” ሸኔ ነሽ ” በሚል ሴት የደፈረው የፖሊስ አባል 7 ዓመት እስር ተፈረደበት

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን፤ ሱሮ ባርጉዳ ወረዳ ውስጥ የፖሊስ አባል የሆነ ግለሰብ (ስሙ ፦ ኮንስታብል ገነሜ ኮንሶ) አንዲት ሴትን ‘ሸኔ’ ነሽ ብሎ በማስፈራራት በመድፈሩ የ7 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ በዳኔ ደንቦቢ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል።

ዳኛ በዳኔ ደንቦቢ ምን አሉ ? ” የግል ተበዳይ (ስሟን ለመጠበቅ አልተገለፀም) ፤ ወንጀሉ የተፈጸመባት ደምቢ ሶሮ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 ላይ ከሌላ ሴት ጋር ከቤቷ በወጣችበት ወቅት ነው።

የግል ተበዳይዋ ከሌላ ሴት ጋር ሆና ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው መጸዳጃ ቤት ጋር ሲደርሱ በስፍራው የነበረው ተከሳሽ የፖሊስ አባል ያስቆማቸዋል።

በዚህ ለሊት ወደየት ነው የምትሄዱት ? በምሽት መንቀሳቀስ ክልክል ስለሆነ የቅጣት 200 ብር አምጡ በማለት የመድፈር ወንጀሉን ከመፈጸሙ በፊት ገንዘብ ለመቀበል ሙከራ አድርጎ ነበር።

ሁለቱ ሴቶች ገንዘብ እንደሌላቸው ሲመልሱለት ‘ኦነግ ሸኔ’ ናችሁ የሚል ሌላ ክስ ማቅረብ ጀመረ።

ለቅጣት ያለውን ገንዘብ እንደማያገኝ ሲረዳ ‘እናንተ ኦነግ ሸኔ ናችሁ። ኦነግ ሸኔ ያለበትን ቦታ ስለምታውቁ ከዚያ ነው የምትመጡት’ በማለት ተቆጣ። ተበዳዮቹም ሸኔ ናችሁ በመባላቸው ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ገቡ።

የጦር መሳሪያ ደቅኖባቸው ‘እገድላችኋለሁ’ ብሎ አስፈራርቶ ወደ ጢሻ ይዟቸው ገባ። ወደ ሰዋራ ቦታ ከወሰዳቸው በኋላም አንደኛዋን ‘ቁጭ በይ ድምጽሽን እንዳታሰሚ’ በማለት ካስፈራራ በኋላ፣ ባለትዳር የሆነችውን ሌላኛዋን ሴት ደፈረ።

ሚስቱ ወደ ውጪ ወጥታ የቆየችበት የተበዳይ ባለቤትም ሚስቱን ፍለጋ ሲወጣ፣ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቦታ ደርሶ አግኝቷታል።

ተከሳሽ ኮንስታብል ገነሜ በሱሮ ባርጉዳ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ወንጀሉን አልፈጸምኩም ብሎ ቢከራከርም፣ ለቀረበበት ክስ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም።

የግል ተበዳይን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ተቀብሏል።

ተከሳሽ ኮንስታብል ገነሜ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 620/1 መሠረት ጥፋተኛ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

አንድ ተከሳሽ በኃይል ወይም በመሳሪያ አስፈራርቶ የመድፈር ወንጀል ከፈጸመ ከ5 አስከ 15 ዓመት እስር ያስቀጣል። ወንጀሉ ሲፈጸም በተበዳይ ላይ የደረሰ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት እንደሌለ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈጽሞ እንደማያውቅ እና ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የ7 ዓመት እስር ተፈርዶበታል። ”

via  ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe