ሼኸ መሐመድ አላሙዲ ተከሰሱ!!

ቦሌ መንገድ ላይ የሚገኘው ቦሌ ታወርስ ህንጻ የክሱ አብይ ምክንያት ነው ተብሏል

የሜድሮክ ኢንቨስትመት ግሩፕ ባለቤት እውቁ ባለሀብት ሼኸ መሐመድ አላሙዲ በረዥም ጊዜ የንግድ ሸሪካቸው በአቶ አብነት ገ/መስቀል መከሰሳቸው ተሰማ፤

ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ልደታ ምድብ የፍትሐብሔር ችሎት የቀረበው የአቶ አብነት ገ/መስቀል ክስ የ640  ሚሊዮን ብር አቤቱታ ሲሆን ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ቦሌ ታወር  ተብሎ ከሚጠራው ህንፃ ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው፤

አቶ አብነት ገ/መስቀል በጠበቃቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ክስ ላይ እንዳመለከቱት ቦሌ ታወርስ የተባለውን ህንጻ ለመገንባት እሳቸውና ተከሳሹ ሼኸ አላሙዲ ቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/ጠግ ማህበር የተሰኘ ድርጅት በ1994 ዓ.ም አቋቁመዋል፤ የዚህ ድርጅት ካፒታል 10 ሚሊዮን ሆኖ መቋቋሙን የሚገልፀው ክሱ የአክሲዮን ድርሻን በተመለከተ ሼኸ መሐመድ አላሙዲ 60 ከመቶ፤  አቶ አብነት ደግሞ 40 ከመቶ አክሲዮን ድርሻ መያዛቸውን ክሱ ያብራራል፤ የድርጅቱ የካፒታል መጠን በ2010 ዓ.ም ወደ 545 ሚሊዮን ብር ሲያድግም ሁለቱም ወገኖች በአክሲዮን ድርሻቸው ልክ መዋጮቸውን መክፈላቸውን በክሱ ላይ ተመልክቷል፤

ድርጅቱ ከተሰማራባቸው የንግድ ዘርፎች መሀከል አንዱ ለተለያዩ  አገልግሎቶች የሚውል ህንፃ መገንባት በመሆኑ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ክልል ወስጥ በከሳሽ ስም የተመዘገበ ስፋቱ 5189 ሜትር ካሬ  የሆነ  በ1992 እና በ1997 ዓ.ም በህግ አግባብ በሊዝ የወሰዱትን የገዛ መሬታቸውን ለግንባታው በነፃ መስጠታቸውን ይገልጻል፤  ይህንን ያደረግሁት ከተከሳሽ ጋር ባለን የቆየ የንግድ ግንኙነትና ከፍ ያለ መተማመን ነው ይላሉ አቶ አብነት፤

የድርጅቲ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ህንጻውን ሲያሰሩ መቆየታቸውን በክስ ማማልቻው ላይ የጠቀሱት አቶ አብነት እስከ 7ኛ ፎቅ ድረስ ህንጻውን ለማድረስ ከራሳቸው ኪስ ብር 215 ሚሊዮን 545 ሺ 367 ብር ከ26  ሳንቲም ማውጣታቸውን ይህም በተከሳሽ በኩል የሚታወቅ መሆኑን ይጠቅሳሉ፤

ይህም ገንዘብ ለህንፃው ግንባታ በቂ ሆኖ ስላልተገኘ አቶ አብነት በተከሳሹ ይሁንታ ከዳሸን ባንክ ብር 400 ሚሊዮን ብር በተለያየ ጊዜ በድርጅቱ ስም መበደራቸውንና ለህንጻው ግንባታ ማዋላቸውን አመልክተዋል፤

አቶ አብነት ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ ለህንጻው ግንባታ ያወጣሁት የግሌ ገንዘብ 215 ሚሊዮን ብር ከሳሽ ሊመልሱልኝ ይገባል አልያም ወደ አክሲዮን ድርሻ ተቀይሮ የአክሲዮን ድርሻዬ እንዲያድግልኝ ፍርድ ቤቱ ይሰወስንልኝ የሚል ሲሆን ከዳሸን ባንክ በድርጅቱ ስም ፈርመው የተበደሩትንና ለህንጻው ግንባታ ውሏል ያሉትን 425 ሚሊዮን ብር የድርጅቱ የጋራ ወጪ ተደርጎ ይቆጠርልኝ አልያም በድርጅቱ ባለን የጋራ የአክሲዮን ድርሻ መጠን የካፒታል  መዋጮ ሆኖ ይወሰንልኝ በማለት በድምሩ የ 640 ሚሊዮን 545 ሺ 367 ብር ከ26  ሳንቲም ክስ ነው ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት፤

ህንፃው በአሁኑ ጊዜ ተጠናቆ እየተከራየ ለማህበሩ ከፍ ያለ ገቢ እያስገኘ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አብነት ከላይ ከተጠቀሰው ወጪ ከሆነው የግል ገንዘባቸው በተጨማሪም ለህንፃው ማስጨረሻ የሚሆኑ የማጠናቀቂያ እቃዎችን ከጣሊያን ሀገር በግል ገንዘባቸው ማስመጣታቸውን በመግለፅ የዚህን ወጪ ዝርዝር ለጊዜው ስለማላውቀው ሰነዶችን አሰባስቤ እንዳቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጠልኝ ብለዋል ፤

ክሱ በጠበቃቸው በኩል የደረሳቸው ሼኸ መሐመድ አላሙዲ ጠበቆች ምላሻቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ለየካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል፤

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe