በመድረኩ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ምሁራን፣ የፓርቲ አመራሮችና ሌሎችም የማህበረሰብ አካላት ተሳትፈዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሳቢያ የሚመጡ ግጭቶችን ለመቀነስ አመለካከት ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን መስራት እንዳለበት የተመከረ ሲሆን እንዲህውም ፖለቲከኞች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች፣ ከስሜታዊነት የፀዱና የተገሩ እንዲሆኑም ጥሬ ቀርቦላቸዋል፡፡
በብሔራዊ መግባባትና ግጭት አፈታት ላይ የሚሠራ ድርጅት ኢንተርናሽናል ሪቫይቫል ሚኒስትሪ (IRM) የተባለው ተቋም፣ ከኢንተር አፍሪካ ግሩፕ (IAG)፣ ከዴሞክራሲና ከምርጫ ኢንስቲትዩት (IDEA) እና ከአውሮፓ ኅብረት (EU) ጋር መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ‹‹የማኅበራዊ ሚዲያ ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ›› የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ወይይት ተደርጓል፡፡
‹‹የሰው ልጅ አንዱ ለአንዱ ጠላት ሆኖ አልተፈጠረም፡፡ ዛሬ በውስጣችን ያለው አመለካከት ባደግንበት አካባቢ የተማርነው የፖለቲካና የማኅበራዊ ጉዳይ ውጤት ነው›› ሲሉ የተናገሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፡ ማኅበራዊ ሚዲያውም ሆነ የመደበኛው ሚዲያ ሰዎች እንዲገለገሉበትና መልዕክት እንዲያስተላልፉበት የሚያገለግል መሣሪያ መሆኑን ከገለፁ በኋላ – የፖለቲካው ልሂቃንና በተለያዩ ስሞች የሚጠሩ የፖለቲካ ተዋንያን ማኅበራዊ ሚዲያውን ምንድነው እየመገብነው ያለነው? ብለው ራሳችን ሊጠይቁ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሌላው የቀድሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ‹‹የማኅበራዊ ሚዲያ ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ›› በሚል ርዕስ በአድማሱ ጣሰው (ዶ/ር) የተጠናውን ጥናት አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በተለያዩ የዕድሜ ክልል፣ የሙያ ዘርፍና የተለያዩ ስብጥሮች እያደገ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማኅበራዊ ሚዲያው ለበጎም ሆነ በጎ ላልሆነ ነገር እንደሚውልም ገልጸዋል፡፡ የአድማሱን (ዶ/ር) ጥናት አጣቅሰው ያስረዱት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ እንደ ጥቅሙ ሁሉ ማኅበራዊ ሚዲያው በኢትዮጵያ ላይ ሥጋት ጋርጧል ሲሉ ለመድረኩ ስጋታቸውን አጋርተዋል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር የተለያዩ ዕርምጃዎች በኢትዮጵያ ይወሰዱ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ኢንተርኔት ማቋረጥ፣ ጦማሪዎችን በማሰር፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን መዝጋት፣ የፀረ ሽብር ሕግን በመጠቀም ግለሰቦችን ተጠያቂ ማድረግና የተለያዩ ከሳይበር ጥቃትና የቴሌኮም ማጭበርበር ጋር የተገናኙ አዋጆች በማውጣት ሥራ ላይ ማዋል፣ የተወሰኑት እንደነበሩ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ጥናቱን እንዳጠኑት ምሁር በማኅበራዊ ሚዲያው ለተፈጠረው ተፅዕኖ ከቅጣት ይልቅ፣ አጠቃቀሙ የሚሻሻልበትንና የሚቃናበትን መንገድ መፍጠር የተሻለ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ደረጀ ገረፋ (ዶ/ር)፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተፈጠሩት ጥሩ የሆኑና ያልሆኑ ነገሮች የማኅበራዊ ሚዲያው ውጤቶች እንደሆኑ አስተያየታቸውን ለመድረኩ አካፍለዋል፡፡ እንዲህውም በአንድ አገር የጋራ የሚባል ነገር እንዲኖር ወጣቶች ላይ የመረጃና የታሪክ ሽግግር ልምድ ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡ የአንዱ አካባቢ እውነታ ተቀባይነት ለተወለደበትና ለሚኖርበት ሥፍራ ብቻ ሳይሆን፣ ሌላው ዘንድ ተሻግሮ የጋራ የሚሆን ነገር መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኢዜማን በመወከል በመድረኩ ላይ የተሳተፉት አቶ አበበ አካሉ፣ መንግሥት የግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉትን የራሱን አመራሮች አደብ ሊያስገዛ ይገባል ብለዋል፡፡ የመንግሥት ተቀናቃኝ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የፖለቲካ ምኅዳሩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ ነው የሚገኘው የሚለውን አስተሳሰብ በመተው፣ ማኅበረሰቡ ጋር ወርዶ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ሚዛናዊ አለመሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያው በስፋት እንዲሄዱ አድርጓቸዋል ያሉት አቶ አበበ፣ ሙያው ወገንተኝነት እንደሚከለክል ሁሉ ሚዲያውም ይህንን ሊከተል እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡