“ስለ ብሔራዊ ጥቅም የማያገባው የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ የለም” ዶክተር ለገሰ ቱሉ

ትኩረቱን በሚዲያ ላይ ያደረገውና በጎንደር ከተማ የተካሄደው ዘጠነኛው የኢፕድ የፓናል ውይይት ሶስት የመወያያ ጽሁፎች ቀርበውና ሠፊ ውይይት በተሳታፊዎች ተደርጎበት ተጠናቋል።
ውይይቱን የመሩት የመንግስት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በማጠቃለያ ንግግራቸው፤
“ስለ ብሔራዊ ጥቅም የማያገባው የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ የለም” ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅም ሲባል ብዥታ መፈጠር የለበትም፤ ብሄራዊ ጥቅም የወንድማማችነትና የአንድነት ጉዳይ ነው፤ በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፓለቲካ መሥኮች ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው በጋራ የሚቆሙበት ጉዳይ ነው፤ ከዚህ አንጻር ማንኛውም ሚዲያ ይሄንን በውል ተረድቶ መሥራት ይገባዋል ብለዋል።
በየትኛውም ዓለም ያለ ሚዲያ ለተመሰረተበት አገርና ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም ይወግናል ያሉት ዶክተር ለገሰ፤ መንግሥትና ሚዲያውም በዚህ ልክ ተግባብተው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር መሥራት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የትኩረት መጠኑ መለያየት ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ሚዲያ ለብሔራዊ ጥቅም ይሠራል፤ መስራትም ይገባዋል። የሁሉም ጥቅም የሚከበረው ሁሉም ሲሳተፍ ነውና።
ሚዲያ ዜና ከማምረት በላይ ተልዕኮ እንዳለው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ መረጃን ከመስጠት ባሻገር ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ የሚያደርጉ እሴቶችን መኮትኮትም አለባቸው ብለዋል።
የሚዲያ ነጻነት ሲባል እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ነው መታየት ያለበት ያሉት ዶክተር ለገሰ፤ በአሜሪካም በአውሮፓም ያለው ነጻነት እንደራሳቸው ባህልና ፓለቲካል ኢኮኖሚ የተቃኘ ነው፤ ስለዚህ የእኛም አገር የሚዲያ ነጻነት በራሳችን ባህልና አውድ ልክ መታየት አለበት ሲሉ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው በሰጡት የማጠቃለያ ንግግር፤ የሳይበር ሚዲያው ማደግን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዴት ልንጠቀምበት ይገል ብሎ ማሰብ ያሥፈልጋል፤ ይህ እድገት ኢንቨስትመንትም መሆኑን አምነን መሥራትም ይጠበቅብናል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት “ማህበራዊ ሚዲያ አደገኛ ነው” እያሉ መቀመጥ አይጠቅምም ያሉት አቶ መሀመድ፤ ዘመኑ ለደረሰበት ደረጃ የሚመጥን ፓሊሲና ስትራቴጂ በማዘጋጀት ዘርፉን መምራት ይገባል ሲሉም ነው ያስታወቁት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህሯ ዶክተር አጋረደች ጀማነህ በበኩላቸው፤ መረጀን በፍጥነት ለህዝብ ማድረስ ከሚዲያዎች ይጠበቃል፤ ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የኮምንኬሽን ቢሮዎች መረጃን ቶሎ ቶሎ መስጠት ሲችሉ በመሆኑ ይህንን ሃላፊነት መወጣት ይገባል ብለዋል።
“የሚዲያ ነጻነት ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ነጻነት ያለገደብ ሊሆን አይችልም” ያሉት ዶክተር አጋረደች፤ ትልልቅ አገሮች ላይ ያለው ተሞክሮም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ነጻነት ሁልጊዜም በኃላፊነት ውስጥ መሆን አለበት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነት መምህሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ጠንካራ ሚዲያ መኖር የጠንካራ መንግሥት መገለጫ ነው፤ ስለዚህ መንግሥት የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች እንዲጠናከሩ አብክሮ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።
መንግስት ሚዲያን ባፈነ ቁጥር የገደል መሚቶ ይሆናል ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ሚዲያዎችም የጋዜጠኝነት ሙያ በሚጠይቀው ልክና አግባብ ሥራቸውን መሥራት አለባቸው፤ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ዓለም ከደረሰበት መድረስ ይቻላል ቀላል ነውና ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ ዛሬ በተካሄደው የኢፕድ ዘጠነኛው የፓናል ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ብዝኃነቶች አሉ። ሚዲያዎችም ይሄንን አውቀውና አክብረው መሥራት ይኖርባቸዋል።
በርካታ ብዝሃነት ያለበት አገር ነው ያለን ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፤ ይህ በሆነበት አገር ላይ የሚተላለፉ ነገሮች ይሄንን ታሣቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe