ሳህለ ሥላሴ ብርሃነ ማሪያም- ኢትዮጵያዊው “ጃክ ለንደን”

ብዙ ቋንቋ ይናገራሉ። በብዙ ቋንቋዎችም መጻፍ ይችላሉ። ከሁሉ በላይ ግን የተዋጣላቸው ተርጓሚ ናቸው። በአማርኛ ስነ-ጽሑፍ ውስጥ የሚታወቁትን ያህል በጉራጊኛ የልብ ወለድ ድርሰቶችም ፋና ወጊ ናቸው። ባለፉት ስድሳ ዓመታት በሶስት ቋንቋዎች (ጉራጊኛ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ) እየጻፉ ለሀገራችን ስነ-ጽሑፍ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ለብቻቸው ካሳተሟቸው ስራዎች መካከል ስምንቱ ወጥ ልብ-ወለድ ድርሰቶች ናቸው። እንደዚሁም ደግሞ ስምንት ያህል የትርጉም ስራዎችን አሳትመዋል። ሶስት ኢ-ልብወለድ መጽሐፎችንም ጽፈዋል።
እኝህ ሰው የ84 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አንጋፋው የስነ-ጽሑፍ ሊቅ፣ ደራሲ እና ተርጓሚ “ሳሕለ ሥላሴ ብርሃነ ማሪያም” ናቸው። ደራሲ ሳህለ ስላሴ ብርሀነ ማሪያም የተወለዱት በአሁኑ የጉራጌ ዞን እምድብር በሚባለው ታዋቂ አምባ ነው። ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት በዚያው በእምድብር ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል። በትምህርቱ ዓለም እንደ ተስፋዬ ገሰሰ እና ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ከመሳሰሉት ታዋቂ የጥበብ ሰዎች ጋር ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አብረው ቆይተዋል።
ጋሽ ሳህለ-ሥላሴ ብርሃነ ማሪያም የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚጽፉ የአፍሪቃ ደራሲዎችን ለማስተዋወቅ በቀየሰው “African Writers Series” የተባለ ባለ ብዙ ቅጽ የአጫጭር ልብ-ወለድ ድርሰቶች መድብል ውስጥ ጽሑፋቸው ከታተመላቸው ሁለት የኢትዮጵያ ደራሲዎች አንዱ ነበሩ (ሌላኛው ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ነው)። ለኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጥቶት በ1994 በተካሄደው የኪነ-ጥበባት እና መገናኛ ብዙኃን ሽልማት መድረክ ላይ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል። የወልቂጤ ይኒቨርሲቲም ውለታቸውን አስታውሶ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶአቸዋል፡፡
—-
ደራሲና ተርጓሚ ሳህለ ስላሴ ብርሀነ ማሪያም ልዩ አድናቆትን ያተረፉት በተለይ በትርጉም ስራዎቻቸው ነው። በአማርኛ ቋንቋ ከተረጎሟቸው ስራዎች መካከል የቻርለስ ዲከንስ ተወዳጅ ድርሰት የሆነው “A Tale of Two Cities (“የሁለት ከተሞች ወግ”) እና የቪክቶር ሁጎ ምርጥ ስራ የሆነው “Les Miserables” (መከረኞች) በጣም የገነኑ ናቸው። በተለይም “መከረኞች”ን በቀጥታ ከፈረንሳይኛው መጽሐፍም የተረጎሙት በመሆኑ ከኦሪጅናሌው ጋር በጣም እንደሚመሳሰል ሁለቱንም ቋንቋዎች የሚናገሩ የስነ-ጽሑፍ ሰዎች ይመሰክራሉ። ጋሽ ሳህለ ሥላሴ ስለትርጉም ስራዎቻቸው ሲናገሩ “Classic የሆኑ ሥራዎችን ነው ለትርጉም የምመርጠው፡፡ አንድ መጽሐፍ በሚሊየን ቅጂ ስለተሸጠና ታዋቂ ስለሆነ ብቻ መርጬ አልተረጉመውም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስፈልጋሉ እንዲሁም ትምህርት ይሰጣሉ የምላቸውን ነው የምተረጉመው” ብለው ነበር።
ጋሽ ሳህለ ሥላሴ ከጻፏቸው ወጥ ልብ ወለድ ድርሰቶች መካከል ‘የሺንጋ ቃያ’ የተሰኘው የጉራጊኛ ቋንቋ ልቦለድ የበኩር ሥራቸው ሲሆን ‘ባሻ ቅጣው’፣ ‘ሹክታ’፣ ‘The Afersata’ እና ‘Warrior King’ የተሰኙት መጽሐፎቻቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ።
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 8/2015

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe