በታላቁ ህዳሴ ግድብ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ የአየር ክልል ለማንኛውም የአየር በረራ የተከለከለ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሎኔል) ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚገነባበት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ የአየር ክልል ከማንኛውም ዓይነት የበረራ እንቅስቃሴ ዝግ እንዲሆን፣ ከሚመለከታቸው የደኅንነት አካላት ጋር በመወያየት ክልከላ ተጥሎበታል።
በመሆኑም የንግድ ወይም የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላኖችም ሆኑ ሌሎች ዓይነት የበረራ እንቅስቃሴዎች፣ ግድቡ በሚገኝበት አካባቢ መከናወን እንደማይችሉ ገልጸዋል። ይህ ቢሆንም የሚመለከተው አካል በሚሰጠው ልዩ ፈቃድ ብቻ በተከለከለው የአየር ክልል በረራ እንዲደረግ ሊፈቀድ እንደሚችል አስረድተዋል። የአገርን ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲህ ዓይነት ክልከላዎችን መጣል በዓለም አቀፍ አሠራር የተለመደ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያም የግድቡን ደኅንነት ለማረጋገጥ ሰትል ይህንን ክልከላ መጣሏን ገልጸዋል። ክልከላውን ከመጣሉ በፊትም ከአየር ኃይልና ከሌሎች የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር ምክክር ተደርጎ የተፈጸመ እንደሆነ፣ ክልከላው ተግባራዊ መደረግ የጀመረውም ከወራት በፊት በ2012 ዓ.ም. ውስጥ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚቃጣን ጥቃት ለመከላለከል የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት መኖሩንና በግድቡ ላይ የአየር ጥቃት ይሰነዝራል የሚል ሥጋት ፈጸሞ እንደማያሳስብ፣ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ቀድም ሲል ባካበተው ልምድ ላይ ዘመናዊ ትጥቆችን በማከል ራሱን በጥሩ ሁኔታ አደራጅቶ የአገሪቱን የአየር ከልል፣ በተለይም ለህዳሴ ግድቡ የ24 ሰዓት ልዩ ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አየር ኃይሉ ሙሉ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቁት ሌተና ጄኔራሉ፣ ከአራት ሰዓት በላይ በአየር ላይ መቆየት የሚችሉ ጄቶችን መታጠቁንም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአየር እንቅስቃሴ ቅኝትን በተመለከተ ማንኛውንም የአየር እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል ከመግባቱ 400 ኪሎ ሜትር የአየር ርቀት ላይ ሳለ፣ ሙሉ በሙሉ መለየት የሚያስችል ራዳር አየር ኃይሉ መታጠቁንም ተናግረዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል ከመግባቱ ከ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለን የአየር እንቅስቃሴ፣ የበረራ ከፍታውን፣ የበረራ ፍጥነቱን፣ እንዲሁም የበረራውን ዓይነት ማለትም የመንገደኞች ይሁን የጦር እንቅስቃሴ መለየት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ምንጭ፡ ሪፖርተር