መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ያሰማራ- ኢሰመጉ

 ጥቅምት፣ 22/ 2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው በተባለው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን ተከትሎ መንግሥት ችግሮቹን ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ “ህጋዊ ነው” ብሎ እንደማያምን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታውቋል።
ጎጎላ ቃንቃ በተባለው ቀበሌ በደረሰው ጥቃት የኦሮሚያ ፖሊስ 32 ሰዎች መገደላቸውን ሲገልፅ አምነስቲ የአይን እማኞችን አባሪ አድርጎ የሟቾችን ቁጥር 54 አድርሶታል።
ኢሰመጉ በዛሬው ዕለት፣ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “መንግሥት አሁን ላይ ችግሮቹን ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ ሕጋዊ፣ ትክክለኛ እና ተገቢ ነው ብሎ አያምንም። “ብሏል።
መንግሥት ጥቃቱን በማድረስ እና በመደገፍ የሚጠረጥራቸውንና የሚወነጅላቸውን አካላት ለፍርድ ማቅረብ ይገባዋል ይላል- የኢሰመጉ መግለጫ
“የሚወነጅላቸውን አካላት በመግለጫዎች ከማውገዝ ባለፈ፣ በሕግ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እና ለተጎጂዎች ፍትሕ እንዲሰጥ ዳግም ይጠይቃል። በማለትም አስፍሯል።
ከዚህም በተጨማሪ በጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎች አፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ፣ በስጋት መኖሪያቸውን ለቅቀው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ የጠየቀው መግለጫው በተጨማሪም ንብረታቸው ለወደመባቸው ተመልሰው ሊቋቋሙ ይገባል ብሏል።
የደህንነት ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎችም በመለየት የአጭር እና የረዥም ጊዜ እቅዶችን በማዘጋጀት ፈጣን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አሳስቧል።
ከትላንት በስቲያ የደረሰው ጥቃት ማንነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው በርካታ ሰዎች መሞታቸውን፣ መቁሰላቸውን እና የንብረት ውድመት መድረሱንም ከአካባቢው ባጠናቀረው መረጃ መረዳት ችሏል።
ኢሰመጉ ተጎጂዎችን አባሪ በማድረግ አሰባሰብኩት ባለው መረጃም ጥቃቱ የተፈጸመው ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ በሚል የተጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ መሆኑን ገልፀዋል።
አካባቢው በኮማንድ ፖስት በመከላከያ ሰራዊት የነበረና ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ሰራዊቱ አካባቢውን ለቅቆ ከወጣ በኋላ እንደሆነም ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe