ሙሉቀን መለሰ “ከዘፈኑ ዓለም አሁን ይቀርብኛል የምለው ነገር የለም’’

በጋዜጠኝነት ህይወቴ በመድረክ ላይ ሲያቀነቅኑ የማየት እድሉን ካላገኘኋቸው አርቲስቶች መሀከል አንዱ ነው አርቲስት ሙሉቀን መለሰ። እርግጥ ነው ሙሉቀንን በመድረክ ብቻ ሳይሆን በአካልም አይቼው አላውቅም ነበር እስካለፈው ቅዳሜ ድረስ። ጋሽ ሙሉቀን ሙዚቃን አቁሞ ወደ መንፈሳዊ ህይወት 1976 ሲገባ እኔ ገና አልተወለድኩም/በሙያ ማለቴ ነው /ከሙሉቀን ጋር ሀገር ቤት እያለሁ ለበርካታ ጊዜአት በስልክ አውርቻለሁ።

ቨርጂኒያ የሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በአካል ሳየው የተሰማኝ ስሜት ግን ልዩ ነበር።አንድ አርቲስት ሙዚቃ ካቆመ 33 አመታት በላይ ሆኖት ዛሬም እንደ አዲስ ድምጻዊ ተወዳጅ የመሆኑ ምስጢር ምን እንደሆነ ለማብራራት ስለሙዚቃ ሳይንስ ጠለቅ ያለ እውቀት ሳይጠይቅ አይቀርም። ሙሉቀን ከጥቂት ወራት ጀምሮ ስለ ጥላሁን ገሠሠሰጠከተባለው አስተያየት ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ሰሞኑን ደግሞ ስለመሞቱ በዙከበርግ ሰሌዳ ላይ ተለጠፎ ታይቷል። ይህንኑ ወሬ የሰሙ ወዳጅ ዘመዶቹም በተደጋጋሚ ስልክ ይደውሉለት ነበር።

ከምሳ ግብዣ በኋላ ቡናችንን ይዘን ለቁም ነገር መጽሄት አንባቢያ የሚሆን ነገር ተጨዋውተናል። ሙሉቀን ጨዋታ ይችላል ብቻ ሳይሆን የዛሬ 30 አመት በፊት የነበሩ ክስተቶችን እያዋዛ ሲተርክ ይገርማል። …..

ቁም ነገር፡በመጀመሪያ ለቁም ነገር አንባቢያን ሃሳብህን ለማካፈል ስለወደድክ እናመሰግናለን፤ሰሞኑን ስላንተ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚነገር ነገር ነበር። ሰምተኸው ይሆን ?

ሙሉቀን፡እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፤ ሰምቼዋለሁ።

ቁም ነገር፡ምንድነው?

ሙሉቀን፡ሙሉቀን ሞቷል ነበር ያሉት። አንድ ጊዜ አይደለም ብዙ ጊዜ ብለዋል። እኔ እንኳ አልከታተለውም። ሰዎች ናቸው እየደወሉ የሚነግሩኝ።

ቁም ነገር:- ማነው እንዲህ የሚለው አሉህ

with muluken meles

ሙሉቀን:- እኔ አላውቃቸውም። የአሁኑን እንኳ እስራኤል ሀገር የሚኖር ሰው ነው የጻፈው ብላ አለምጸሀይ ወዳጆ ደውላ ነግራኛለች።

ቁም ነገር:- አሁን ግን ጤንነትህ እንዴት ነው?

ሙሉቀን፡እግዚቸብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። ህክምናዬን በአግባቡ እየተከታተልኩ ነው፣ አሁን እንደውም የተወሰነ ሰዓት ዎክ አደርጋለሁ። ደህና ነኝ።

ቁምነገር፡አሁን ከማን ጋር ነው የምትኖረው?

ሙሉቀን፡ከቤተሰብ ጋር ነኝ፣ ባለቤቴም አለች፣ ልጆቼም እዚህም ኢትዮጵያም አሉ።

ቁም ነገር፡ወደ ኋላ ልመልስህና ድሮ በሙዚቃ ሙያ ውስጥ ሳለህ የሙዚቃ መሳሪያ ትጫወት ነበር ይባላል፡፡

ሙሉቀን፡ሁለገብ ሙያተኛ ነበርኩ፣ እዘፍናለሁ፣ ግጥምና ዜማ እሰራለሁ። የሙዚቃ መሳሪያም እጫወት ነበር። ለምሳሌ የኩኩ ሰብስቤ ዘፈን ሲቀረጽ ድራም ተጫውቻለሁ። የብዙነሽ በቀለ ዘፈን ላይ ደግሞ ትራንፔት ተጫውቻለሁ። በነገርህ ላይ ቦብ ማርሌ አዲስ አበባ የመጣ ጊዜ አብረን ሰርተናል። ስምንት ዘፈኖችን በጋራ ለመዝፈንና ሲዲ ለንደን ላይ ማውጣት ተነጋግረን ነበር። ሲሞት ያው ተገላገልኩ።

ቁም ነገር፡ቀደም ሲል ከብዙአየሁ ደምሴ ጋር የነበረው አለመግባባት በምን ተቋጨ?

ሙሉቀን፡ብዙ አየሁ ቀድሞውኑ ስራውን ሲሰራ አላስፈቀደኝም። የማውቀው ነገር የለም። የሆነ ቀን አንድ ቡና ቤት ገብቼ ቡና ስጠጣ አንድ ሰው መጥቶ እግሬ ላይ ወደቀ። ምንድነው ስል ያንተን ዘፈን የተጫወትኩት ነኝ ይቅርታ አድርግልኝ አለኝ። እንደሰው ይቅርታ አድርጌልሃለሁ፣ ግን ተደብቀህ ሰርቀህ በዝፈንህ ግን አዝኛለሁ አልኩት።

ቁም ነገር፡ግን እኮ አንድ ዘፈን የተወሰነ ዓመት ካለፈው የህዝብ ይሆናል ይባላል፣

ሙሉቀን፡ስህተት ነው። እዚህ ሀገር ያሉ አርቲስቶች ሰርተው ካለፉ በኋላ እንካ ቤተሰቦቻቸው ወራሽ ይሆናሉ። የኢትዮጵያ ህግ ብቻውን ይህንን መብት ሊከለክል አይችልም።

ቁም ነገር፡ሙሉቀን ሙዚቃ አቁሟል፣ ወጣት አርቲስቶች የቆዩ ዘፈኖችን እንደገና ዘፍነው ቢጠቀሙ ምን አለበት የሚሉ ሰዎች አሉ?

ሙሉቀን፡ጥሩ ጥያቄ ነው። የሚሰራው ያጣ፣ ሰው ይለምናል እንጂ አይሰርቅም። ሙሉቀን ትቷቸዋልና ብሰርቃቸው የሚጠይቀኝ የለም ማለት ተገቢ አይደለም። የተቸገረ ሁሉ ይስረቅ ከተባለ እኮ ህገ ወጥነት ነው የሚሰፍነው።

ቁም ነገር፡ግን ፈቃድ ቢጠይቁህ ትፈቅድላቸዋለህ?

ሙሉቀን፡ልፈቅድ እችላለሁ፣ ላልፈቅድ እችላለሁ። በዛ ወቅት የምኖርበት ሁናቴ ነው የሚወስነው።

ቁም ነገር፡ከጥቂት ዓመታት በፊት ያንተን ዘፈኖች አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ በአዲስ መልኩ አንተ ሳትዘፍን በኪቦርድ ብቻ አቀናብሮት በሲዲ ተቀርፆ ለገበያ ቀርቧል። አውቀኸው ነው የወጣው?

ሙሉቀን፡አውቀዋለሁ፣ ያንን አይነት ስራ መስራት የሚችለው አበጋዝ ብቻ ነው። የእኔን ድምፅ ከሙዚቃው መለየት የሚችል ነው። ከዛ በኋላ ሙዚቃውን በተሻለ መንገድ በመጫወት አዋህዶታል። እኔም ስራውን ሱፐርቫይዝድ አድርጌዋለሁ።

ቁም ነገር፡ክፍያውስ?

ሙሉቀን፡ወደ 65 ዶላር ተከፍሎኛል። ግን በአንድ ጊዜ አይደለም፣ በተለያየ ጊዜ ነው።

ቁም ነገር፡ግን ሙሉቀን ዘፈን አቆመ እንጂ ከዘፈኑ መጠቀም አላቆመም የሚሉህ አሉ?

ሙሉቀን፡በስራዬ ብጠቀም ችግሩ ምንድነው፣ የሰው እጅ ከማየት ይሻላል። መካፈል የፈለገ ካለ ይጠይቀኝ። ለሻይ መጠጫ የሚሆን ነገር እሰጣለሁ /ሳቅ/

ቁም ነገር፡እንደው አብረውህ ከሰሩ ደራሲያን መሀከል የምታደንቃቸው የትኞቹን ነው?

ሙሉቀን፡ብዙ ናቸው፣ የመጀመሪያው ከህዝብ ጋር የተዋወቅሁበትን ስራ የሰጡኝ አቶ ተስፋዬ አበበ ናቸው። በመጀመሪያ እንቧይ ሎሚ መስሎ ሰው ያደናግራል፣ የሚለውን ድርሰት ሰጡኝ፤ ከዛ 

እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ፣

የፊት ጉዴን ትታ እደግ ማሞ አለችኝ፣

በሚለው ዘፈን የበለጠ ታወቅሁ። ከዛ በኋላ አለምፀሀይ ወዳጆ፣ ይልማ /አብና አበበ መለሰ ጋር ሰርቻለሁ።

ቁም ነገር፡የሸዋሉል መንግስቱስ?

ሙሉቀን፡እሷ የተለየች ናት። ላተርፋት ባለመቻሌ ሁልጊዜ እቆጫለሁ። ኢህአፓ ትልቅ ሰው ነው ያሳጣን፣ በዚህም የተነሳ ኢህአፓዎችን አሁንም ድረስ ተቀይሜአቸዋለሁ።

ቁም ነገር፡ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ተገናኛችሁ?

ሙሉቀን፡ በለው የሚል አንድ ዘፈን ነበረኝ፣ በዛ ዘፈን ላይ የራሴን የፍቅር ዘፈኖች ጨምሬ ዘፍኜ ዘፈኑን ሰማችና ይሄ እኮ የጀግና ዘፈን ነው ለምንድነው የፍቅር ግጥም ጨምረህ የዘፈንከው፣ ከፈለግህ እኔ ድርሰቶችን እሰጥሀለሁ ብላ ይዛ መጣች፣ በዚህ መልኩ ነው የተገናኘነው፡፡

ቁም ነገር፡የቱን ዘፈን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠችህ?

ሙሉቀን፡– ‹‹ጀመረኝ ፍቅር ጀመረኝ›› የሚለውን ዘፈን ነው። ከዛ በኋላ ወደ አስር ዘፈኖችን ድርሰት ሰርታ ሸክላ አውጥቻለሁ። ደሞ እኮ ግጥሙንም ዜማውንም ራሷ ሰርታ ነው የምታመጣው። ስንፍና የማታውቅ በጣም ተሰጥኦ ያላት ልጅ ነበረች። በህይወት ብትቆይ በጣም ምርጥ ምርጥ ስራዎችን ትሰራ ነበረ ብዬ አምናለሁ። በእድሜ ትንሽ ብትበልጠኝም ጥሩ ቅርርብ ነበረን።

ቁም ነገር፡ከወራት በፊት በጥላሁን ገሠሠ ዙሪያ የሰጠኸው አስተያየት አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፤ ምንድነው የተፈጠረው ነገር?

ሙሉቀን፡እኔ እንደምታውቀው ቃለ መጠይቅ ለማንም ሰው ሰጥቼ አላውቅም፤ ብዙዎቹም ይጠይቁኛል፤ ከሬዲዮም ከጋዜጣም፤ ከመፅሔትም፣ መንፈሳዊ ሚዲያም ጠይቀውኝ ፈቃደኛ አልሆንኩም፡፡ ታዲያ እዚህ ሀገር አንድ ጊዜ ቨርጂኒያ ውስጥ አንድ ጋዜጣ ትወጣለች፡፡ ናፍቆት የምትባል ነች፡፡ የነጋዴዎች ማስታወቂያ ልዩ ልዩ የቢዝነስ ዜናዎች የምታወጣ ጋዜጣ ናት፡ ፡ እና የዛን ጊዜ የወጣችው ጋዜጣ የፊት ለፊት ገፅ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ /ጊዮርጊስ ፎቶ አለ፡፡ ታዲያ ከፎቷቸው ስር የተፃፈው ምን ይላል መሰለህ? ‹ፕሬዚዳንቱ ሞተዋልይላል፡፡ እሳቸው ደግሞ አሁንም በህይወት አሉ፡፡ ከዛ ቀጥሎ የእኔ ፎቶግራፍ አለ፡፡ እኔ ፎቶ ስር ደግሞ ታዋቂው ዘፋኝ ሙሉቀን መለሰ በጠና ታሟል፤ በሞት አፋፍ ላይ ነው ያለው፤ ወዳጅ ዘመዶቹእየጠየቁት ነውብሎ ፅፏል፡፡

ቁም ነገር፡በወቅቱ ታመህ ነበር?

ሙሉቀን፡አልታመምኩም፤ ታመሃል ብሎ እንኳ አልጠየቀኝም፤ ሰውየውን አላውቀውም ይህንን የፃፈውን፡፡ ከዛ ያንን የተመለከቱ ሰዎች እየተደናገጡ እኔ ጋር መደወል ጀመሩ፤ ሁኔታውን ሲረዱ ጋዜጣው ላይ ባለው የስልክ አድራሻ ሲደውሉለት አላናግር እያለ ወደ መልዕክት ማስቀመጫ ሳጥን ውስጥ ስልኩን ያስተላልፋል፡፡ እኔም ጥቂት ቀን ቆይቼ ስደውልለት ወደ መልዕክት ማስቀመጫ ማሽኑ ይሰደኛል፤ ከዛ እኔም የሰራው ስራ ትክክል እንዳልሆነ መልዕክት አስቀመጥኩለት፡፡

ቁም ነገር፡መቼ ነው?

ሙሉቀን፡አንድ አራት ዓመት ይሆነዋል፡፡ ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ቺካጎ ውስጥ ሌላ ናፍቆት የሚባል መፅሔት ይታተማል፡፡ እዛ መፅሄት ላይ አንድ እኔን የምታደንቅ ልጅ ግሩም የሆነ ፅሑፍ አውጥታ አንድ ሰው ይዞልኝ ይመጣል፤ እንደውም ባለቤቴ ነች መሰለኝ ይዛ የመጣችው፡፡ ሳነበው ከዛ በፊት የቤተክርስቲያን መድረክ ላይ የተናገርኩትን ሰምታቤተክርስቲያን ሙሉቀንን በደንብ አልያዘችውም፤ በደንብ አገልግሎት እየሰጠ አይደለምበሚል ተነሳስታ ነው ያንን ፅሑፍ ያወጣችው፡፡

ቁም ነገር፡ካንተ ጋር ትተዋወቃላችሁ?

ሙሉቀን፡እኔ አላውቃትም፡፡ ፅሑፉ በጣም ጥሩ ስለነበር የመፅሔቱ አዘጋጅ ጋር ደውዬ ይህንን ፅሑፍ የፃፈችውን ሰው ማግኘት እፈልጋለሁ፤ አድራሻዋን እባክህ ስጠኝ አልኩት ሰጠኝ፤ ደወልኩላት መፅሔቱ ላይትዝታበሚል የብዕር ስም ነበር የፃፈችው፡፡ ከዛ ተግባባን ፤ሩቅ ቦታ ነበር የምትኖረው ባለቤቷንም ይዛ መጥታ ተዋወቅን ቤተሰብ ሆንን የተወሰነ የገንዘብ ስጦታም አበረከቱልኝ፤ ከዛ የተሰወነ ጊዜ ስንደዋወል ከቆየን በኋላ የመፅሔት አዘጋጅ ቃለ ምልልስ አድርጎ ለአንባቢያን አሁን ያለህበትን ታሪክ ለማውጣት ይፈልጋል ብላ ደወለችልኝ፡፡ ተይ እኔ ከዚህ በፊት ለሬዲዮም ለጋዜጣም ቃለ ምልልስ እምቢ ብያለሁስላት ትንሽ ጊዜ ቆይታ እንደገና ታነሳብኛለች፡፡ በየጊዜው እየደወለች ደግማ ደግማ ደግማ ስትጨቀጭቀኝ ተረታሁላት፤ለሰውየው ስልኩን ሰጥታው ላነጋግርህ አለኝ፡፡

ቁም ነገር፡በአካል ወይስ በስልክ?

ሙሉቀን፡በስልክ ነው፤ እሱ ያለው ቺካጎ ነው፡፡ እኔ ያለሁት ዋሽንግተን ነው፤ ሰውየውን በአካል አይቼው አላውቅም፡፡

ቁም ነገር፡ጋዜጠኛውን?

ሙሉቀን፡አዎ፣ ግርማ ዘገየ ነው የሚባለው፡፡ ከዛ ቃለ ምልልሱን ከማድረጋችን በፊት አንድ ቃል አስገባሁት፡፡ በስልክ የምናደርገውን ቃለ መጠይቅ ድሮ የነበርኩበትን ህዝቡ ያውቀዋል፡፡ አሁን ከሙዚቃውም ከወጣሁ ብዙ ጊዜዬ ስለሆነ ለወጣቱ ትውልድም የት ነው ያለው? ምን ይሰራል? ብሎ ለሚጠይቅ ሰው እንግዲህ አሁን ስላላሁበት ሁኔታ እንድንነጋገር ነው የምፈልገው፤ ስለው ችግር የለውም ግን መነሳት ያለብን ከድሮው ድምፃዊነትህ ነውአለ፡፡ እሺ ግን ደግሞ አሁን የምንነጋገረውን ቃለ መጠይቅ በፅሑፍ አሳይተኸኝ ከተፈራረምን በኋላ ነው የምታወጣው ብዬ ስለው ሳንፈራረምማ ሳይታረም እንዴት ይወጣል? አለ፤ ከዛ ነው መነጋጋር የጀመርነው፡፡ ስለ ድሮው ሁኔታ የተወሰነ ነገር ካወራን በኋላከዘፋኞች ማንን ታደንቃለህ?› አለኝ፡፡ እኔ መጀመሪያ የምወደውና የማደንቀው ምንሊክ ወስናቸውን ነው፤ ከዛ ተሾመ ምትኩን፤ ከዛ ማህሙድ አህመድን ከዛ ጥላሁን ገሠሠን አልኩት፡፡ ይህን ጊዜ አንደኛ የሚባለውን ጥላሁንን እንዴት አራተኛ አደረከው?› አለኝ፡ ፡ ይሄ የምርጫ ጉዳይ ነው፤ የሙዚቃ ሰዎች የየራሳቸው አስተያየት አላቸው፤ ብዬ ስለሙዚቃ ምንነት ማወቅ ከፈለግህ የምትፅፈው ሳይሆን ለራስህ ግንዛቤ እንዲሆንህ ላስረዳህ ብዬ አንዳንድ ምሳሌዎችን እየጠቀስኩ ነገርኩት፡፡ ልብ አድርግ ይሄ ላንተ ብዬ የማስረዳህ ነው እንጂ የምትፅፈው አይደለም ብየዋለሁ፡፡ የሚገርምህ ግን ገና ቃለምልልሱን አድርገን ሳንጨርስና ለሌላ ቀን ቀጠሮ ይዘን ከተለያየን በኋላ ክፍል አንድ፣ ክፍል ሁለት እያለ ማውጣት ጀምሯል፤ ገና እኮ

የመንፈሳዊ ህይወቴን ታሪክ አልነገርኩትም።

ቁም ነገር፡ሳታየው ማለት ነው?

ሙሉቀን፡እውነቴን ነው የምልህ፤ የምዋሽበት ምንም ምክንያት የለም፤ መውጣቱን ያዩ ሰዎች አምጥተው ሲያሳዩኝ ሁሉም ተደናገጠ፡፡ ከዛ ሁሉ ካወራነው ወሬ ውስጥ መርጦ ያወጣው ስለጥላሁን የተናገርኩትን ነው፡፡ በዛ ላይ ለእርሱ ላስረዳው ብዬ የነገርኩትጨምሮ

ያላልኩትንጥላሁን ዘፋኝ አይደለም አለብሎ ነው ያወጣው፡፡ ጥላሁን እኮ ወንድሜ ነው፤ በስራው መንገድም ሙዚየም ሊሰየምለት የሚገባ ሰው ነው። ብዙ ነገር አብረን ያሳለፍን ወዳጄ ነው፡፡ ጓደኛ ከመሆናችን የተነሳ ወደ መንፈሳዊ ህይወት ከመግባቴ በፊትቄሱእያለ ነበር የሚጠራኝ፤

ቁም ነገር፡ለምን?

ሙሉቀን፡ምክር ስለማበዛ ነዋ! እሱ ግን ያልጠየቀኝን ሁሉ እየጨመረ ነው ያወጣው፤ ከዛ ንድድ አለኝ፣ ከዛ ሲደወል ለምን ሳታሳየኝ አወጣኸው? ስለው ህዝቡ እየጠበቀ ስለሆነ ነው ያወጣሁት አለኝ፤ በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ አይነት ሰው መሆንህን ባውቅ ኖሮ ቃለ ምልልሱን አልሰጥህም ነበር፡፡ አሁንም ይቀጥላል ያልከውን ነገር ትተህ ቀጣዩን ክፍል አቋርጠው አልኩት፡፡ በዚሁ ተለያየን፡፡ ግን ከዛ በኋላ ቃለ ምልልሱን ሳያቆም ሌላ ፅሁፍ በእኔ ላይ ፃፈ፡፡

ቁም ነገር፡ምን የሚል?

ሙሉቀን፡አሉባልታ ነገር ነው፤ ሙሉቀን ያለ እርሱ ሀይማኖተኛ ያለ አይመስለውም፤ ያለ እርሱ ዘፋኝ ያለ አይመስለውም። እየሱስን ተቀበል አለኝ እያለ መጻፍ ጀመረ፤ ከዛ ያኔ በፊት የወጣችውን ጋዜጣ ትዝ አለችኝ፡፡ አጠገቤ ያሉ ሰዎችንም ስጠይቅ ያቺ ጋዜጣ ናፍቆት

እንደምትባል አስታወሱኝ፡፡ በዛ ቂም ተነሳስቶ ነው ድጋሚ ያጠቃኝ፤

ቁም ነገር፡ከጋዜጠኛው ጋር ያገናኘችህን ሴት አግኝተህ አላነጋገርካትም?

ሙሉቀን፡አናግሬያታለሁ፤ ይሄ ሰውዬ እኮ እንደዚህ አደረገኝ፤ ስላት እንዴት? አለች፤ ስንነጋገርም እሷ ስለሌለች አሁን ምን እናድርግ አለች፤ አሁን ንገሪው ለህዝቡ ያለእኔ ፈቃድ ቃለ ምልልሱን ማውጣቱን ተጠቅሶ ይቅርታ ይጠይቅ ብዬ ነግሬያታለሁ፡፡ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ጥላሁን ዘፋኝ አይደለም ብዬ አልተናገርኩም፡፡ ልልም አልችልም፡፡ እንደውም ራሴ ደውዬ የት ቦታ ነው ጥላሁን ዘፋኝ አይደለም ብዬ. ስጠይቀው እንደዛ ብለህ አንተም አልተናገርክም፤ እኔም አልጻፍኩትም ሲለኝ በስልኬ ቀድቼዋለሁ። ልትሰማው ትችላለህ ድምጹን። መጽሄቱ ላይ ግን ጽፎታል። እኔ ከዘፈኑ የወጣሁት የተሻለ አግኝቼ ነው፡፡ እውነቱን በመናገር ነው የምታወቀው፡፡ በፊትም አሁንም እውነቱን ነው የምናገረው፡፡ ከዘፈኑ ዓለም አሁን ይቀርብኛል የምለው ነገር የለም፡፡ ሌላው ደግሞ በሀገር ቤት ሌላ መፅሔት ይህንኑ ስህተት ያሳተመ መፅሄት እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡ ለመሆኑ መፅሔቱ ያንን ቃለ ምልልስ ሲያትም ሙሉቀን ይህንን ተናግረሃል ወይ?› ማለት አልነበረበት? የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርስ ይፈቅድላቸዋል ወይስ ሙሉቀን መንፈሳዊ ሰው ስለሆነ ምንም አያደርገንም ብለው ነው ይህንን የሚያደርጉት? በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡

ቁም ነገር፡አዲስ አበባ ላይ የታተመው መፅሔት አዘጋጆችን ልታነጋግራቸው አልሞከርክም?

ሙሉ ቀን፡እኔ ከእነርሱ ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም፡፡ አላውቃቸውም፡፡ ነገር ግን ግርማን ጠይቄዋለሁ፤ እሱ ያንን ከእኔ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ለማንም እንዳልሰጠና ከዌብ ሳይት ላይ ወስደው ያለ እርሱ ፍቃድ እንደሰሩ ነው የገለፀልኝ፡፡ ይህንን ሲናገርም ቀድቼዋለሁ።

ቁም ነገር፡አመሰግናለሁ፡፡

(ቁም ነገር መጽሄት ነሃሴ 2009)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe