ሦስተኛው ዙር ”ዳሸን ከፍታ“ የሥራ ፈጠራ ውድድር በተለየ መልኩ ሊጀመር ነው

ዳሸን ባንክ በሥራ ፈጠራ ዘርፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት እየተገበረ ያለው ”ዳሸን ከፍታ“ የሥራ ፈጠራ ውድድር ለሦስተኛ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሊካሄድ ነው፡፡
ባንኩ ውድድሩን ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማካሄድ በአማካሪነት ከቀጠረው ዊቬንቸር ሆልዲንግስ ከተሰኘ ሃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት እንዲሁም የሚዲያ አጋር ከሆነው የአፍሪካ ሬኔሳንስ ቴሌቪዥን (አርትስ ቲቪ) ጋር በትላንትናው ዕለት ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ፣ም በዋናው መስሪያ ቤት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የዘንድሮው ውድድር በባህር ዳር፣ ደሴ፣ መቀሌ፣አዳማ፣ድሬዳዋ፣ወላይታ፣ ሃዋሳ፣ጅማና አዲስ አበባ ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን፤ በነዚህ ከተሞች በባንኩ ቅርንጫፎች የሰልጣኞች ምዝገባ ከሰኔ 18 እስከ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ይከናወናል፡፡
ለተመዘገቡ ተወዳዳሪዎች በሥራ ፈጠራ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል ሥልጠና በነዚህ ከተሞች ከተሰጠ በኋላ ሰልጣኞቹ የፈጠራ መነሻ ሃሳባቸውን በፅሁፍ በባንኩ ቅርንጫፎች በኩል እንዲያቀርቡ የሚደረግ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት የተመረጡ ተወዳዳሪዎች ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተጨማሪ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ለውድድር ዝግጁ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ስልጠናውም ተወዳዳሪዎቹ የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን እንዴት መሸጥ እንደሚችሉና የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ወደገበያ ማቅረብ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የውድድሩ አሸናፊዎች ከዕውቅና እና ሽልማት በተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያገኙም ተጠቁሟል፡፡
ባለፉት አመታት በተከናወኑት የዳሽን ከፍታ የስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተውና የፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎላቸው ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ለሌሎች ወጣቶች ጭምር የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe