ሶስት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ በሀገር በቀል ሲቪክ ድርጅት የሚሰጥ ዓመታዊ ሽልማትን አሸነፉ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል “የዓመቱ ምርጥ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሽልማትን” ለሶስት ኢትዮጵያውያን አበረከተ። ሶስቱ አሸናፊዎች የተመረጡት፤ በትግራይ፣ በአማራ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ላሉ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች እና የተገለሉ ማህበረሰቦች ሰብዓዊ መብት መከበር እያከናወኗቸው ባሉ ስራዎች መሆኑን ማዕከሉ ገልጿል። 

ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፤ “የዓመቱ ምርጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን” መርጦ ሲሸልም የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ማዕከሉ የተመሰረተበትን ሶስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ትላንት ማክሰኞ ጥር 21፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ ስነ ስርዓት፤ ወ/ሮ ገነት ኪዳነ፣ ወ/ሮ ትጥቅነሽ ዓለሙ እና አቶ አርጋው አየለ የተባሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

ከተሸላሚዎቹ አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ገነት፤ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ሴቶች ያጋጠሟቸው ችግሮች እንዲቀረፉ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማቱ እንደተበረከተላቸው ተገልጿል። እኚሁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፤ በክልሉ ላሉ አካል ጉዳተኛ ሴቶች የሚሰጠው ህክምና “በተፈለገው ልክ ያለመሆኑን” ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ “ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ እና አገልግሎቱ በስፋት እንዲዳረስ” ማድረጋቸውን ማዕከሉ ጠቅሷል።

በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች በመጠለያ ካምፖች የሚደረገው የአስቸኳይ እርዳታ ስርጭት፤ ለአካል ጉዳተኞችም “በእኩል ተደራሽ እንዲሆን” ከሌሎች አጋር ማህበራት ጋር በመሆን ጥናት በማካሄድ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ እና እንዲሻሻል ማድረጋቸው ተመልክቷል። በትግራይ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር ላለፉት 20 ዓመታት ያገለገሉት ወ/ሮ ገነት፤ አካል ጉዳተኞች “ያለዋስትና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በመታገል እና ለውጥ በማምጣት” የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑም ተነግሮላቸዋል።

በአማራ ሴቶች ማህበር በፕሮጀክት አስተባባሪነት ያገለገሉት ወ/ሮ ትጥቅነሽ ዓለሙ፤ ሌላኛዋ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዓመታዊ ሽልማት አሸናፊ ናቸው። ወ/ሮ ትጥቅነሽ በአማራ ክልል ያሉ ሴቶች መብቶቻቸው እንዲከበር መታገላቸውን የገለጸው ማዕከሉ፤ ጾታ ተኮር የሆኑ ጥቃቶች “የበለጠ ትኩረት እንዲያገኙ” መስራታቸውን አስታውቋል።

በክልሉ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች “ተገቢ ፍትህ እንዲያገኙ” እንደዚሁም “የመልሶ ማቋቋም እና መሰል ድጋፎችን” የሚያገኙበትን ዕድል የማመቻቸት ኃላፊነት ተወጥተዋል ተብሏል። በአማራ ክልል በስፋት የሚፈጸመው የልጅነት ጋብቻን በመከላከል ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦም በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ተወስቶላቸዋል። በሸላሚ ድርጅቱ  መረጃ መሰረት ወ/ሮ ትጥቅነሽ የ843 የሴት ህጻናት ጋብቻ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

ወ/ሮ ትጥቅነሽን ለሽልማት ካበቋቸው ሰራዎች አንዱ፤ በወሊድ ምክንያት በእናቶች ላይ የሚከሰተው የፊስቱላ ችግር ተጠቂዎች ህክምና የማግኘት መብታቸው እንዲከበር ያደረጉት ጥረት መሆኑ ተጠቅሷል። በዚህም ጥረታቸው ከ2000 በላይ የፊስቱላ ተጠቂ እናቶች ህክምና እንዲያገኙ ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ገልጿል። ሴቶች የውሳኔ ሰጭነት አቅማቸው እንዲጎለብት እና በየደረጃው ባሉ እርከኖች ተሳትፎአቸው እንዲጨምር በማገዝ ረገድም ወ/ሮ ትጥቅነሽ ሚና እንደነበራቸው ማዕከሉ አክሏል።

ከ18 አመት የአውሮፓ እና የአሜሪካ የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ “አቤኔዘር ሰፖርቲቭ ዴቬሎፕመንት አሶሴሽን” የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት የመሰረቱት አቶ አርጋው አየለ፤ የዘንድሮው “የዓመቱ ምርጥ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሽልማትን” ያሸነፉ ሶስተኛ ሰው ሆነዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸውን የጀመሩት በሐመር ብሔረሰብ አባላት ዘንድ ጥቃት የሚደርስባቸውን “የሚንጊ ህጻናት በመታደግ” እንደሆነ ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በሐመር ብሔረሰብ አባላት ዘንድ “የአንድ ህጻን ልጅ የታችኛው ጥርስ ቀድሞ ከበቀለ፤ ልጁ ወይም ልጅቱ የተረገመ ነው ወይም ነች” የሚል እምነት አለ። በዚህ እምነት መሰረትም፤ በዚህ መልክ የተወለዱ ህጻናት እስከ መገደል የደረሰ ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይቷል። አቶ አርጋው “በተሳሳተ አመለካከት ብቻ መሰረታዊ በህይወት የመኖር መብታቸውን የሚያጡትን የሚንጊ ህጻናትን በመታደግ”፤ በበጎ አድራጎት ማዕከል እንዲጠለሉ እና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ሲያደርጉ መቆየታቸው በበጎ ስራነት ተጠቅሶላቸዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹን ለዘንድሮው ሽልማት ያሳጫቸው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙት የባጫ ማህበረሰብ አባላት “የመኖር እና የመማር እድል እንዲያገኙ” ባደረጉት “ከፍተኛ ጥረት” መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታውቋል። ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ በታች እንደሆነ የሚነገርላቸው የባጫ ማህበረሰብ አባላት፤ ከአጎራባቾቸው የሱርማ እና ቦዲ ማህበረሰብ አባላት “ከፍተኛ ጥቃት” የሚደርስባቸው መሆኑን ማዕከሉ አስታውሷል።

“ማንነታቸው እና ቋንቋቸው ለመጥፋት ተቃርቧል” የተባለላቸው የባጫ ማህበረሰብ አባላት ያለባቸው ችግር እንዲታወቅ እና ጉዳዩም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ደርሶ መፍትሄ እንዲያገኙ አቶ አርጋው ከፍተኛ ሚና መወጣታቸውን ማዕከሉ ገልጿል። በዚሁ ክልል የሚገኙት እና በአካባቢያቸው ባለው ህዝብ ሲገለሉ ለቆዩ “የመንጃ ማህበረሰብ” አባላት የመማር ዕድል እንዲያገኙ ማድረጋቸውም እንዲሁ በማዕከሉ ተነስቷል።

“ውስብስብ ማህበራዊ ችግሮች ሁሉ ለመፍታት ቁልፉ ያለው ሰላም ላይ ነው” የሚል እምነት ያላቸው አቶ አርጋው፤ በዚሁ ዙሪያ የሚሰራ “ግሎባል ፒስ ባንክ” የተሰኘ ማህበር ባለፉት ዓመታት ማቋቋማቸውም በሸላሚው ድርጅት ዕውቅና እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። “ግሎባል ፒስ ባንክ” አብረው የሚኖሩ ማህበረሰቦችም ሆነ ግለሰቦች “እንዲቀራረቡ እና እንዲነጋገሩ የማድረግ” ዓላማ ያለው ማህበር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)   

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe