ማብቂያ ያጣው የኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሞት መንገድ

ሞትና የሞት ዜና ለኢትዮጵያውያን አዲስ ክስተት መሆኑ እያበቃ ይመስላል፡፡ በተለይም ሀገር ጥለው በሚሰደዱ ስደተኞች ዙሪያ የሚደርሰው ሰቆቃ በዓለም መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ለዜናነት መብቃቱ ከስንት አንድ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንም ዘንድ /በተለይ በመንግስቶቹ/ ከስደት ጋር የተያያዘው ዜና ለአቅመ ዜናነት መብቃት ሳይችል እየቀረ ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢነቱ እንዳለ ነው፡፡ በባህር ሲጓዙ ፤ በበረሃ ሲያቋርጡና በሰው ሀገር ገብተው የሚያዙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ አንዳንዱ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፡፡

ሰሞኑን   ከጂቡቲ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ባሕር ውስጥ ሰምጠው የሞቱት እና ደብዛቸው የጠፋው ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አይኦኤም ለቢቢሲ  አረጋግጧል። ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይኦኤም ለቢቢሲ ሐሙስ አመሻሽ ላይ እንዳረጋገጠው በጀልባዎቹ ላይ የነበሩት እና በአደጋው የሞቱት ከ45 በላይ ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ከጂቡቲ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በደረሰ አደጋ ቢያንስ 45  ስደተኞች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ላይ ተገፍትረው መሞታቸው ተዘግቧል።

በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ክፍል ሚኒስትር አማካሪ የሆኑት አቶ አደራ ተመስገን አደጋው የደረሰው በሁለት ጀልባ ተሳፍረው ከየመን ወደ ጂቡቲ እየመጡ በነበሩ ስደተኞች ላይ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኤምባሲው ሠራተኛ ጨምረውም አደጋው የደረሰባቸው ስደተኞች በባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እንዳይያዙ ወደ ባሕር ዳርቻው ሳይደርሱ ከጀልባው “እንዲወርዱ በመደረጉ [ወደ ውቅያኖሱ ዘልለው እንዲገቡ በመገደዳቸው]  አብዛኞቹ ዋኝተው መውጣት ባለመቻላቸው ለሞታቸው ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይኦኤም በበኩሉ በጂቡቲዋ ኦቦክ የባሕር ዳርቻ ላይ ያጋጠመው አሰቃቂው አደጋ ስደተኞቹ በኃይል ከጀልባዎቹ ላይ ወደ ባሕሩ እንዲገቡ በአዘዋዋሪዎች በመገደዳቸው ነው ብሏል።

በዚህ ዓመት ብቻ (እኤአ በ2024)  ከአራት ጊዜ በላይ የጀልባ መስመጥ አደጋ መከሰቱን የተናገሩት አቶ አደራ ከሟቾቹ መካከል ኢትዮጵያውያን ሊኖሩበት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ከ45  በላይ ስደተኞች የሞቱበት እና በርካቶች ደብዛቸው በጠፋበት በዚህ አደጋ ተሳፍረው የነበሩ ስደተኞች ከየመን ወደ ጂቡቲ በራሳቸው ፍላጎት እየተመለሱ የነበሩ ሲሆን “አንዳንዶቹ በሄዱበት ጀልባ የሚመለሱ” እንዳሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ስደተኞችን ከየመን አሳፍረው ወደ ጂቡቲ ሲጓዙ የነበሩት ሁለቱ ጀልባዎች ከ300 በላይ ሰዎችን ይዘው ነበር። በዚህም አንደኛው 100 ሁለተኛው ደግሞ 210 ስደተኞችን አሳፍረው ወደ ጂቡቲ ሲያመሩ እንደነበር ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ተናግረዋል።

አይኦኤም እንዳለው በጀልባዎቹ ላይ የነበሩት ስደተኞች ወደ ጂቡቲ የባሕር ጠረፍ ሲቃረቡ የመናዊ በሆኑት የሰው አዘዋዋሪዎች ወደ ባሕሩ እንዲገቡ እና በዋና ወደ ዳርቻው እንዲደርሱ አስገድደዋቸው በርካቶች ለሞት ተዳርገዋል።

ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደተናገሩት አንዲት ሴት ሰምጣ ስትሞት የአራት ወር ልጇ ከሌሎች 98 ሰዎች ጋር በሕይወት ሊተርፍ ችሏል።        የፍልሰተኞቹ ድርጅት ከጂቡቲ የመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን በባሕሩ ውስጥ የገቡትን ሰዎች ለማዳን ባደረጉት ጥረት 55 ሰዎች በሕይወት ለማትረፍ ችለዋል። ሌሎች የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል።

የጂቡቲ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ አባላት “እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት 61  ሰዎች የገቡበት አልታወቀም። ሰዎቹን ለማግኘት የምናደርገው ፍለጋ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

አይኦኤም እና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረባው እንደሚሉት በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉ ከተረጋገጠው እና መሞታቸው ከታወቁት ውጪ ከ110 በላይ ስደተኞችደብዛቸው ጠፍቷል።

በዓለማችን በርካታ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ የሚጓጓዙባቸው ናቸው ከሚባሉ አስፈሪ የባሕር መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው ይህ ሥፍራ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች አህጉሪቱን ጥለው ለመውጣት ይጠቀሙበታል።

ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ በአደጋው ደብዛቸው የጠፋውን ሰዎች ለማግኘት “መጠነ-ሰፊ ፍለጋ” እየተደረገ መሆኑን ያሳወቀው የጂቡቲ ባሕር ጠረፍ ጥበቃ ከአይኦኤም ጋር በመተባበር እስካሁን 115 ሰዎችን ማዳን መቻሉን ገልጿል።

የባሕር ጠረፍ ጥበቃው አክሎ እንዳስታቀው ጀልባዎቹ ተገልብጠው የሰመጡት ሰሜን ምዕራብ ጂቡቲ ከምትገኘው ኾር አንጋር ግዛት 150 ሜትር ርቀት ላይ ነው።

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ቀይ ባሕርን ተጠቅመው በነዳጅ ሀብት ወደ በለፀጉ የባሕረ ሰላጤ አገራት ይጓዛሉ። ስደተኞቹ በአገሮቻቸው ያሉ ግጭቶችን፣ ተፈጥዊ አደጋዎችን እና የኑሮ ውድነትን በመሸሽ ነው የሚሰደዱት።

ባለፈው ዓመት ሰኔ በተመሳሳይ የመን ድንበር አቅራቢያ ቀይ ባሕር ላይ አንዲት ጀልባ ተገልብጣ 56 ሰዎች መሞታቸውን 140 ሰዎች መጥፋታቸው ይታወሳል።

የአደጋው ሰለባ የነበሩት ስደተኞች ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የመጡ ነበሩ። ከሟቾቹ መካከል 31 ሴቶች እና ስድስት ሕፃናት ይገኙበታል።

ቀይ ባሕርን ተጠቅመው ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2022 ከነበረው 73 ሺህ ወደ 97 ሺህ 200 ማደጉን አይኦኤም አስታውቋል።

አብዛኞቹ ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት ነው ይህን ባሕር መስመር ለማቋረጥ የሚሞክሩት።

ስደተኞቹ ብዙውን ጊዜ ለአደጋ የሚጋለጡት በአነስተኛ ጀልባ በከፍተኛ ቁጥር ታጭቀው በአደገኛው ባሕር ላይ ለመጓዝ ሲሞክሩ መሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል።

አሁን ያጋጠመውን አደጋን በአውሮፓውያኑ 2024 ካጋጠሙት አሰቃቂው መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በአይኦኤም በተደረገው ምዝገባ በምሥራቁ የስደት መስመር ከ1,300 በላይ ሰዎች ባሕር ውስጥ ሰጥመው የሞቱ ናቸው፡፡

የምሥራቁ መስመር ተብሎ በሚታወቀው ከሱማሊያና ጅቡቲ ወደ የመን በሚወስደው የፍልሰት መስመር በኩል የሚጓዙ ፍልሰተኞች ቁጥር ባለፉት ሁለት ዓመታት በ13 በመቶ መጨመሩን ዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት አስታውቋል።

በተጠቀሰው ዓመት በዚህ መስመር በኩል ከኢትዮጵያ የወጡ ፍልሰተኞች ብዛት በ27 በመቶ ጨምሮ ቁጥሩ ከ234 ሺሕ በላይ መድረሱን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል። በዚሁ ዓመት በመስመሩ ከተጓዙ ፍልሰተኞች መካከል 96 በመቶዎቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው ተብሏል።

በተጠቀሰው ዓመት 462  ፍልሰተኞች በጀልባ መስጠም እንደሞቱም ድርጅቱ ጠቅሷል። ባለፉት ወራት ከሳዑዲ ዓረቢያ ከተመለሱት ፍልሰተኞች መካከል፣ 35 በመቶዎቹ ወደ አማራ ክልል፣ 30 በመቶዎቹ ወደ ትግራይ እና 29 በመቶዎቹ ወደ ኦሮሚያ ሂደዋል ተብሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe