“በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፋላሚዎች አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይገባል”- ፕሬዝደንት ባይደን

የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡም ባይደን ጥሪ አቅርበዋል።

አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሁሉንም ሀገሮች ፍላጎት ያማከለ ስምምነት እንዲደረስ መሻቷ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ በትግራይ የሚደረገው ጦርነት ያስከተለው ስብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል እየተፋለሙ ያሉ ሁሉም ወገኖች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም ኋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመግለጫቸው አክለውም “የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ” ጠይቀዋል።

በክልሉ ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ የሚስተዋሉ “መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች” ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን እና ሊቆሙ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ በያዝነው ሳምንት እንዳስታወቀው ፣ እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑንና በኢትዮጵያ ከ1970ዎቹ ወዲህ ከፍተኛ የረሀብ አደጋ እንዳንዣበበ ማስታወቁን የጠቀሰው መግለጫው ፤ ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች የሰላም መንገድ እንዲከተሉ፣ ዕርዳታ ያለምንም መስተጓጎል ለተቸገሩት እንዲደርስ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ፕሬዝደንቱ መጠየቃቸውን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መሪዎችና ተቋማት ለብሔራዊ እርቅና መግባባት ቅድሚያ ሰጥተው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን በማቆም ለውይይት እና ለጋራ ሀገራዊ ጉዳይ እንዲሰሩ አሜሪካ ጥሪ ታቀርባለችም ብለዋል ፕሬዝደንቱ።

በኢትዮጵያ ላለው ችግር መፍትሄ ለማፈላለግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነች ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን፤ ሀገራቸው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት የምትሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ፣ አሜሪካ በቀጠናው የምታካሂደውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማጠናከር በዚህ ሳምንት ወደ ቀጠናው እንደሚጓዙም ጠቁሟል።

ፕሬዚዳንት ባይደን በመግለጫቸው አክለውም አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሁሉንም ሀገሮች ፍላጎት ያማከለ ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት እንዳላት በመግለጽ፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሁሉም አካላት ጋር እንደሚመክሩም አስታውቀዋል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe