በሶማሌ እና በአፋር ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ለማውረድ ሁለቱ ክልሎች በመንግሥትና በሕዝብ ለሕዝብ ደረጃም መነጋገር እንደሚቀጥሉ በሶማሌ ክልል ምክትል የኮምንኬሽን ኃላፊ የሆኑት ዲባ አሕመድ ለቢቢሲ ገለጹ።
በሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ማክሰኞ እለት 10 ሰዎች እንደተገደሉና ከሰኞ ጀምሮ የሞቱት ሰዎች ባጠቃላይ 27 እንደሆኑ ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለት የአፋር ክልል ኮሚዩኔኬሽን ኃላፊ አቶ አሕመድ ካሎይታ በድንበር አካባቢ በነበረው ግጭት 10 ሰዎች መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የትምህርት ሚኒስቴር ባልደረቦች መሆናቸው ተዘግቧል።
“በሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢ ያለው ግጭት ቆይቷል። ከሁለት ዓመት በላይ ብዙ ሰው የሞተበት የድንበር ግጭት ነው” ያሉት ምክትል ኃላፊዋ፤ የዚህ ሳምንት ክስተት ግን ከቀደሙት የተለየ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጥቃቱን በተመለከተ ምርመራ እየተካሄ እንደሚገኝ ጠቁመው “አሸባሪ ቡድን በሚል ያስቀመጡበት ሁኔታ አልተመቸንም። አሸባሪ ቡድን የሚባል እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አላየንም። በእርግጥ የሽብር ጥቃት ነው። የተገደሉት አስሩም ንጹሀን ዜጎች ናቸው” ብለዋል።
ከዚህ ቀደምም በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች መካከል ንግግር እየተደረገ እንደሆነ አስታውሰው፤ “እኛ በመነጋገር እናምናለን። የአፋር ወንድሞቻችንም ያምናሉ ብዬ ነው የማስበው። ንግግሩ ይቀጥላል” ሲሉ አስረድተዋል።
ምክትል የኮምንኬሽን ኃላፊ የሆኑት ዲባ፤ ጥቃቱን ማን እንዳደረሰ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸው፤ “ሕዝቦቹ ወንድማማች ናቸው። ሁከት የሚፈጥር ሦስተኛ አካል አለ ብዬ ነው የምገምተው። ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደረግ አካል አለ። መጀመሪያም ክስተቱ እንዲፈጠር እቅዱን ዘርግተው አሁንም ሰላም እንዳይኖር ንቅናቄ እያደረጉ ነው” ብለዋል።
የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ተመሳሳይ ባህል እንዳላቸው እንዲሁም በጋብቻም ተሳስረው እንደሚኖሩ በማጣቀስ፤ “ለፖለቲካ ፍጆታ ብለው በልቶ ጠጥቶ ያላደረ ሕዝብ ማጫረስን በምን እንደምገልጸው ራሱ አላውቅም” ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን በአካባቢው ሰላም እንሰፈነና በፌደራልና በክልል ደረጃም ንግግር እንዳለ ገልጸዋል።
አያይዘውም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ400 ያላነሱ ሰዎች እንደተገደሉ እና ንብረትም እንደወደመም ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ስለ ግጭቱ ምን አለ?
በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 17፣ 2013 ዓ.ም በአፋር ክልል ገዳማይቱ በምትባል አካባቢ በትምህርት ቤት ውስጥ የተገደሉት የትምህርት ሚኒስቴር ሁለት ሰራተኞች “አሸባሪ በሚባሉ ኃይሎች” እንደሆነ የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ አስታውቀዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመቆጣጠር የተሰማሩት የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች አቶ ሙላት ፀጋዩ እና አቶ አበባው አያልነህን ጨምሮ በክልሉ በደረሰ ጥቃት አስር ሰዎች ተገድለዋል።
በክልሉ ዞን ሶስት ገለአሎ በምትባል ወረዳ፣ ሰርከሞና ቴሌ ቀበሌ በሚባል መንደር የሚገኙ የአርብቶ አደር ማሕበረሰብ ላይ ጥቅምት 16፣ 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት በተፈፀመ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።
አቶ አህመድ “የሽብር ጥቃት” ያሉትም ሴቶችና ህፃናት ላይ እንዳነጣጠረም ጠቅሰዋል። የትምህርት ሚኒስቴርም ሰራተኞች በጥይት መገደልም ከዚህ “የሽብር ጥቃት ብለው” ከሚጠሩት ጋርም የተያያዘ ነው ይላሉ።
በክልሉ የተለያዩ ግጭቶች እንደሚያጋጥሙ የሚናገሩት አቶ አህመድ እንዲህ አይነት “መሰል የሽብር ጥቃት” ሲያጋጥም ግን ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ቀደምም በባለፈው አመት በአፋምቦ ወረዳ ኦግኖ ቀበሌ በተመሳሳይ መልኩ ሌሊት ላይ ሴቶችና ህፃናት ላይ ያነጣጠረ “የሽብር ጥቃት ተፈፅሞ ቁጥራቸውን ያልጠቀሱት ሰዎች መገደላቸውን ያስታውሳሉ።
ጥቃት የደረሰበት አካባቢ የኢትዮ-ጂቡቲ አውራ ጎዳናና አለም አቀፍ መተላለፊያ ድንበር እንደሆነም ይገልፃሉ። ጥቃቱን ያደረሱት አካላት ማንነትን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ በህገ ወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ተሰማርተው የነበሩና ያ እንቅስቃሴያቸው የተገታባቸው ኃይሎች “በአካባቢው የሚኖሩ የሶማሌ ኢሳ ጎሳ ማህበረሰቦችንም ከለላ በማድረግ” ህዝቡን እያጠቁ ይገኛሉ ብለዋል።
“አሸባሪ ለየትኛውም አይወግንም እነሱን ከለላ አድርጎ ከመጣ የነሱን ሰላም ሊያውክ የሚችል ኃይል እንደሆነ ታውቆ እነሱም በነሱ ውስጥ አቋርጠው እዛ ቦታ ላይ ሽብር ሊፈጥሩ የሚችሉ ኃይሎችን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር መቻል አለባቸው” ይላሉ።
በአካባቢው የሽብር ጥቃት እየተደጋገመ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ አህመድ በቅርቡም በክልሉ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ድጋፍ ለማድረግ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ልዑካኖችም ላይ በደረሰ ጥቃት የአንድ ፀጥታ ኃይል ህይወት ያለፈ ሲሆን አንዱም ተጎድቷል።
ልዑካኖቹ ድጋፋቸውን አድርሰው ሲመለሱ በፀጥታ ኃይሎቹ ላይ ባነጣጠረ ጥቃትም ህይወት መጥፋቱን አስታውሰዋል።
“አገሪቷ ላይ የመጣውን ለውጥ የማይደግፉና የሚፃረሩ ከውጭም የራሳቸው የሆነ ተልእኮ ያላቸው ኃይሎች አገሪቷ የጀመረችውን የብልፅግናና የአንድነት ጉዞም ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ናቸው” የሚሏቸው ኃይሎችም በክልሉም የሚፈፀመው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።
እነዚህ ኃይሎች በድንገተኛ ሁኔታ ጥቃት እያደረሱ የሚገኙ ሲሆን በከባድ መኪና አሽከርካሪዎችም እንዲሁ ጥቃቱ እየተፈፀመ ይገኛሉ ብለዋል።
ይሄ መስመር አለም አቀፍ መተላለፊያ ድንበር እንደመሆኑ መጠን የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት መጠበቅም ኃላፊነት የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ኃይል በመሆኑም እነሱም የሚችሉትን እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
“የኮንትሮባንድ ንግድ የተቋረጠባቸው ሊኖሩ ይችላሉ እነዚሁ ኃይሎች ናቸው ተደራጅተው የሽብር ጥቃት ፈፅመው የሚመለሱት።” የሚሉት ኃላፊው እንደዚህ ጥቃት የሚፈፅሙ ኃይሎችን የሶማሌ ክልልም ይሁን ሁሉም ሊያወግዝ ይገባል ይላሉ ።
“የኢሳ ማህበረሰብ በተለይም ገዳማይቱ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችም ከውስጣቸው ወጥቶ ሌሎች ላይ ጉዳት አድርሶ የሚመለሱ ኃይሎችን መታገል አለባቸው። ሽፋን ከመሆን ይልቅ መከላከል ይገባል።” ብለዋል
በባለፈው አመትም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ ከአገሪቱ ሰላም ሚኒስቴር እንዲሁም ከሶማሌ ክልልም ጋር ችግሩን ለመፍታትና ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም የተናገሩት ኃላፊው ክልሉም የማጣራት ሰራውን እንደሚቀጥልና የህዝብ ለህዝብ ውይይትም ይቀጥላል ብለዋል።
በተለይም ክልሉ በጎርፍ ክፉኛ ተጠቅቶ ኃብቱና ንብረቱን ባጣበት ወቅት ማጋጠሙም አሳዛኝ እንደሆነ የሚገልፁት ኃላፊው ጥቃቱ የደረሰባቸው አርብቶ አደር ማህበረሰብ እንዲሁ በጎርፉ ኃብትና ንብረቱን የተቀማ ነው ይላሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር ስለተገደሉት ባልደረቦቹ የሰጠው ምላሽ
በክልሉም በሰራ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸውን ላጡት ሁለት የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በዛሬው ዕለት ሽኝት መደረጉን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
ሰራተኞቹ ወደ አፋር የተንቀሳቀሱት ጥቅምት 13፣ 2013 ዓ.ም ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ወደሚሰሩበት ቦታ ገዳማይቱ በምትባል ቦታም ትምህርት ቤት ውስጥ ስራ እየሰሩ እያለ ነው ባልታወቁ ሰዎች በጥይት መመታታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ኮሚዩኒኬሸን ጉዳዮች ዳይሬክተር ሐረጓ ማሞ ይናገራሉ።
ሰራተኞቹም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ከማስቀጠልም በተጨማሪ በልጅነታቸው በመዳራቸውና በሌሎች ምክንያቶች ወደ ኋላ እየቀሩ ያሉ ሴቶችንም አትኩሮት በመስጠት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግም ነው ወደ ቦታው ያመሩት።
ጂቡቲ መስመር ላይ አንዳንድ አለመረጋጋቶች በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ እለት፣ ጥቅምት 16፣ 2013 ዓ.ም ተከስቷል የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን በማስመልከት የትምህርት ሚኒስቴሩ መረጃ አልነበረውም ወይ? ተብሎ ዳይሬክተሯ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሰራተኞቹ ከተባለው ቀን በፊት ቀደም ብለው እንደወጡና ከሰኞ በፊት በነበረውም ሁኔታ ሰላም የነበረ መሆኑን ይናገራሉ።
ከሄዱበት እለትም ጀምሮ የተለያዩ አካባቢዎችም ስራ መስራትም ችለው እንደነበርም ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞቹን በቡድን ወደተለያዩ ቦታዎች የላከ ሲሆን እነዚህ ሰራተኞችም በአጋጣሚ እንደተገደሉም ሐረጓ አስታውቀዋል።
የሰራተኞቹ አስከሬን ከአፋር ክልል በዛሬው ዕለት፣ጥቅምት 18 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባም ገብቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞችም ለሰራተኞቹ አስከሬን ወደየአካካቢያቸው ሽኝት ማድረጋቸውንም መረጃው ጠቁሟል።
በወቅቱም ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የአበባ ጉንጉን ከማኖር በተጨማሪ በሰራተኞቹ እልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ኃዘንም ገልፀው ለወዳጅ፣ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።
ሁለቱ ሰራተኞች በተገደሉበት ወቅት የመቁሰል አደጋ ያጋጠመው ሌላኛው የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኛ አቶ ደምሴ ታምሬ የቀዶ ህክምናውን በክልሉ አድርጎ እያገገመ መሆኑንም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነውን መረጃ ያስረዳል።