መዳሊያ ላመጡ አትሌቶች በአዲስ አበባ 500 ካሬ ሜትር የመሬት ስጦታ ተበረከተላቸው። ስጦታው የተበረከተው በከተማው አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ ነው ተብሏል።
በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሽልማት (በካቢኔ ውሳኔ) ፦
አትሌት ለተሰንበት ግደይ 500 ካሬ ሜትር መሬት
አትሌት ጎተይቶም ገ/ስላሰ 500 ካሬ ሜትር መሬት
አትሌት ታምራት ቶላ 500 ካሬ ሜትር መሬት
አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ (ልዩ ተሸላሚ) 500 ካሬ ሜትር መሬት እና ወርቅ ቅብ ” እናመሰግናለን ” የሚል ስጦታ
ለመላው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን 10 ሚሊዮን ብር
የወርቅ ቅብ ሰሃን ” እናመሰግናለን ” የሚል ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ
አትሌት ዳዊት ስዩም 250 ካሬሜትር መሬት
አትሌት መቅደስ አበበ 250 ካሬሜትር መሬት
አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው 350 ካሬሜትር መሬት
አትሌት ለሜቻ ግርማ 350 ካሬሜትር መሬት
አትሌት ሞስነት ገረመው 350 ካሬሜትር መሬት እንዲሁም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡክ 10 ሚሊየን ብር ተበርክቷል፤
በሌላ በኩል አሁን ስራ ላይ ባለው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለማስተላለፍ በሚደነግገው የሊዝ አዋጅ 721/2004 መሠረት በጨረታ፤ በድርድርና ማህበራዊ ጠቀሜታ ላላቸው ፕሮጀክቶች በካቢኔው ውሳኔ መሠረት ብቻ ሲሆን ከዚህ በፊት በሽልማት መሬት ሊሰጥ እንደሚችል ይፈቅድ የነበረው አንቀፅ ለሙስና ተጋላጭ መሆኑን ምክንያት ባድረግ እንዲሰረዝ መደረጉ ይታወሳል፤ በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ በሽልማት መልክ የከተማ መሬትን ለግለሰቦች ማስተላላፍ የሚከለክለውን አዋጅ በተቃረነ መልኩ ለአትሌቶች መሬት መሸለሙን የተቹት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የህግ ባለሙያ ለአትሌቶቹ ከዚህ በላይም ቢደረግ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ነገር ግን በዚሁ ህግ መሠረት ከዚህ በፊት ወርቅ ላመጡ አትሌቶች ለእነ ጥሩነሽ ዲባባ፤ መሰረት ደፋርና ማሬ ዲባባን ለመሳሰሉ አትሌቶች የመሬት ሽልማት የሸለመ ሲሆን በ16ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላሸነፉ አትሌቶች ግን የከተማ አስተዳደሩ ተጠይቆ ህጉ አይፈቅድም በማለት የገንዘብ ሽልማት ብቻ እንደሰጠ ያስታውሳሉ፤
በ2017 እ.ኤ.አ በለንደን አስተናጋጅት በተካሄደው የ16ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ላይ ተካፍለው ለኢትዮጵያ ወርቅ ያመጡት በ10000 ሜትር ሴቶች አልማዝ አያና እንዲሁም በ5000 ወንዶች ወርቅ ያመጣው ሙክታር እድሪስ ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ የመሬት ሽልማት የተነፈጋቸው አትሌቶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፤ በተለይ አልማዝ አያና ድጋሚ በ5000 ሜትር ተሳትፋ የብር መዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል፤
ታምራታ ቶላ በወቅቱ በማራቶን ሁለተኛ በመውጣት ብር መዳሊያ ያስመዘገበ አትሌት የነበረ ሲሆን ታምራት በዘንድሮው ውድድር ወርቅ በማግኘቱ የመሬት ተሸላሚ ሆኗል፤
ይህ በአትሌት መሀከል የሚደረግ ልዩነት ወጥነት ሳይኖረው የሚከናወን መሆኑ የፍትሐዊነት ጥያቄ ይነሳበታል የተባለ ሲሆን መንግስት የመሬት ሽልማትን በተመለከተ ከሙስና በፀዳ መልኩ ሊያከናውን የሚችልበትን የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እንዳለበት የህግ ባለሙያው ይናገራሉ፤

