ምርጫ ቦርድ የሶማሌ ክልል ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ አደረገ

በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የተሰጠውን አሉታዊ አስተያየት አጣጥሎታል

የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ በሚያነሱባቸው ቀበሌዎች ሊያቋቁማቸው የነበሩ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙ መወሰኑን በመቃወም፣ የሶማሌ ክልል ያቀረበውን አቤቱታ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ውድቅ አደረገ።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከሶማሌ ክልል የቀረበውን አቤቱታ ውድቅ ከማድረጉ በተጨማሪም፣ የምርጫ ጣቢያዎች የት እና እንዴት እንደሚቋቋሙ የመወሰን ሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው ለምርጫ ቦርድ መሆኑን በማስታወስ፣ ይህንን አስመልክቶ ቦርዱ የሚሰጠውን ውሳኔ ክልሎች ተቀብለው ማስፈጸም እንዳለባቸው አሳስቧል።

ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎች እንዴት እንደሚቋቋሙ የሚወሰነው ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ በመሆኑ፣ ‹‹የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች የሥልጣን ውዝግብ ምክንያት ሊሆኑ አይገባም፤›› ብሏል።

የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የአስተዳደር ጥያቄ የሚያነሱባቸው ሰምንት ቀበሌዎች ላይ የሚቋቋሙ 30 የምርጫ ጣቢያዎች፣ በሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያ ሥር ተካለው በምርጫ ቦርድ ይፋ ተደርገው የነበረ ሲሆን፣ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ‹‹ቀበሌዎቹ የአፋር የአስተዳደር ወሰን አካል በመሆናቸው፣ በሶማሌ ክልል ሥር ሊካለሉ አይገባም›› የሚል አቤቱታ አስቀድሞ አቅርቦ ነበር። 

ቦርዱ ከአፋር ክልል የቀረበለትን ቅሬታ በመመርመር መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጥቶበታል።

ቦርዱ በሰጠው ውሳኔም የውዝግብ ምክንያት በሆኑት ቀበሌዎች እንዲቋቋሙ የተባሉት 30 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙና በቀበሌዎቹ የሚኖሩ ሕዝቦች ‹‹እንዳይቋቋሙ›› ከተባሉት የምርጫ ጣቢያዎች አቅራቢያ በሚገኙ የምርጫ ጣቢዎች በመመዝገብ በምርጫው መሳተፍ እንደሚችሉ የሚገልጽ ነው።

ይህንን ያወሰነውም ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ እንጂ የምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀት ከክልሎች የአስተዳደር ወሰን ጋር ግንኙነት ኖሮት እንዳልሆነ አስገንዝቧል።

ይሁን እንጂ ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አልተቀበለውም። ቦርዱ ውሳኔውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ቅሬታውንም በደብዳቤ ለቦርዱ አቅርቧል።

የሶማሌ ክልል ተጠባባቂ ርዕሰ መስተዳደር በሆኑት አቶ ሙስጠፋ ኡመር ተፈርሞ ለምርጫ ቦርድ የተላከው የቅሬታ ደብዳቤ፣ ምርጫ ቦርድ ያሳለፈው ውሳኔ ለአንድ ወገን ያደላና ፍትሐዊ በመሆኑ፣ በሶማሌ ክልል መንግሥት በኩል ተቀባይነት እንደሌለው ይገልጻል።

ለውዝግብ ምክንያት የሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች ባለፉት አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች፣ በሶማሌ ክልል ሥር ሆነው ምርጫዎቹ መከናወናቸውን ያስታወሰው የሶማሌ ክልል፣ ‹‹ባለፉት ጠቅላላ ምርጫዎች ሲደረግ በነበረው አግባብ የምርጫ ጣቢያዎቹ እንዲቋቋሙ እያሳሰብን ይህ ካልሆነ በምርጫው ለመሳተፍ የምንቸገር መሆኑን እናሳውቃለን፤›› ብሏል።

የሶማሌ ክልልን አቤቱታ ውድቅ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ውዝግብ በተነሳባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ቀሪ እንዲሆኑ የወሰነው ከምርጫ ሰላም አኳያ ብቻ እንደሆነና ውሳኔውም በአፋርም ሆነ በሶማሌ ክልል የአስተዳደር ወሰን ክርር ላይ ውጤት እንደማይኖረው አስታውቋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በምርጫው ለመወዳደር እንቸገራለን በማለት የሰጡትን አሰተያየት በተመለከተም፣ በምርጫ የሚወዳደሩት ፓርቲዎችና ዕጩዎች እንጂ የክልል መንግሥታት እንዳልሆኑ እየታወቀ ‹‹ርዕሰ መስተዳድሩ በምርጫው ለመሳተፍ እንቸገራለን ሲሉ የገለጹት፣ በሕግ ዕይታ ትርጉም ምንም ትርጉም የማይሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲል ቦርዱ አጣጥሎታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሶማሌ ክልል ያነሳውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አስመልክቶ ክልሉ የሚሰጠውን ምላሽ ወይም አስተያየት ለማካተት ሪፖርተር ወደ ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe