ሶስት የአዉሮጳ ሐገራት ለፍልስጤም የመንግሥትነት ዕዉቅና ሰጡ

ኖርዌይ፣ ስጳኝና አየርላንድ ለፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር የመንግሥትነት ዕዉቅና እንደሚሰጡ አስታወቁ።የሶስቱ የአዉሮጳ ሐገራት መሪዎች ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓት ግን በየፊናቸዉ እንዳስታወቁት ለፍልስጤም የመንግስትነት ዕዉቅና መስጠት በአካባቢዉ ሠላም ለማስፈን ይጠቅማል።እስራኤል ርምጃዉን አጥብቃ ተቃዉማለች።
የአየርላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ሲሞን ሐሪስ ዛሬ ለሕዝባቸዉ ባደረጉት ንግግር «ለፍልስጤምና ለአየርላንድ ታሪካዊና ጠቃሚ ዕለት» ብለዉታል።ፍልስጤሞች ለነፃነት የሚያደርጉትን ትግልም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ አየርላንድ ከ100 ዓመት በፊት ለነፃነት ካደረገችዉ ትግል ጋር አመሳስለዉታልም።
የኖርዌይ ጠቅላይ ሚንስትር ዮናስ ጋሕር ስቶሬ በበኩላቸዉ የሶስቱን ሐገራት ዉሳኔ ሌሎች ሐገራትም ይከተላሉ የሚል ተስፋ አንዳላቸዉ አስታዉቀዋል።ጠቅላይ ሚንስር ስቶሬ አክለዉም «በብዙ አስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉና የቆሰሎበት ጦርነት በሚደረግበት በዚሕ ወቅት ለፍልስጤምና ለእስራኤል እኩል ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችለዉን ብቸኛዉን -ጎን ለጎን በሰላምና በደሕንነት የሚኖሩ የሁለት መንግስታትን አማራጭ በሕይወት ማቆየት አለብን።» ብለዋል።
የስጳኝ ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በፋንታቸዉ ማድሪድ ዉስጥ ለተሰየመዉ ለሐገራቸዉ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን «ለፍልስጤም የሰላም ፕሮጀክት አይከተሉም» ብለዋል።ሳንቼዝ አክለዉም «ኔታንያሁ የፍልስጤም ሠላማዊ ሰዎችን «በረሐብና ሽብር እየቀጡ ነዉ» በማለትም የእስራኤሉን መሪ ወቅሰዋል።ሳንቼዝ ከዚሕም በተጨማሪ «እስራኤል ላይ ከደረሰዉ ጥቃት በኋላ «አሸባሪዉን ቡድን ሐማስን መዉጋት ተገቢ ነዉ» ብለዋል።ይሁንና «ጋዛና በሌላዉም የፍልስጤም ግዛት የደረሰዉ የከፋ ሕመም፣ጥፋትና ስቃይ የሁለት መንግስታት መፍትሔን ለአደጋ፣ ለከፋ አደጋ ማጋለጡ በግልፅ እየታየ ነዉ።» አከሉ የስጳኝ ጠቅላይ ሚንስትር።
ስጳኝ፣ እስራኤል በጋዘ ሠርጥ የከፈተችዉን ወታደራዊ ዘመቻ አጥብቀዉ ከሚቃወሙ ጥቂት የአዉሮጳ ሐገራት አንዷ ናት።ግራ ዘመሙ የስጳኝ መንግስት ካለፈዉ ጥቅምት ጀምሮ ለእስራኤል ጦር መሳሪያ መሸጥ አቁሟል።
የእስራኤልና የፍልስጤም አፀፋ
እስራኤል የሶስቱን ሐገራት ዉሳኔ አጥብቃ ተቃዉማዋለች።የእስራኤል ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር የስጳኙ ጠቅላይ ሚንስትር መግለጫ ከመሰማቱ በፊት ኖርዌና አየርላንድ የሚገኙ አምባሳደሮቹ ወደ ሐገራቸዉ እንዲመለሱ ጠርቷል።የእስራኤል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እስራኤል ካትዝ «እነዚሕ ሐገራት ለፍልስጤም የመንግስትነት ዕዉቅና በመስጠታቸዉ ለአየርላንድና ለኖርዌ ግልፅና የማያሻማ መልዕክት አስተላልፋለሁ።» ብለዋል።የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት (PLO) የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሑሴይን አል ሺይክ በX (የቀድሞዉ ትዊተር) ባሰራጩት መልዕክት ሶስቱን ሐገራት አመስግነዉ ዉሳኔዉን «ለነፃዉ ዓለም፣ ታሪካዊ» ሁኔታ ብለዉታል።
ከዚሕ ቀደም ዕዉቅና የሰጡና ያልሰጡ ሐገራት
የጀርመኑ ዜና አገልግሎት (DPA) እንደዘገበዉ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አብዛኞቹ ለፍልስጤም የመንግስትነት ዕዉቅና ሰጥተዋል።ዩናይትድ ስቴትስ፣ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ጀርመንን የመሳሳሉ ኃያል ምዕራባዉያን መንግስታት ግን እስካሁን ዕዉቅና አልሰጡም።ጀርመን »የሁለት መንግስታት መፍትሔ» የሚባለዉን ሐሳብ ትደግፋለች።ይሁንና መፍትሔዉ ገቢር መሆን ያለበት በእስራኤልና በፍልስጤም ስምምነት ብቻ መሆን አለበት ባይ ናት።
ዛሬ ለፍልስጤም የመንግስትነት እዉቅና ለመስጠት ከወሰኑት ስጳኝና አየርላንድ የአዉሮጳ ሕብረት አባላት ናቸዉ።ኖርዌይ ግን የሕብረቱ አባል አይደለችም።ከአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መካከል ስዊድን የዛሬ 10 ዓመት ግድም ለፍልስጤም የመንግሥትነት ዕዉቅና ሰጥታለች።ዛሬ ዕዉቅና ለመስጠት የወሰኑት ሶስቱ ሐገራት እንዳስታወቁት ዕዉቅናዉ በመጪዉ ሳምንት ማክሰኞ ገቢር ይሆናል።
SourceDW

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe