ማኅበራዊ ሚዲያ እና የአእምሮ ጤና

ከዚህ ቀደም ለሰው ልጅ አስቸጋሪ የነበረው ፈተና ብቸኝነትን መጋፈጥ ነበር፡፡ ዘንድሮ ፈተናው የተለየ መልክ ይዟል፡፡ መረጃዎች በዝተዋል፡፡ የመረጃ አውታሮች ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ የሰው ልጆች በየዕለት ኑሯቸው ውስጥ መረጃ የእህል ውኃ ያህል የሚያስፈልጋቸው ኾኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያው ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ይህ መልካም ቢኾንም ከቁጥጥር ውጪ መኾኑና ለሌሎች ተግባራት መስጠት ያለብንን ጊዜ ለማኅበራዊ ሚዲያ ብቻ መስጠታችን የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት ጀምሯል፡፡
በእርግጥ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶችም ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች ቀዳሚ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ አንድ ጥናት አመልክቷል እንደተባለውም በአሜሪካ የሚገኙ ከሃያ በመቶ በላይ ተማሪዎች በየዕለቱ ለአምስት ሰዓት ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ‹ከመጠን በላይ የኾነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በአእምሮ ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምን ይኾን?› የሚል ጥያቄ ያነሱት የጥናት ባለሙያዎች በአነስተኛ መጠን ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም የቻሉ ሰዎች የተሻለ የአእምሮ ጤንነት ያላቸው መኾኑን ደርሰውበታል፡፡ ለምሳሌ ማኅበራዊ ሚዲያን አብዝተው የሚጠቀሙ ሰዎች አብዝተው ከማይጠቀሙት አንጻር ለድብርት የመጋለጥ ዕድላቸው ሦስት እጥፍ ጨምሮ ታይቷል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን በበዛ ቁጥር ከዕውነታው ዓለም በተለየ መንገድ ተገቢ ላልኾነ ጠባይ፣ ተጨባጭ ላልኾኑ ሕልማዊ ሐሳቦች እንዲሁም በምንከታተላቸው መረጃዎች ተፅዕኖ ስር በከፍተኛ ደረጃ መውደቅ ውስጥ እንገባለን፡፡ ‹ንቁ› የሚባሉ ዓይነት ተጠቃሚዎች (ማለትም በተደጋጋሚ ሐሳቦችን፣ ምስሎችና ቪዲዮዎች የምንለጥፍ) ከኾንን ከእያንዳንዷ ልጥፍ አድናቆት ወይም ‹ላይክ› የምንሻ በመኾኑ እነኚህ አድናቆቶች ሲቀንሱ ራሳችንን ወደመጠራጠር እንገባለን፡፡ ራሳችንን የሁሉም ነገር ማዕከል አድርገን እንመለከታለን፡፡ ችግራችንን በቀላሉ መረዳት ያቅተናል፡፡ የሚተቹንን ሰዎች ከማጥቃት የማንመለስና እንድንደነቅና እንድንወደስ ብቻ የምንሻም እንኾናለን፡፡ ይህ ስሜት በወቅቱ መታከም ካልቻለ ራስን ወደመጥላት ከፍ ሲልም ራስን እስከማጥፋት ሊመራ ይችላል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያን ከመጠን በላይ መጠቀም አካላዊ ጤናን የመጉዳት አቅም እንዳለውም የጥናት ባለሙያዎች አረጋግጠዋል፡፡ የእንቅልፍ መጠን እንዲያንስ ያደርጋል፣ ይህ ደግሞ በቂ እንቅልፍ በማግኘት መሟላት የነበረበትን የጤና ሁኔታ በእጅጉ ያቃውሰዋል፡፡ ለራስ ምታት፣ ለዕይታ ችግር እንዲሁም ለረጅም ሰዓት መቀመጥ ለሚያመጣቸው ሌሎች የጤና እክሎችም ይዳርጋል፡፡
ታዲያ ችግሩን ለመቅረፍ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
የመጀመርያው መፍትሔ ከጊዜ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሰዓታችን ላይ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ ነው፡፡ በቀን ጥቂት ሰዓት ወይም በሳምንት ጥቂት ቀናት ሊሆን ይችላል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አስፈላጊ ኾኖ ስናገኘው ብቻ መጠቀም እንልመድ፡፡
ሌላኛው መፍትሔ ደግሞ ሌሎች አማራጮችን ከመመልከት ጋር ይገናኛል፡፡ ብዙ ሰዎች ዲጂታል ዕቃዎችና ማኅበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙት ማኅበራዊ ግንኙነት ለመመሥረትና በዚያ ውስጥ መቆየት እንዲችሉ በማሰብ ነው፡፡ ስለዚህ በቡድን ከጓደኞቻችን ጋር መጫወት፣ ቤተሰባዊ የጋራ ጊዜያት በአብሮነት ማሳለፍ፣ መዝናኛ ስፍራዎች ላይ መገኘት፣ ማንበብ ወይም ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ይመከራል፡፡

መነሻ ምንጭ፡- psychologytoday.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe