ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርጫ መታዘቢያ የይለፍ ካርድ መከልከሉ ተሰማ

ምርጫ ቦርድ ኮሚሽኑ ላቀረበው የይለፍ ካርድ ጥያቄ ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓም በጽሁፍ ምላሽ መስጠቱን የሪፖርተር ምንጮች የገለጹ ሲሆን ፤ ቦርዱ በሰጠው ምላሽም በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ስነምግባር አዋጅ አንቀጽ 123 ድንጋጌ መሠረት ቦርዱ በምርጫ ጣቢያ ተዘዋውረው መታዘብ እንዲችሉ የይለፍ ካርድ ይሰጣቸዋል ተብለው ከተገለጹት አካላት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አለመገለጹን በምክንያትነት የሚጠቅስ ነው።

ቦርዱ በሰጠው በዚህ የጽሁፍ ምላሽ መሠረት በምርጫ ጣቢያዎች ለመገኘት የይለፍ ካርድ የሚሰጣቸው ፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀማጭና ተዘዋዋሪ ወኪሎች ፣ ለምርጫ ታዛቢዎች ፣ ለጋዜጠኞች መሆኑ በዚሁ አዋጅ እንደተጠቀሰ እና ትርጓሜም እንደተሰጠው አስረድቷል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቦርዱ የይለፍ ካርድ ይሰጣቸዋል ተብለው በአዋጁ ከተገለጹት ውስጥ የሚገኝ ባለመሆኑ ቦርዱ የይለፍ ካርድ መስጠት እንደማይችል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ምላሽ በመቃወም ቦርዱ ውሳኔውን ዳግም ገምግሞ ማስተካከያ እንዲያደርግ መጠየቁን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ እና ክትትል የማድረግ ስልጣን በተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 1224/2020 በአንቀጽ 6(11) ድንጋጌ የተሰጠው መሆኑን እንዲሁም ፤ ማንኛውም ሰው ለኮሚሽኑ ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠት ግዴታ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 39 የተጣለበት መሆኑን በመጥቀስ ቦርዱ ውሳኔውን እንዲያስተካክል ጠይቋል።

ቦርዱ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን ባከናወነበት ወቅት ለኮሚሽኑ አስፈላጊውን የይለፍ ካርድ መስጠቱን በማስታወስ ቦርዱ አሁንም አስፈላጊውን የይለፍ ካርድ እንዲሰጠው በደብዳቤ ማሳሰቡን ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል።

ምርጫ ቦርድ ሰኔ 7 ቀን በሰጠው የጽሁፍ ምላሽ በተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ኮሚሽኑ በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ ክትትል እንዲያደርግ ስልጣን የተሰጠው መሆኑን እንደሚገነዘብ የጠቀሰ ሲሆን ፤ ነገር ግን ኮሚሽኑ በምርጫ ጣቢያዎች እንዲገቡ በቦርዱ የይለፍ ካርድ እንደሚሰጣቸው በአዋጅ 1162/2011 ከተጠቀሱት መካከል የኮሚሽኑ ስም ባለመጠቀሱ የይለፍ ካርዱን ለመስጠት እንደማይችል አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ክትትል የማድረግ ስልጣን በአዋጅ እንደተሰጠው ቦርዱ ካመነ ቦርዱ ፤ ኮሚሽኑ ይህንን ኃላፊነቱን እንዴት ሊወጣ እንደሚችልም ማወቅ አልያም መገመት ይኖርበታል ሲሉ ምንጮቹ ይገልጻሉ።

ኮሚሽኑም ለቦርዱ በጻፈው የምላሽ ደብዳቤ ” ለዓብነት የምርጫ ጣቢያዎች እና የምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በምርጫ ጣቢያዎች መገኝትን እና ማጣራትን ይጠይቃል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ማስረዳታቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል። /reporter newspaper/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe