ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት መክፈት እንደማትፈልግ ገለፀች

የሱዳን የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር አብደላህ ሐምዶክ እሁድ እለት ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የመክፈት ፍላጎት እንደሌላት ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገራት መካከል አለመግባባት በፈጠረው የድንበር ጉዳይ ሱዳን ጦርነት ውስጥ ያለመግባት “የፀና አቋም” እንዳላት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ይህንን ያሉት እሁድ ዕለት በፊንላንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራውን የአውሮጳ ልዑካን ቡድን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ሁለቱ አገራት ይገባኛል የሚሉትን የድንበር አካባቢ ጉዳይ ለመፍታት፣ ሱዳን በኃይል ከያዘችው አካባቢ ለቅቃ መደራደር እንደሚያስፈልግ ስትናገር ቆይታለች።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር ያለውን ውጥረት ለመፍታት የሶስተኛ አካል ጣልቃ ገብነትን እንደማትፈልግ አቶ ውሂብ ሙሉነህ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድንበር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ቴክኒካል አማካሪና በኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባል ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሁለት አገሮችን ያወዛገበው ድንበር፤ ከፍ ያለ የእርሻ ልማትና ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች የሚደምቁበት አካባቢ ነው። በሁለቱም አገሮች የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪ ድንበርተኞች የይገባናል ጥያቄን ያነሱበታል፡፡

እሁድ እለት ሱዳን ካርቱም የገባውን የአውሮፓ ልዑካንን ቡድን የመሩት የፊንላንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትርንና የተለያዩ የአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ሱዳን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ስላላት አቋም እና በአገሪቱ ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ መነጋገራቸውን የአገሪቱ ዜና ወኪል ዘግቧል።

ሱዳን በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ካከናወነች በብሉ ናይል ዳርቻ በሚኖሩ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ሕይወት አደጋ ውስጥ ይወድቃል ስትል ማስረዳቷን የሱዳን ዜና አገልግሎት፣ ሱና ዘግቧል።

የሱዳን ካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር የአውሮፓ ልዑክ የሁለት ቀን የሥራ ጉብኝትን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ላይ ልዑኩ የአውሮፓና ሱዳን ትብብርን በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን ባገናዘበ መልኩ እንዲሁም የሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ውጥረትን ስደተኞችን እንዲሁም የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ መወያየታቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።

የአውሮፓ ልዑክ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።የአውሮፓ ልዑክ ቡድንም ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያደረገው ውይይት ውጤታማ እንደነበር መግለፁ ተመልክቷል።

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ምሥራቃዊው የአል-ቀዳሪፍ ግዛት ላይ ማንኛውንም የአየር በረራ እንዳይካሄድ ማገዷ ይታወሳል።

ለመሆኑ ከዚህ ድንበር ጋር በተያያዘ ያለው ታሪክ ምንድነው?

ኢትዮጵያና ሱዳን የሚጋሩት ድንበር ርዝመት 750 ኪሎ ሜትር ያካላል። ነገር ግን ይህ ድንበር አብዛኛው ርቀት ግልጽ በሆነ መንገድ መሬት ላይ አልተመላከተም።

ይህን ለማሳካት ተደጋጋሚ ንግግሮች ተጀምረው በተደጋጋሚ ተቋርጠዋል። ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ የተባሉ ተመራማሪ፤ “የአፍሪካ ቅኝ ግዛት ዘመን ድንበሮች በተለይም የሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ” በተሰኘና በእንግሊዝኛ በተጻፈ ጥናታቸው እንደገለጹት የሁለቱ አገሮች ድንበር የአሁን ጊዜ ወሰን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1902 እና በ1907 የተደረጉ የአንግሎ-ኢትዮጵያ የካርታ ላይ ምልከታ ስምምነቶችን መሠረት ያደረጉ ናቸው።

በቅኝ ግዛት ወቅት በሱዳንና በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለተመላከቱ ድንበሮች ኃላፊነቱ ተሰጥቶት የነበረው ሁነኛ ሰው የአይሪሽ ተጓዥና አሳሽ የነበረው ቻርለስ ግዊይን ነበር።

የሱዳን ገዳሪፍና ብሉ ናይል ግዛቶች ከአማራ ክልል ጋር ይዋሰናሉ። በ1908 ነበር በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ድንበር የተሰመረው።። የአልፋሽቃ ማዕዘን ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በይገባኛል የምትወዛገብብት አካባቢ ረዥም የግዛት ድንበር ነው ያላት።

ሁለቱም አገሮች ለም ነው የሚባለውን ፋሽቃ አካባቢን እጅጉኑ ይፈልጉታል።ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ማዕዘን ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ድንበር ሁለቱም አቅጣጫ የሚገኙ ገበሬዎች ባሻገራቸው ያሉ ለም መሬቶች ላይ ያማትራሉ።

አልፋሽቃ ማዕዘን በደቡብ ምሥራቅ ሱዳን ምሥራቃዊ ገዳሪፍ የሚገኝ ለም መሬት ነው።አልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው።

ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞችም በቅርብ ይገኛሉ። ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር በድጋሚ ለማስመር፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ቀደም ካለው አስተዳደር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሬው ሕዝብ ሉአላዊ መሬቱን ቆርሶ እየሰጠ ነው በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ነው የቆየው።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ቀን እንዲያሳውቁ መመርያ አስተላልፈውላቸው ነበር።ሆኖም አወዛጋቢውን ድንበር መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ እስከዛሬም አልተሳካም፡፡

Sourceቢቢሲ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe