“በትግራይ አስቸኳይ እርዳታ ካልደረሰ የ77ቱ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል”

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ አስቸኳይ የእርዳታ አቅርቦት እንዲደርስ ካልተደረገ በ1977ዓ.ም የነበረው ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ዶ/ር ሐጎስ ጎደፋይ ተናገሩ።

ባለፈው ዓመት ጦርነቱ ከተከሰተ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ የክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅርን ሕገ ወጥ ብሎ ቢያፈርሰውም የጤና ቢሮ ኃላፊ እንደሆኑ የሚናገሩት ዶ/ር ሐጎስ ያለው የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በረሃብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በርካታ መሆኑን ለቢቢሲ ትግርኛ ዶክተር ሐጎስ ጎደፋይ፣ በክልሉ የመገናኛ ዘዴዎች ችግር በመኖሩ የረሃቡን መጠን ሙሉ በሙሉ ለማወቅ አዳጋች እንዳደረገው ገልጸዋል።

“የደረሱንን መረጃዎች ስናይ ግን በቀን በየሆስፒታሉ ከ3 እስከ 4 ሰዎች በረሃብ እየሞቱ ነው” ያሉት ዶ/ር ሐጎስ ጎደፋይ፣ በማዕከላዊ ዞን አካባቢዎች ተምቤን፣ አድዋና አክሱም፣ ዛና – የሠሜን ምዕራብ አካባቢዎች፣ በራያ እንዲሁም እንዳሞኾኒ፣ በደቡብ ምሥራቅ ደረጃው ቢለያይም በርካታ ወረዳዎች “አደጋ ላይ” መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ አካባቢዎች ከዚህ በፊትም በረሃብ የሚጠቁ እንደነበሩ ኃላፊው አክለው አመልክተዋል።ዶ/ር ሐጎስ በክልሉ ያለውን ሁኔታ ለመመልከት በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው እንደነበር ገልፀው፣ በተለይም በማዕከላዊ ዞን፣ ራያ አካባቢ እንዲሁም ተንቤን ያለውን ሁኔታ መታዘባቸውን ይናገራሉ።

“የረሃብ ሁኔታው እየባሰበት ነው። በተለይም በህጻናት፣ በሚያጠቡ እናቶችና በነፍሰጡሮች ላይ የሚታው ችግር ሰፊ ነው” ብለዋል።ያለው ሁኔታ በዓለም ደረጃ ባለው የምግብ እጥረት መለኪያ ሲለካ “25 በመቶ ደርሷል። አንድ አገር 15 በመቶ ከደረሰ አደጋ ላይ እንዳለች ታውቆ የምግብ እርዳታ ለማደል እቅድ ይወጣል። አሁን እዚህ 25 በመቶ ደርሷል” ሲሉ ተናግረዋል።

የረሃቡ ደረጃ ከወረዳ ወረዳ እንደሚለያይ የሚናገሩት ዶ/ር ሐጎስ፣ “አማካዩን ቁጥር ነው እየገለጽኩ ያለሁት እንጂ በአንዳንድ ወረዳዎች ከ30 በመቶ በላይም ደርሷል። አሁን አስቸኳይ እርዳታ መቅረብ ካልቻለ ወደ 77ቱ ሁኔታ ልንሸጋገር እንችላለን” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

በትግራይ ከአንድ ዓመት በታች የዕድሜ ክልል የሚገኙ ህጻናት ከ250 ሺህ በላይ እንደሚሆኑ፣ ከአምስት ዓመት በታች የሚሆኑት ደግሞ አንድ ሚሊዮን እንደሚደርሱም ኃላፊው ጠቅሰዋል።

“ከእነዚህ መካከል ከ60 እስከ 70 በመቶዎቹ በረሃብ አደጋ ላይ የወደቁ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሆስፒታሎች እየገቡ ካሉት ህጻናት አብዛኛዎቹ ከረሃብ ጋር በተያያዘ ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት ነው።”

የጤና ኬላዎች የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ቢጠበቅባቸውም ይህንን እያደረጉ አለመሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሐጎስ፣ በረሃብ የተጎዱ ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም ቢመጡም በሆስፒታሎች በቂ የምግብ አቅርቦት ባለመኖሩ ችግሩ የበለጠ ፈታኝ መሆኑን ያስረዳሉ።

“ትልቁ ችግር ደግሞ በሆስፒታሎች በቂ ምግብ አለመኖሩ ነው። አልጋ ይዘው ለሚታከሙም በቂ ምግብ የለም።”

“ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶችም በከባድ ችግር ውስጥ ናቸው ያሉት። በቂ ምግብ አያገኙም። የሚያገኟትም ቅድሚያ ለልጆቻቸውና ለቤተሰብ ነው የሚያውሏት። በዚህ ምክያት በአሁኑ ጊዜ 78 በመቶ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ችግር ላይ ወድቀዋል” ብለዋል።

በትግራይ ውስጥ የነበሩት የጤና ተቋማት 90 በመቶ ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን ዶ/ር ሐጎስ አክለው ተናግረዋል።

“ከ22 ሺህ በላይ የጤና ባለሞያች ተበትነዋል። ወደ 37 የሚሆኑ ሠራተኞች አገልግሎት እየሰጡ በነበሩበት ወቅት ተገድለዋል። በምዕራብ ትግራይ ብቻ 78 የጤና ባለሙያዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።

የጤና ተቋማት ምንም ዓይነት ሕክምና መስጫ ቁሳቁስ እንደሌላቸውም ጨምረው ተናግረዋል።

ትግራይ ውስጥ መድኃኒት የሚባል የለም” ያሉት ኃላፊው ዶ/ር ሐጎስ፣ የልብ ችግር ላለባቸው፣ የኤችአይቪ እና የስኳር ሕሙማን ቢያንስ ቢያንስ ለሦስት ወር ተቀማጭ መድኃኒት ያስፈልግ እንደነበር ይናገራሉ።

“የወባ በሽታን ጨምሮ፣ ሰዎች በተለያዩ በሽታዎች እየተጠቁ ነው” ያሉት ዶ/ር ሐጎስ የነበረው መድኃኒት አልቆ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የትግራይ ክልል በህወሓት አማጺያን እጅ መውደቁን ተከትሎ የግንኙነት መስመሮች የተቋረጡ ሲሆን ባንክ፣ የቴሌኮምዩኑኬሽን አገልግሎት እንዲሁም መብራት ተቋርጧል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊም “ጥሬ ገንዘብ የለም። የጤና አገልግሎት እጥረትም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው። አሁን በነጻ ነው እየሰራን ያለነው።”

የትግራይ አማጺያን በርካታ የክልሉን ግዛቶች ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ሁሎም መንገዶችና መገናኛ መስመሮች በመዘጋታቸው ከ90 በመቶ በላይ የክልሉ ሕዝብ ለረሃብ አደጋ እንደተጋለጠ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

አንድ ዓመት ሊሞላው አንድ ወር የቀረው የትግራይ ጦርነት እጅግ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውሶችን ሲያስከትል እና በርካታ የጤና ተቋማት ወድመዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe