ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ ተጠየቀ!!

እናት ፓርቲ መንግሥት ታጣቂ ቡድኖች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ዘግናኝ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ማስቆም ካልቻለ በይፋ ዓለማቀፍ እገዛ ይጠይቅ አለ እናት ፖርቲ ፤

ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች ብሄራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅም ፖርቲው ጠይቋል፤

ታጣቂዎች ቅዳሜ’ለት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ 260 ንጹሃንን እንደገደሉ ሮይተርስ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል። ከጥቃቱ የተረፉ አንዳንድ እማኞች ጥቃቱን የፈጸሙት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች እንደሆኑ እና ሟቾችም የአማራ ብሄር ተወላጆች እንደሆኑ ተናግረዋል።

አብን በበኩሉ የፌደራል፣ የኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን ለመከላከል እና ጭፍጨፋውን የሚያስቆሙ ተጨባጭ ርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁነትና ፍቃደኝነት ሊያሳዩ አልቻሉም ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል።

አብን መንግሥት በአማራዎች ላይ የሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን እንደ ተፈጥሯዊ እና መደበኛ ክስተት ቆጥሯቸዋል በማለትም ወቅሷል። መንግሥት ጭፍጨፋውን ማስቆም ካልቻለ የጥቃት ተጋላጭ ዜጎችን ጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ራሳቸውን ከጭፍጨፋ የሚከላከሉበትን ሁኔታ ባስቸኳይ እንዲፈጥር፣ ጭፍጨፋውን የፈጸሙና ተባባሪ የመንግሥት አካላትን ለሕግ እንዲያቀርብ እና በሕይወት ለተረፉት አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ አብን ጨምሮ አሳስቧል።

እናት ፓርቲ መንግሥት ታጣቂ ቡድኖች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ዘግናኝ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ማስቆም ካልቻለ በይፋ ዓለማቀፍ እገዛ ይጠይቅ ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። መንግሥት የንጹሃንን ጭፍጨፋ በቸልታ ያለፉ የክልልና የአካባቢ አስተዳደር ኃላፊዎችን በሕግ እንዲጠይቅና በምትካቸው ከጥላቻ የጸዱ አመራሮችን እንዲሾም እና ሕዝብን ለከፋ ጥቃት ከማጋለጥ እንዲቆጠብም ፓርቲው አሳስቧል። ፓርቲው ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች ብሄራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅም ጠይቋል።

ባልደራስ፤ ኢዜማና ነፃነትና እኩልነት ፖርቲዎች በየፊናቸው የምዕራብ ወለጋውን የንፀሃን ጭፍጨፋ ያወገዙ ሲሆን መንግስት አነስተኛ የሚባለውን የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ተግባሩን ለመፈፀም አለመቻሉን ጠቅሰው ወቅሰዋል፤

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ኢመደበኛና ሕገወጥ ታጣቂ ቡድኖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት ተቀባይነት የለውም በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ጽፈዋል። ዐቢይ ኅብረተሰብን ማሸበር ዓላማቸው ያደረጉ ቡድኖች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሟቸውን ሕይወት ቀጣፊ ድርጊቶች መንግሥታቸው እንደማይታገስም እና ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላምና ደኅንነት ማስፈን ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢ መደበኛ ታጣቂ ቡድን ያሉት ማን እንደ ሆነ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አላብራሩም፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe