በምርጫ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ለፌደራል እና ክልል የፍትሕ ተቋማት ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው

በምርጫ የሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ለፌደራል እና ክልል የፍትሕ ተቋማት ባለሙያዎች እና አመራሮች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

በዚህ ሥልጠና ላይ በዋናነት በምርጫ ወቅት በወንጀል የሚያስጠይቁ ተግባራት እና የምርመራ እንዲሁም አጥፊን በሕግ እንዲጠየቅ የማድረግ ሂደትን በተመለከተ የዐቃቤ ሕግ፣ የፓሊስ ተቋማት አመራሮች እና ባለሙያዎች ሚና ይዳሰሳል።

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋ፥ ዜጎች ዴሞክራሲን ከሚለማመዱባቸው መንገዶች አንዱ እና ዋነኛው ምርጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ተግባር አደጉ በተባሉ ሀገራት ውስጥ ክርክር ማስነሳቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚስተዋል ተግባር መሆኑን አስታውሰዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ በሰላም እንዲከናወን እና በምርጫ ሂደት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ካጋጠሙም በአግባቡ መመርመር ያስችል ዘንድ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ሠልጣኞች በትኩረት ሥልጠናውን ተከታትለው ወደመጡበት ተቋማት ሲመለሱ ያገኙትን እውቀት ለባልደረቦቻቸው በአግባቡ ተደራሽ እንደሚያደርጉ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሥልጠናው በዛሬው ውሎው ስለ ምርጫ በሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ውስጥ የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች የመጀመሪያ ክፍል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሲሳይ አልማው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በነገው ዕለትም ሥልጠናው ቀጥሎ ከምርጫ ጋር በተገናኘ በወንጀል የሚያስጠይቁ ተግባራትን እና የምርመራ ጥፋተኛነትን በተመለከተ በተቋሙ ዐቃቤ ሕግ አቶ ሀብታሙ ብርሌ አማካኝነት ሥልጠና የሚሰጥ ይሆናል።

ሥልጠናው እየተሰጠ ያለው ዘንድሮ የሚካሄደውን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ነፃ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፍትሕ ተቋማት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነም ተገልጿል።

SourceFBC
Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe