«በሕዝባችን ለመዳኘት ዝግጁ ነን!» በለጠ ሞላ የአብን ሊቀመንበር

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ የንቅናቄውን የምርጫ ዝግጅትና መሰል ጉዳዮች በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፤ እኛም ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
1. በቀጣዩ ምርጫ የትሕነግ አለመኖርን በተመለከተ፦
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ የትህነግ አለመኖር ለኢትዮጵያ አንዱ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ ወደፊት የተሻለች ሁሉም ዜጎች በእኩልነትና በወንድማማችነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመገንበት ትሕነግን መሰል የሕዝብ ጠላት የሆነ ድርጅት መክሰሙ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ ነው፡፡ ሆኖም ይሄ ብቻ ግብ ሊሆን ስለማይችል መጪው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታአማኔ እንዲሆን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል::
2. ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ፦
አብን በምርጫው ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ሰፊ ዝግጅት እያደረግን ሲሆን በምርጫው ሕዝባችንን የሚመጥኑ ብቁ እጩዎችንና አማራጭ የፖሊሲ ኃሳቦችን በማቅረብ አሸናፊ ለመሆን «ጊዜው አሁን ነው!» በሚል መሪ ቃል እየሰራን ነው፡፡ በቀጣም ቀሪ ስራዎችን በምርጫ ቦርድ ሰሌዳ መሰረት ለመከወን ሰፊ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ምርጫውም እስከአሁን ከነበሩት በተለዬ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታአማኒ እንዲሆን መንግስት እንደ መንግስት እኛም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ኃላፊነታችንን በምን አግባብ ነው መወጣት ያለብን የሚለውን አስበንበትና ተጨንቀን መስራት ይኖርብናል፡፡ እኛ የነገዋንና ሁሉም ዜጎች እናቴ ብለው የሚቀበሏት አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እያስብን መስራት አለብን የሚል እንደ ፓርቲ ፅኑ አቋም አለን፡፡ ሕዝቡም በሰከነ መንፈስ ምርጫው ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ እንዲሆን ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ ድኅረ ምርጫ ሚናውን መወጣት ይኖርበታል::
የምርጫው ውጤት ተዓማኒና ቅቡልነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ሚናውን መወጣት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመሰረታዊነት ጥያቄዎቻቸው በሁሉም መስክ ሊታረቁ የሚችሉ ባይሆኑ እንኳ ሊህቃኑ ሆደ ሰፊ ሆነው አንዱ ሌላውን ለማዳመጥ፤ ለመገንዘብና ለመመካከር ብሎም ለሰጥቶ መቀበል ዝግጁነቱና ቀናነቱ ካለ ልዩነቶች ቢኖሩም አንድ ሊያደርጉን የሚችሉ ብዙ ነገሮች መኖራቸው መታወቅ አለበት ብለዋል:: ይህ ሲሆን ሁላችንም እንደሕዝብ አሸናፊ እንሆናለን ብለን እናምናለን፡፡
3. የፖለቲካ ምህዳሩን በተመለከተ፦
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር ወጥ የሆነ መልክ የለውም፤ ምህዳሩ ሰፊ ወይም ጠባብ ነው ለማለት ያስቸግራል:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ እኛ በይፋ የምንቀሳቀስባቸው፣ ፖለቲካ የምንሰራባቸው፣ በነፃነት ሕዝባችንን የምናደራጅባቸው እና መዋቅሮቻችንን የዘረጋንባቸው አካባቢዎች አሉ:: ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢዎች የተወሰኑ ውስንነቶች ማለትም የታችኛው የመንግስት መዋቅር በፈለግነው ልክ እንዳንቀሳቀስ መሰናክል የሚፈጥር ቢሆንም የማደራጀትና ንቅናቄን የመፍጠር ስራዎችን በነጻነት እንስራለን፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ከእዚህ አንጻር ካየነው ሰፍቷል ልንል እንችላለን:: ነገር ግን በሌሎች አካባቢዎች መዋቅሮች ኖረውን የፖለቲካ ስራ ብንሰራም በአካባቢዎቹ በይፋ የመንቀሳቀስ መብታችን በእጅጉ የተገደበባቸው፣ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን የሚንገላቱባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ወጥ መልክ የሌለው የፖለቲካ ምህዳር ያላት አገር ናት ለማለት ያስደፍራል::
በአጠቃላይ ምህዳሩ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በሁሉም አካባቢ ምቹና አስቻይ መሆን አለበት፤ ይህ እንዲሆንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብረን እንሰራለን፡፡ ጊዜው በሕዝብ ይሁንታ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ብሎም ተዓማኒ ምርጫ ሥልጣን የሚያዝበትና አገርና ሕዝብን የምናገለግልበት ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከኖርንበት የሴራና የጥላቻ ፖለቲካ መፋታትና ሥልጡን ፖለቲካ ማራመድ ይኖርብናል፡፡ ከዚያ ዳኝነቱን ለሕዝባችን መስጠትና ውጤቱን በፀጋ መቀበል የሁላችንም ግዴታና ኃላፊነት ነው፤ እኛ በሕዝባችን ለመዳኜትና ውጤቱንም በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ መጠፋፋትና የሕዝባችንን መከራ ማራዘም ብሎም ካለፉት የውድቀት መንገዶች አለመማር ነው፡፡
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe