“በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሐብ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ይኸ [በጎርጎሮሳዊው] 2011 በተከሰተ ጠኔ 250 ሺሕ ሶማሊያውያን ህይወታቸውን ካጡ ወዲህ ባለፉት አስር አመታት ዓለም ያየው የከፋ ረሐብ ነው” ያሉት ማርክ ሎውኮክ ከ37 አመታት በፊት በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ግዙፍ እና አሳዛኝ ረሐብ ያስታውሳል ብለዋል።
በትግራይ ክልል እና በሰሜን ኢትዮጵያ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የሚዳርግ የከፋ ረሐብ መከሰቱ አይቀሬ ነው ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ አስጠነቀቁ። ኤኮኖሚው ከንግድ ሥራዎች፣ ከሰብል እና ከማሳ ጋር ወድሟል ያሉት ማርክ ሎውኮክ የባንክ እና የቴሌኮምዩንኬሽን ግልጋሎቶች አለመኖራቸውን ገልጸዋል።
ትናንት አርብ ባወጡት መግለጫ “ከረሐብ ጋር በተያያዘ ሰዎች መሞታቸውን እየሰማን ነው” ያሉት ሎውኮክ “ሰዎች ሊነቁ ይገባል” የሚል ጥሪ አቅርበዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ገንዘብን ጨምሮ ዝግጅት ሊያደርግ ይገባል ያሉት ማርክ ሎውኮክ ካለፈው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ጀምሮ ውጊያ በበረታበት የትግራይ ክልል ይፈጠራል ያሉትን ረሃብ ከ1977ቱ ክስተት ጋር አወዳድረውታል።
በመግለጫቸው “በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሐብ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ይኸ [በጎርጎሮሳዊው] 2011 በተከሰተ ጠኔ 250 ሺሕ ሶማሊያውያን ህይወታቸውን ካጡ ወዲህ ባለፉት አስር አመታት ዓለም ያየው የከፋ ረሐብ ነው” ያሉት ሎውኮክ ከ37 አመታት በፊት በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ግዙፍ እና አሳዛኝ ረሐብ ያስታውሳል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1977 እና 78 ዓ.ም. በተከሰተው ረሐብ እና ባስከተላቸው ሕመሞች ሁለት ሚሊዮን ገደማ አፍሪካውያን እንደሞቱ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ከሟቾቹ መካከል አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው።
“አሁን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመቶ ሺሕዎች ወይም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አለ” ያሉት ሎውኮክ ምግብ እና ሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ለተቸገሩ ማድረስ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች እጅግ ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ በትግራይ ክልል 93 ወረዳዎች ዕርዳታ እየተሰራጨ መሆኑን አስታውቆ ነበር። ከ93 ወረዳዎች በአስራ አራቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕርዳታ እያሰራጨ መሆኑን ባለፈው ሐሙስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በመጀመሪያው ዙር ለ4.5 ሚሊዮን፣ በሁለተኛው እና ሶስተኛው ዙር ደግሞ 4.3 ሚሊዮን ተረጂዎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች ማከፋፈሉን አስታውቋል።
ቢልለኔ እንዳሉት የዓለም የምግብ መርሐ ግብር (World Food Programme) ፣ ዎርልድ ቪዥን፣ ኬር፣ ማሕበራዊ ረድኤት ትግራይ (ማረት) እና ፉድ ፎር ዘ-ሐንግሪ የተባሉ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል እርዳታ እያቀረቡ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን በቅርብ ወራት በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በዋናነት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኙ አካባቢዎች መርዳታቸውን ሎውኮክ ገልጸዋል። ነገር ግን በትግራይ ተቃዋሚ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በሚገኙ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው “ምግብ እንዳያገኙ ሆን ተብሎ፣ ተደጋጋሚ እና ዘላቂ ጥረት ይደረጋል” ሲሉ ከሰዋል።
ኃላፊው በኤርትራ ወታደሮች እና ሌሎች ሚሊሺያዎች ቁጥጥር ሥር በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች ዕርዳታ ማድረስ እጅግ ከባድ መሆኑንም ጠቁመዋል። “ጠብመንጃ እና ቦምብ የታጠቁ ሰዎች በሚያደርጉት እና የፖለቲካ አለቆቻቸው አድርጉ እያሉ በሚነግሯቸው ምክንያት የእርዳታ ሰራተኞች” መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን የገለጹት ሎውኮክ የከፋ ረሐብ ለተጋረጠባቸው እርዳታ ለማድረስ ክልከላው ሊቀለበስ እንደሚገባ እና “ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ ናቸው” ያሏቸው የኤርትራ ወታደሮች መውጣት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። “ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ አደርጋለሁ ያሉትን ያድርጉ፤ ኤርትራውያኑ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ያስገድዱ” ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ጣሊያን እና ካናዳ መሪዎች ከሰኔ 4 እስከ 6 በእንግሊዝ ኮርንዎል በሚያደርጉት ስብሰባ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እና የከፋ ረሐብ ሥጋት ዋንኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንዲያደርጉትም ጥሪ አቅርበዋል።
ማርክ ሎውኮክ ከ37 አመታት ገደማ በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተው አይነት ረሐብ ከተደገመ ዳፋው ብርቱ እና ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ሊሆን እንደሚችል ትናንት አርብ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል።