷ በቅዱስ ገብርኤል የሰንብት ትምህረት ቤት ውስጥ ተሳታፊ ነበረች፤ አሁንም ቢሆን ምራቅ ከዋጠች በኋላም ከቤተክርስቲያን ደጅ የምትጠፋ አይደለችም፤የማስቀደሻ ጧፍ፤ ሜሮንና ግምጃ ያጡ የገጠር አድባራትንና ገደማትን ለመደገፍ በሚካሄዱ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ ነጠላዋን ተከናንባ ወዲያ ወዲህ ማለት ልማዷ ነው፤

መሠረት ‹የህፃናት ልብ ህሙማን› መብራት(ቴ)

‹የምትመለከቱት ህፃን  ስሙ ሳምሶን ይባላል። ከተወለደ ጀምሮ የልብ ህመም ታማሚ ነው። በተጨማሪም የሳንባ ግፊት ችግር ስላለበት ለህይወቱ እጅግ አስጊ ስላደረገው በአስቸኳይ የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረግ እንዳለበት በሀኪሞች ስለተወሰነ ከሚያስፈልገው ጠቅላላ ወጪ 320,000 ብር ገደማ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪውን ገንዘብ እናንተ ደጋግ ኢትዮጵያውያን አሟልታችሁ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ይህን ታዳጊ ልቡን ትጠግኑለት ዘንድ በፍቅር እማፀናለሁ›

ይህ መልዕክት መሠረት መብራቴ በኦፊሻል የፌስ ቡክ ገፃ ላይ የፃፈችው ከወራት በፊት ነው፤ የህዝብ ፍቅር የታደለችው መሠረት ለህፃናት የልብ ህሙማን በምታሳየው ርህራሄ ብዙ ተከታይ ማፍራት ችላለች፤ ይህንን የህዝብ አክብሮትና ፍቅር ለበጎ ዓላማ ከሚጠቀሙ አርቲስቶች መሀከል አንዷ የሆነው መሠረት ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ የተወለዱ ህጻናትን ህይወት ለመቀጠል የወገኖቿን ድጋፍና እርዳታ በመሻት በምታደርጋቸው ጥሪዎች በጎ መላሽ በማግኘት የህጻናቱን እስትንፋስ በፈጣሪ ፈቃድ  በተደጋጋሚ አስቀጥላለች፤

እንደ ህፃን ሳምሶን ሁሉ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ6ሺ የማያንሱ ህፃናት በቀዶ ጥገና ሊድን በሚችል የልብ ህመም ይሰቃያሉ፤ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ከሆነ የልብ ህሙማን የሆኑ ህፃናት ወደ ህክምና ማዕከል ከመጡና ህክምናውን ካገኙ ከ98 ከመቶ  የሚሆኑት ይድናሉ፤ ግን ህክምናው ቦታ መድረስና ወጪውን መሸፈን የብዙ ወላጆች ራስ ምታት ነው፤ በመሆኑም የህክምና እርዳታውን ሳያገኙ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ህፃናት ወደዚያኛው ዓለም ይሰናበረታሉ፤ ይህ የዕለት ተዕለት ክስተት መሠረት መብራቴን እረፍት ከነሷት ከራርሟል፤ ‹ምን ላደርግ እችላለሁ› ብላ የተነሳቸው አርቲስቷ ያላትን ስም ዝናና የህዝብ ፍቅር የህጻናቱን ልብ ለመጠገን ለማዋል በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማህበር በኩል የዛሬ አራት ዓመት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆና እንድትሰራ ጥያቄው ሲቀርብላት ጥያቄው እንዲደገምላት አልጠበቀችም፤ እርግጥ ከዚያ በፊት በሴቶችና በህፃናት፤ በኤችአይቪና በፌስቱላ እንዲሁም በጎዳና ወጣቶች ፀረ ሱስ  ዘመቻ ዙሪያ ከሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት ጋር ሆና የበኩሏን አስተዋፅኦ አበርክታለች፤ የዓመታት በፊትም የሜሪጆይ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆና አገልግላለች፤

መሠረት ከኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል ጋር ያላት ትውውቅ ‹አንድ ብር ለአንድ ልብ!› ከተሰኘው ከረዥም ዓመታት በፊት ሲካሄድ ከነበረው የግንዛቤ መፍጠሪያና ገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ጋር የተያያዘ ነው፤ በወቅቱ የህፃናትን ልብ ለመጠገን እና ቋሚ የሆነ ሆስፒታል ለመገንባት እንቅስቃሴ በእነ ዶ/ር በላይ አበጋዝ ሲካሄድ መሠረት የሀሳቡ ደጋፊ ብቻ ሳትሆን በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ ውስጥም ተሳታፊ ነበረች፤ ይህን የሚያሳዩ የመሠረት የልጅነት ፎቶግራፎች አሁንም ድረስ በማዕከሉ ማህደር ውስጥ ተጠርዘው ይገኛሉ፤

መሠረት ከልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት ሚና እንድትጫወትና የተሰበሩ የልሀጻናት ልብን በመጠገን ሂደት ውስጥ የበኩሏ አሻራ እንድታኖር ጥያቄው ሲቀርብላት ማገልገል የህይወት ጥሪዋ ስለነበር አይኗን አላሸችም፤ ‹ማገልገል ፍፅም ደስታ የማገኝበት የህይወት ተልዕኮ ነው› ብላ ስለምታምን በቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ህይወቷም ለሰዎች የመድረስ ጥሪዋን ተግባራዊ ለማድረግ አጋጣሚውን ተጠቅማበታለች፤ የማዕከሉ ቦርድ አባላት በጉዳዩ ላይ ተወያይተው መሠረትን የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው ሠርተፍኬት ቢሰጧትም ባይሰጧትም ‹ለሰዎች መድረስ፤ የአቅሜን ያህል ማድረግና መርዳት በረከት የማገኝበት ኑሮዬ ነው› ብላ ለምታምነው መሠረት አጋጣሚው የበለጠ እንድትሰራበት አግዟታል፤ በጎ ፈቃደኝነት የዕድሜ ልክ አገልግሎት ነውና የልብ ህሙማን ህጻናት ወረፋ እስኪጠፋና ህጻናቱ ድነው መቦረቅ እስኪጀምሩ ድረስ ማገልገል መታደል ነው ብላ ነው የምታምነው፤

ለወትሮ ህፃናት ሲጫወቱና ሲፍለቀለቁ መመልከት ለሚያስደስታት መሠረት በዚህ አይነት ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ ህመም ጋር የተወለዱ ህጻናትን ልብ አሳክሞ ተስፋቸው ሲበራ ማየት የዘወትር ፀሎቷ ነበርና  አጋጣሚውን እንደበረከት ነው የተመለከተች፤ ግን በልብ ህመም ሳቢያ አልጋ ላይ ተኝተው አይናቸው ሲንከራተት የሚውሉ ህጻናትን ስትመለከት ስሜቷ ስስ ነው፤ መጀመሪያ ገደማ ህፃናቱን ስትመለከት እንባ ይቀድማት ነበር፤ አይታ በማልቀስ ብቻ መፍትሔ እንደማይመጣ በመረዳት በእግዚአብሔር፤ በራሷና በወላጆች ፊት ቃል ገባች፤ ‹አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ለእነዚህ ህፃናት ተስፋ ለመሆን› በማለት፤ ውላ ሳታድርም ሀ ብላ የሰዎችን በር ማንኳኳት ጀመረች፤ በየመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ በየትምህርት ቤቶች፤ በየባህል ማዕከላት የልብ ህሙማን ህጻናትን ወቅታዊ ችግሮች ይዛ በመሄድ ግንዛቤ ፈጥራለች፤

‹ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ፤ ለሃምሳ ሰው ጌጡ!› እንዲሉ መሠረት ባለፉት አራት ዓመታት ከሙያዋ ፤ ከኑሮዋና ከግል ስራዋ ላይ ያላትን ጊዜ ሳትሰስት ለማዕከሉ በማዋል በርካታ ህፃናት ልባቸው እንዲጠገን ምክንያት ሆናለች፤ የበርካታ እናቶች እንባ እንዲታበስ ማድረግ ችላለች፤እሷ በቂ ነው ባትልም፤

ከዚህ ጋር በተያያዘ ማዕከሉ በጣም በርካታ የስኬት ታሪኮች ያሉት ቢሆንም ለረዥም ጊዜ ወረፋ በመጠበቅና ወደ ህክምና ማዕከሉ መምጣት ባለመቻላቸው የሚያሸልቡ የልብ ህሙማን ህፃናት ያጋጥማሉ፤ መሰረት በዚህ ልቧ ቢሰበርም  ድነው የሚስቁ በርካታ ህፃትናን ፊት በማየት ተስፋዋ ይለመልማል፤ ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጪ ሀገር ሄደው እንዲታከሙ የሀኪሞች ቦርድ ውሳኔ ለሰጣቸው የልብ ህሙማን ህፃናት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት በግል ስልኳ፤ የፌስ ቡክ ገፃ እና በግል ግንኙነቷ በኩል ህፃናቱን በተመለከተ ጥያቄ የምታቀርብላው ሰዎች የሚያሳዩት ርብርብ ያኮራታል፤ ስማቸው ሳይገለፅ ህፃናትን ውጪ ሀገር ድረስ ወስደው የሚያሳክሙ ሰዎች መኖራቸው ተስፋ ይሰጣታል፤በአጭር ቀናት ውስጥ ጎደለ የተባለው ብር ሞልተው ህጻናቱ ከእነ አስታማሚያቸው ወደ ተባለው ሀገር ሄደው ታክመው ድነው መምጣታቸው ያስደስታታል፤ ህክምና አግኝተው ከሞት አፋፍ የተመለሱ ህፃናት  ከመሠረት ጋር ቤተሰብ ሆነዋል፤ በልደት ክብረ በዓላቸው ላይ የማትቀር እንግዳ ትሆናለች ፤

መሠረት ለምትሰራው ስራ እዩኝ እዩኝ ብላ አታውቅም፤እውቅና ፍለጋም በየሚያዎች ላይ አትታይም፤ ይልቁንም የግል ህይወታቷን ጨምሮ ከሙያዋ ጋር በተያያዘ የሚነገሩባትን አሉባልታ ለማስተባበል ሞክራ አታውቅም፤ ራሷን ከሚዲያ ካራቀች ዓመታት ተቆጥረዋል፤

መሠረት እርዳታ ከማሰባሰብ ስራ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ያልተለየው ስልትን ትከተላለች፤ ከአሁን በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ለእርዳታ ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ የሚኖረው ውዝግብ የብዙዎችን ስሜት የሚጎዳ ሆኖ ያለፈበትን አጋጣሚ እናውቃልን፤ ጥቂት ገንዘብ ለግሰው ስምና ዝናቸውን በየሚዲያው የሚያስነግሩ ወንዝ አመጣሾችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፤መሠረት በበጎ ፈቃድ አምባሳደርነቷ ለልብ ህሙማን ህጻናት ማሳከሚያ የሚሆን ገንዘብ ስታሰባስብ  ግን ከገንዘቡ ጋር አላስፈላጊ ንክኪ እንዳይኖራት በማድረግ በቀጥታ ለማዕከሉ  ገቢ የሚደረግበትን መንገድ ነው የምትከተለው፤ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ በሀገር ውስጥ ከሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ጎን ለጎን በሰሜን አሜሪካ በመጓዝ ለማዕከሉ የሚሆን ገቢ ያሰባሰበችው በዚህ መነሻነት ነው፡፡

በየዓመቱ በሰሜን አሜሪካ በሚካሄደው የሜኖሶታው የኢትዮጵያውያን የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ከፕሮግራሙ አዘጋጅ የዘሐበሻው ሄኖክ ደገፉ ጋር በመነጋገር በአንድ መድረክ የተጀመረው የገቢ ማሰባሰቢያ በ6 ከተሞች ተካሂዶ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከልብ ህሙማን ህጻናት ጎን መቆማቸውን በተግባር ያሳዩበት ጊዜ ሆኖ ተመዝግቧል፤ መሠረት ወደ አሜሪካ ስትሄድ በተወሰኑ ስቴቶች በመዘዋወር እስከ 100 ሺ ዶላር ለማዕከሉ ገቢ ለማግኘት እቅድ ይዛ የተጓዘች ቢሆንም በየሄደችባቸው ስቴቶች በነበረው አቀባበልና በእሷላይ ባሳደሩት እምነት ከእቅዷበላይ ከ126 ሺ ዶላር በላይ መሰብሰብ እችላለች፤ከሜኖሶታ የተጀመረው ፕሮግራም በሲያትል፤በአትላንታ፤ሳንቲያጎ፤ሎስአንጀለስ፤ ዲሲ፤ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በመዘርጋት ስኬታማ ገቢ ማሰባሰብ ተችሏል፤

ለአንድ ወር ያህል በቆየችባቸው ስድስት ስቴቶች በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለ ልብ ህሙማን ህጻናት ችግር ሰፊ ግንዛቤ አግኝተዋል፤ ልባቸው የተነኩትም በሙያቸውና በሀሳባቸው ከህጻናቱ ጎን ለመቆም ፍላጎት አሳይተዋል፤ ለህፃናቱ ህክምና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በላኩት ገንዘብ የታከሙና እስትንፋሳቸው የተመለሱ ህጻናት በማዕከሉ አስተባባሪነት በቅርቡ ‹የእናመሰግናለን!› ፕሮግራም ለማካሄድ እቅድ ተይዟል፤

የማዕከሉ እንቅስቃሴ

በሳምንት ከ6 እስከ 9 ለሚሆኑ የልብ ህመም ታካሚ ህፃናት ነፃ ህክምና እየሰጠ ያለው የህፃናት ልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል ህክምናውን የሚሰጠው ከህብረተሰቡ እና ከተለያዩ አካላት በሚያገኘው ድጋፍ ነው፤ ያም ሆኖ ግን  ማዕከሉ በዓመት 500 ታካሚ ህፃናትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚያስፈልገው ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን ብር በጀት የሚሰበስብው ከህብረተሰቡ ነው፡፡ ይህን ለማሳካትም  በእነ መሠረት መብራቱ አይነት የህጻናት ልብ ተስፋዎች የተለያዩ በጎ አድራጊ ተቋማትን በር ማንኳኳትና ደጅ መጥናት አስፈላጊ ነው፡፡

ማዕከሉ እስከአሁን ድረስ  በበጎ አድራጊ ድርጅቶችና ቀና ልብ ባላቸው ግለሰቦች ድጋፍ ከ9500 በላይ ህፃናትን በፈጣሪ እርዳታ  እንደ እድሜ እኩዮቻቸው እንዲቦርቁ አስችሏል፤ ግን አሁንም በየቀኑ ወደ ማእከሉ የሚመጡትን ጨምሮ ከ 7000 በላይ ህፃናት የወገንን ተስፋ ሰንቀው ይጠብቃሉ፤

በተለይም የኮቪድ 19 መምጣት የገቢ ማሰባሰብና የታመሙ የልብ ህሙማንን የቀዶ ጥገና ስራ ቢያስተጓጉለውም ማዕከሉ ከአቅሙ በታች እንዲሰራ የሚያደርገው  አላቂ የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፤

ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣውን የህፃናት የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ለሚሰጠው የህፃናት ልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሚውል አላቂ የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት አሁንም አለበት።

ለህፃናት ልብ መርጃ ማዕከሉ የሚደረጉት ድጋፎች ዘርፈ ብዙ ናቸው፤ አንዳንንድ ተቋማት በተቋም ደረጃ ማዕከሉን ለመደገፍ ጥረት ሲያደርጉ ሌሎች ሰራተኞቻቸውን በማስተባበር መዋጮ አሰባስበው ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ወረፋ በመጠበቅ ላይ የሚገኙ የልብ ሕሙማን ሕፃናትን ሕይወት ለመታደግ ወደ ውጭ ሀገር በሚሄዱበት ወቅት የትራንስፖርትና ሌሎች መጪያቸውን ከመቻል ጀምሮ ትልቅ አስተዋፅዎ የሚኖራቸው ተቋማትን በመለየት የመግባቢያ ሰነዶችን ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመፈራረምም ወደ ስራ ገብቷል፡፡

እንደ አብነትም መሠረት በአምባሳደርንት የምታስተዋውቀው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት የማዕከሉን የስድስት ወራትን ወጪ ለመሸፈን ቃል ገብቷል፤  አንድ መቶ ሕፃናትን ወደ ውጭ ሃገር ወስዶ ለማሳከም በተያዘው ፕሮግራምም  ሮታሪ ኢንተርናሽናል የሕክምና ወጪውን በመሸፈን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓዦቹን ወጪ በመሸፈን፣ የጤና ሚኒስቴር አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ እና የልብ ሕሙማን ደግሞ ወራፋ ላይ የሚገኙ ታካሚ ሕፃናትን በመለየት እና ታክመው ከመጡ በኋላ ክትትል በማድረግ በትብብር ይሰራሉ ተብሏል፤

የፌስ ቡክ ፈተና

‹መንግስት ችላ ያለው ነገር ቢኖር› ይላል በመሠረት መብራቴ የፌስ ቡክ ገፅ ስር የሰፈረ የአንድ በሀዘን የተጠቃ አባት አስተያየት ‹መንግስት ችላ ያለው ነገር ቢኖር የልብ ህሙማን ህፃናት ነገር  ነው፤እንደ ልማት ባንክ የሁሉም ተቋማት ሀላፊነት ሊሆን ይገባል፤ እነ መሲም ሊታገዙ ይገባል፤ ለ120 ሚሊየን ህዝብ አንድ የልብ ማዕከል ያሳፍራል፤ መንግስት ከሁሉም ነገሮች በፊት ችግሩን የሚቀርፉ ተቋማት እንዲበዙ ሊሰራ ይገባል፤ ችግሩ ስለደረሰብኝ ነው ወቀሳ ያበዛሁት፤ የምወደው የ4 ወር ልጄን የልብ ህክምናው ማግኘት ስላልቻለ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሞቶ ከቀበርኩት አንድ ወር ገደማ ነው፤ የችግሩ ስፋት በጣም እያመመኝ ነው።›

መሠረት ማዕከሉን ለመርዳት በስፍራው ለሚገኙ በጎ አድራጊዎች አነቃቂና ተስፋ ሰጪ ንግግር ከማድረጓ በተጨማሪ  በራሷ የግል የፌስ ቡክ ማህበራዊ ትስስር ገፆችና በ6710 የማዕከሉ የገቢ ማሰባሰቢያ የቴሌ ቁጥር ላይ  ጨምሮ በጎ ፈንድሚ ላይ ለጋሾች የህጻናቱን ልብ እንዲታደጉ ቅስቃስ ታደርጋለች፡፡

መሰረት ከ300 ሺ በላይ ተከታይ ያለው የፌስ ቡክ አካውንት  እና ከ90 ሺ በላይ ተከታይ ያለው የፌስ ቡክ ገፅ  የህፃናቱን ችግሮች በማጋራ ህክምና የሚያገኙበትን መንገድ የምታፈላልግበት ነው፤ በግሏ ኢንስታግራም ገፁዋም ተመሳሳይ መልዕክቶችን ታስተላልፋለች፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና የመሠረትን ፎቶግራች የያዙ ሀሰተኛ የፌስ ቡክ ገፆች ግን ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋራት የድጋፍ ማሰባበሰብ ስራውን እየረበሹት ነው፤ እንደማንኛውም ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ አርቲስት አንድና ሁለት ሀሰተኛ የፌስ ቡል ገፆች እንደሚከፈቱ የሚጠበቅ ቢሆንም በመሠረት ስም የተከፈቱ ሀሰተኛ ገፆች ግን ብዛታቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹ ከዋናው የመሠረት እውነተኛ ገፆች የላቁ ተከታዮችን ማፍራት ችለዋል፤

በእነዚህ ሀሰተኛ ገፆች ላይ ከዋናው ገፆች ላይ ተወሰዱ ፎቶግራፎችንን እውነት መሰል ዘገባዎች ስለሚስተናገዱባቸው የማህበራዊ ትስስር ገፁ ተከታዮች በቀላሉ ሊታለሉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፤በተለይም ከ140 ሺ በላይ ተከታይ ካለው ከኢንታግራም ገፆ ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ወስደው የሚፃፉት መልዕክቶች አንዳንዴ የግል ህይወቷን ሳይቀር የሚነኩ ሆነው ተስተውለዋል፤በቲውተር ላይም ፎቶግራፏን ተጠቅመው የፖለቲካ አክቲቪስት ያደረጓት ብዙ ናቸው፡፡

መሠረት እነዚህን ሀሰተኛ ገፆች ሀሰተኛ መሆናቸውን በተደጋጋሚ በራሷ እውነተኛ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ከማጋለጧ በተጨማሪ ገጹዋን ለማረጋገጥ/ ቬሪፋይ/ ለማስደረግ ለሜታ ኩባንያ ያቀረበችው ጥያቄ ወራት በመውሰዳቸው ሳቢያ የግል ህይወቷም ሆነ የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት ስራዋን እያወኩት ስለመሆኑ ይታያል፤ ያም ሆኖ መሰረት በስሟ ሀሰተኛ ዘገባዎች በመፃፋቸው ሳቢያ አንዳንድር ታዋቂ ሰዎች እንደሚያደርጉት ራሷን ከማህበራዊ ሚዲያ አላራቀችም ፤እውነት ነው፤ ትክክል ነው፤ ለህብረተሰቡ ይጠቅማል የምትለውንና ያንፃል የምልትለውን መልዕክቷን ታስተላልፍበታለች፤

ከዚያ ውጭ በስሟ ተከፍተው በፖለቲካ ጉዳይም ይሁን በግል ህይወቷ ዙሪያ  ‹በሬ ወለደ!› አይነት  መልዕክት የሚያስተላልፉ ግለሰቦችን ‹ልቦና ይስጣቸው! › ከማለት ውጭ ‹ለምን› ብላ አታውቅም፤

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe