ሞስኮ ከቀናት በፊት ባስተናገደችው የሩሲያ-አፍሪካ አለም አቀፍ የፓርላማ ጉባኤ ላይ የሞስኮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የእስያና አፍሪካ ሀገራት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አሌክሲ ማስሎቭ ይፋ እንዳደረጉት የሩሲያ ት/ቤቶች አፍሪካዊ ቋንቋዎችን በትምህርት አይነትነት መስጠት እንደሚጀምሩ መግለፃቸውን የዘገበው TASS ነው። በዚህም የስዋሂሊ እና አማርኛ ቋንቋዎች ትግበራ የሚጀመር ይሆናል ነው ያሉት የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር.።
ቋንቋዎቹ ከዚህ ቀደም በሩሲያም ሆነ በሶቪየት ኅብረት ዘመን በትምህርትነት ያልተሰጡ ናቸው ያሉት አሌክሲ ማክሎቭ አክለው እንደገለፁት “ሀገረ ሩሲያ፣ የአፍሪካዊያንን እሳቤና መሰረታዊ የዕድገት ዘይቤዎች ለመረዳትና አህጉረ አፍሪካም ትልቅና አንድነት ያላት መሆኗን መረዳት የሚችል አዲስ ትውልድ በማፍራት ላይ ናት።
ተቋማቸው ጠፍተው የነበሩ በርካታ ቋንቋዎችን ለማስተማርን እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ በትምህርትነት እየተሰጡ ከሚገኙት መካከል ዮሩባ፣ ሶማሊኛ፣ ዙሉ እና ሌሎች በርካታ ቋንቋዎችን የሩሲያ ተማሪዎች በትኩረት እየተማሯቸው ይገኛል ብለዋል።
በዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ ሩሲያ ከምዕራባውያን አገሮች ጋር የገጠማትን የዲፕሎማሲ ተጨባጭ ተከትሎ በሩሲያ ት/ቤቶች ይሰጥ የነበረውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ በቻይንኛ የመተካት ሃሳብ በወርሃ ታህሳስ 2022 ለሩሲያው ስቴት ዱማ ቀርቦ እንደነበር ያወሳው ደግሞ ሞስኮ ታይምስ ሲሆን፤ ይህን ሃሳብ ያቀረቡት የሩሲያ ስቴት ዱማ የደህንነትና የፀረ-ሙስና ኮሚቴ አባል የሆኑት ቢጅሱልታን ካምዛቭ ነው። በዚህም የቻይንኛ ቋንቋ “አስገዳጅ (compulsory) ሆኖ በሩሲያ ሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ መካተት እንዳለበት አምናለሁ ብለዋል። ሩሲያዊው ህግ አውጪ አክለውም ቻይና እና የአረብ ሀገራት በራቸውን ከምዕራባዊ ሀገራት ይልቅ ለሩሲያ ክፍት እያደረጉ በመጡባት የአለማችን ተጨባጭ ሁኔታ በትምህርት ቤቶች የቋንቋ ማስተማር ላይም ልውጠት ይፈጠር ዘንድ ግድ የሚል ነው።
የዱማው የትምህርት ኮሚቴ ኃላፊ ኦልጋ ካዛኮቫ በበኩላቸው የሥርዓተ-ትምህርቱ ለውጥ በወቅታዊው ፖለቲካዊ ተጨባጭ ላይ ብቻ ተመስርቶ እንግሊዘኛ ላይ እንደማይዘምት የተናገሩ ሲሆን፣ አዲሱ የቋንቋ ማስተማር የቻይንኛ ቋንቋን በት/ቤት ስርአተ ትምህርት ላይ ገቢራዊ ከማድረግ በፊት የማስተማሪያ ቁሳቁሶች፣ የመማሪያ መጽሃፎችና የመሳሰሉ ግብአቶችን ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር ይሆናል ብለዋል።

