በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ታገደ

በሕገ-ወጥ መንገድ የተሰበሰበ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ የውጭ ምንዛሪ መታገዱን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

መንግስት በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ባንኮች በውጭ አገራት ገንዘብ የሂሳብ ደብተር የሚከፍቱበትን የዲያስፖራ አካውንት ሕግና የአሠራር ስርዓት በመጣስ የተለያዩ ግለሰቦች በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባካሄደው ክትትል ማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል።

በዚሁ መሠረት አገልግሎቱ እስካሁን ባደረገው ክትትል፣ የትንተናና ማጣራት ሥራዎች 85 ግለሰቦች የተሰታፉበት እና መጠኑ 20,226,583 ዶላር (ሃያ ሚሊየን ሁለት መቶ ሃያ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰማኒያ ሶስት ዶላር) የውጭ አገር ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ በማድረግ ለወንጀል ምርመራ መተላለፋን አስታውቋል።

ወንጀሉ የተፈፀመው የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችንና የማጭበርበር ስልቶችን በመጠቀም ሲሆን ከነዚህም መካከል አንደኛ ውጭ አገር ሳይሄዱ ውጭ አገር ሄደው የተመለሱ በማስመሰል ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በማቅረብና በመጠቀም፣ ሁለተኛ ከውጭ አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው በመግባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው እንደገቡ በማስመሰል ቀሪውን በህገ-ወጥ መንገድ ከጥቁር ገበያ ላይ በመሰብሰብና ሀሰተኛ ሰነድ/ዲክላራሲዮን በማቅረብ፣ ሦስተኛ የሌላውን ሰው ዲክላራሲዮን የራስ አስመስለው በመጠቀም፣ አራተኛ ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ አካውንት በመክፈትና በመጠቀም በአጠቃላይ ሌሎች ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በመጠቀም የወንጀል ተግባራት መፈጸማቸውን መረዳት መቻሉም ተገልጿል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባካሄደው ክትትል፣ ትንተናና ማጣራት ሂደት ውስጥ ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዲያስፖራ አካውንትን በሚመለከት ያወጣውን መመሪያ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 እንዲሁም የወንጀል ህግን በመተላለፍ የተፈጠረውን ዕድል ለወንጀል መጠቀሚያ ማዋላቸውን ማረጋገጥ ተችሏልም ተብሏል።

በመሆኑም፤ በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊዎች ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጉዳዩ ለወንጀል ምርመራ መተላለፉን ያስታወቀው አገልግሎቱ፤ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊቱ እንዲታቀቡም ሲል የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አሳስቧል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe