ርዕሰ አንቀጽ = አየር ላይ ቆመናል፤ መውደቂያችን ያስፈራል!

ጥሎብን ለራሳችን ጀግኖች የምንሰጠው ቦታ አናሳ ነው፡፡ ከተገለገልንባቸው በኋላ እንደ ሸንኮራ አገዳ መጥጠን እንጥላቸዋለን፡፡ ከነመፈጠራቸው እንዘነጋቸዋለን፡፡ ህይወታቸው ሲያልፍ ለተወሰነ ጊዜ ሸብ ረብ ካልን በኋላ ከዚያ በፊት እንዲያ የሚባል ሰው እንደሌለ ሁሉ ስማቸውን ማንሳት እንኳ እናቆማለን፡፡
ከመሬት ስር ቀብረን የተውናቸው ጀግኖቻቸን ብዙ ናቸው፡፡ ከሞቱ በኋላ የዘነጋናቸው የትውልዱ አርአያዎች ቁጥር አድጓል፡፡ ትላንትን እንዳልነበር ሁሉ አፈር አልብሰነዋል፡፡ አየር ላይ ቆመናል፡፡ መውደቂያችን ያስፈራል፡፡
በቁምነገር መጽሔት ላይ በተከታታይ አሁን በህይወት ስለሌሉት እና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በየዘርፉ ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ታላላቅ ሰዎች እያነሳን በስማቸው አደባባይ እንዲሰየም፣ ሙዚዬም እንዲቋቋም፣ ሐውልታቸው ትውልዱ በሚያየው ቦታ እንዲቆም ይሄ እንኳ ባይቻል በተቀበሩበት ቦታ ያለው ሐውልታቸው በእንክብካቤ እንዲያዝ ጮኸናል፡፡ ሰሚ ባያገኝም፡፡ የሚመለከታቸውን ተቋማትም በደብዳቤ እስከመጠየቅ ደርሰናል፡፡ የሚገርመው ነገር አንዳቸውም ምላሽ አልሰጡንም፡፡ ደብዳቤውን ቅርጫታቸው ውስጥ ወርውረው ፊታቸውን አዙረዋል፡፡ ‹ሮምን በባዶ እግሩ የወረረው› ልበ ብርቱው አትሌት አበበ ቢቂላ በአደባባይ ላይ ሐውልት ሊቆምለት ይገባል ብለን በዚያ ዙሪያ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ከጠየቅናቸው አካላት መካከል ቅንነታቸውን ያሳዩት የጃፓን ኤምባሲ የስራ ሃላፊዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱ ይሄን ያደረጉት አበበ ቢቂላ በሃገራቸው ምድር ኦሎምፒክን ስላሸነፈ ነው፡፡ ከዚያ ያለፈ ከአበበ ጋር የሚያስተሳስራቸው ገመድ የለም፡፡
አበበ የበቀለባትን ምድር የሚያስተዳድሩት ሰዎች ግን ለጻፍንላቸው ደብዳቤ እንኳን ምላሽ የሚሰጡበት ቅንነት አልነበራቸውም፡፡ ይህ ጉዳይ በትውልድ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ እኛም ሰሚ ባይኖርም እንኳ ጩኸታችንን እንቀጥላለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe