የሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ማግኘቱን ተናገሩ።
በአገራቸው ላለፉት ሁለት ወራት በሰዎች ላይ ሙከራ እየተደረገበት የነበረው ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
ክትባቱ አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ማለፉን የገለጹት ፑቲን፤ ልጃቸው ክትባቱን እየወሰደች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
ጥቅምት ላይ ክትባቱን በጅምላ የመስጠት እቅድ እንዳለ የአገሪቱ አመራሮች ቢናገሩም፤ ባለሙያዎች የሩስያ የክትባት ምርምር እየሄደ ያለበት ፍጥነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
ባለፈው ሳምንት፤ የዓለም ጤና ድርጅት ሩስያ ክትባት ስታመርት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እንድትከተል ማሳሰቡ አይዘነጋም።
የሩስያ ክትባት ድርጅቱ በሦስተኛ ደረጃ ሙከራ ላይ ካስቀመጣቸው ክትባቶች አንዱ አይደለም። እነዚህ ክትባቶች በሰዎች ላይ ተሞክረው ተጨማሪ ምርምር መካሄድ አለበት።
ፕሬዘዳንት ፑቲን ግን፤ በሞስኮው ጋማሊያ ተቋም ውስጥ የተሠራው ክትባት ቫይረሱን “በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል” ነው ብለዋል።
የሩስያ የጤና ሚንስትር ሚካኤሊ ሙራሽኮ፤ ክትባቱ “በጣም ውጤታማና ደህንነቱ የሚያስተማምን” ነው ብለዋል። ክትባቱ የሰው ልጆች ኮቪድ-19ን ድል የሚነሱበት እርምጃ እንደሆነም አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት፤ የሩስያ መንግሥት ክትባቱ ላይ ስኬታማ ምርምር እንዳካሄደ አስታውቆ፤ በጅምላ ክትባቱን መስጠት እንደሚጀምር ይፋ አድርጎ ነበር።
በመላው ዓለም ወደ 100 የሚጠጉ ክትባቶች ላይ ምርምር እየተደረገ ይገኛል። ከነዚህ መካከል በሰው ላይ ሙከራ የተካሄደባቸውም አሉ።
ክትባት የማግኘት ሂደቱ ፈጣን ቢሆንም በርካታ ባለሙያዎች እስከ ቀጣዩ ዓመት አጋማሽ ድረስ ክትባት በስፋት አይዳረስም ይላሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ክርስቲያን ሊንድሜር “አንዳንዴ በግላቸው ምርምር የሚያካሂዱ ሰዎች ውጤታም እንደሆኑ ይናገራሉ። ይህም እጅግ መልካም ዜና ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አያይዘውም፤ ውጤታማ ክትባት በማግኘት እና በምርምር ደረጃዎች በማለፍ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ አስምረውበታል።
ምንጭ፡ ቢቢሲ
በሩስያ የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ አገኘ


Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!