ሲኖዶሱ ስለ የኦሮሚያ ቤተክህነት እንቅስቃሴ ያሳለፈው ውሳኔ

ሲኖዶሱ ስለ የኦሮሚያ ቤተክህነት እንቅስቃሴ ያሳለፈው ውሳኔ
———————————————————-

1- አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ ሰላም እና ፍቅርን በመስበክ እና በተግባር በመፈጸም ለሀገር እና ለመላው ዓለም አርኣያ የሆነችውን እናት ቤተ ክርስቲያን ያለ ስሟ ስም፣ ያለግብረዋ ግብር በመስጠት በተለይም የተከበረውን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ባለውለታ የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳገለልችው እና አቅዳ እንደበደለቸው ለማስመሰል እና ለማስቆጠር አቅደው ቤተ ክርስያኒቱን እና ሀገርን ለመከፋፈል ድብቅ አጀንዳ ይዘው በተነሡ ግለሰቦች እና ቡድኖች አለአግባብ እየተሠራጨ ያለው አፍራሽ እና ከፋፋይ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም እና ድምጽ ካለመሆኑ በተጨማሪ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ እንደሚያስረዳን ሕገ ወጦቹ ግለሰቦቹ እና ቡድኖች የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የሚያገለግለው እና የሚባርከው መንፈሳዊ አባት እንደሌለው ቢገልጹም እንኳንስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ነፃነት ከተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ የተገኙት እና ነፍሳቸውን ሳይሳሱ በሰማዕትነት ዋጋ የከፈሉትን የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ታሪክ የማይረሳውን ውለታ የዘነጋ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት በመዓርገ ጵጵስና ሹማ በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት ለሐዋርያ አገልግሎት አሠማርታ መላውን የክልሉን ሕዝበ ክርስቲያን በማገልገል ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ ለክልሉ ሰላም እና አንድነት ዋጋ በመክፈል ላይ የሚገኙትን ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙትን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና በእነሱ የሚመሩ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ያሉ በርካታ ጽ/ቤቶች ከዐሥራ አምስት የሚበልጡ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶች እና መዋቅሮችን ፈጽሞ የካደ አድርጎት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ እያወገዘ በዚህ አድርጎት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከዚህ አድርጎታቸው እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፤

2- የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የኦሮሞ ሕዝብ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ እንደ ትናንቱ ሁሉ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ በተቻላት አቅም መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ለማድረግ የጸሎት፣ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እና ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጎም እና በማዘጋጀት፣ ከአምስት በላይ የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ አንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅን በጀት መድባ በማቋቋም መላውን የኦሮሞ ብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ስታገለገል የቆየችውን እና ያላቸውን ወደ ፊትም ዘመኑን በዋጀ መልኩ አጠናክራ የምታገለግለውን እናት ቤተ ክርስያናችሁ መሆኗን አውቃችሁ አንድነታችሁን እና ፍቅረ ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመከፋፈል የተነሡትን የጥፋት ኃይሎች በጽናት በመቃወምና አንድነት እና ፍቅራችሁን አጠናክራችሁ ቤተ ክርስያናችሁን እና ሃይማኖታችሁን ከጥፋት ኃይሎች ትጠብቁ እና ትንከባከቡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል፣

3- አዲስ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚል መዋቅር በራሳቸው ሥልጣን መሥርተው በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ በሰጣቸው እድል ቀርበው የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም ወቅት ጥያቄውን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን ቀደም በኮሚቴ ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቶበት እያለ ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠው በማስመሰል ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ አዲስ መዋቅር ፈጥረው መግለጫ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን አምነው ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 የተቀጠሩ ቢሆንም በዕለቱ የኮሚቴው ዋና ተጠሪ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ያልተገኙ ሲሆን 2 የኮሚቴው አባላት ብቻ ከተሰጣቸው ሰዓት አሳልፈው ከመምጣታቸውን በላይ 2ቱ ግለሰቦች በጽሑፍ ባቀረቡት ምላሽ በሕገወጥ አቋማቸው የፀኑ መሆናቸውን የገለጹ በመሆኑ የግለሰቦቹ እንቅስቃሴም ሆነ የኦሮሞ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተብሎ የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን አውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተ ክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ትጠብቁ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

4- ከዚህ በላይ በተገለጸው መሠረት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልናም ሆነ ከሕገ የመነጨ ሥልጣን ሳይኖራቸውና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሕግ የመነጨ መብት በመጋፋት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሎጎ /አርማ/፣ ማህተምና መጠሪያ ስያሜ መጠቀማቸው ሕገወጥ አድራጎት በመሆኑ የሚመለከታችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሎጎ /አርማ/ እና ማህተም እንዲሁም መጠሪያ ስያሜ መጠቀም የማይችሉ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምት በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ታስከብሩ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት እያሳሰበ፤ የጽ/ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያም በሕገወጦች ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ አዟል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe