ሚኒስትሯ  ለመደበኛ ስልካቸው ያላግባብ የተከፈለውን 109 ሺሕ ብር ትምህርት ሚኒስቴር እንዲመልስ ተደረገ

የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ለሚጠቀሙበት የመደበኛ ስልክ ክፍያ ጣሪያ እንዲወጣ ፓርላማው ጠይቋል፤ዝርዝር አለን

በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የበላይ ኃላፊዎች ለመደበኛ ስልክ የሚከፈል ገንዘብ ጣሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲያወጣ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠየቀ፡፡

በቀድሞው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መደበኛ ስልኮች ወርኃዊ የፍጆታ ጣሪያ ባለመውጣቱ ለተቋሙ ሥራ መዋሉ በኦዲት ማረጋገጥ አለመቻሉን፣ በ2012 ዓ.ም. ለተወሰኑ ስልኮች ብቻ አገልግሎት እንደተከፈለ የተገለጸ 2.6 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታውቋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የ2012 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ግኝት ላይ ባደረገው የውይይት መድረክ፣ የመደበኛ ስልክ የፍጆታ ጣሪያ ሳይቀመጥለት በርካታ ገንዘብ መባከኑ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች የሚጠቀሙባቸው መደበኛ ስልኮች፣ የክፍያ ጣሪያን የሚወስን አሠራር እንደሌላቸው በውይይቱ ወቅት ተነግሯል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በመንግሥት ተቋማት አመራሮች ለሚጠቀሙባቸው መደበኛ ስልኮች፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የክፍያ ጣሪያ እንዲያወጣ አሳስበዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም. በሥራ ላይ እንደዋለ የቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የገለጸውንና በኦዲት ለማረጋገጥ ያልተቻለውን 2.6 ሚሊዮን ብር የስልክ ወጪ፣ በአማካይ አሥር ሺሕ ብር እየተከፈላቸው የሚሠሩ 22 ሠራተኞችን መቅጠር እንደሚቻል አቶ ክርስቲያን ተናግረዋል፡፡

በኦዲት ግኝቱ ሪፖርቱ ከላይ ከተጠቀሰው ገንዘብ በተጨማሪ በተቋሙ የስልክ ዝርዝር ውስጥ ላልተካተቱ የስልክ ቁጥሮች በአጠቃላይ 68,062.32 ብር ክፍያ መፈጸሙን፣ እንዲሁም አገልግሎት ለማይሰጡ 47 የስልክና የፋስክ መስመሮች በአጠቃላይ 9,317.28 ብር ክፍያ መፈጸሙ ተመላክቷል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር የፋይናንስና ግዥ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አበራ ጎዴቦ፣ የቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በመስከረም 2014 ዓ.ም. ለሁለት ከመከፈሉ በፊት የቀድሞዋ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደ ማሪያም (ፕሮፌሰር) ተቋሙን ከለቀቁ ጀምሮ ከሕግ ውጪ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስም 109 ሺሕ ብር ለመደበኛ ስልካቸው መከፈሉን ገልጸዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም.ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሯ  የተጠቀሙትን ገንዘብ እንዲመልሱ በደብዳቤ ተጠይቀው ገንዘቡን መ/ቤቱ መመለሱን አስረድተዋል፡፡

በኃላፊነት ደረጃ የነበሩና በእጃቸው ንብረት ይዘው የት እንዳሉ የማይታወቁ ኃላፊዎች አሁንም ስለመኖራቸው ለሪፖርተር የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የመንግሥት ተቋማት የበላይ ኃላፊዎች የሚመሩትን ተቋም ሲለቁ አንድ ሠራተኛ ከሥራው ሲለቅ እንደሚጠየቀው መልቀቂያ (ክሊራንስ) ስለማይጠየቁ፣ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጠር ይችላል ብማለታቸውን ሪፖርትር ዘግቧል፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe