በአለም ከተዘነጉ መፈናቀሎች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ ተካታለች

የኖርዌጂያን የስደተኞች ካውንስል በአለማችን የተዘነጉ መፈናቀሎች በሚል ባወጣው አመታዊ ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ በዘጠነኛነት ተቀመጠች።

የሀገራት ዝርዝሩ ያካተተው በ2018 የተከሰተውን መፈናቀል መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ በቀዳሚነት ካሜሮን፣ በማስከተል ኮንጎ የስደተኞች ጉዳይ ቸል የተባለባቸው ሀገራት በሚል ተቀምጠዋል።

ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ በኢትዮጵያ ውስጥ 2.9 ሚሊየን የተፈናቀሉ ወገኖች መኖራቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ ይህም ሀገሪቱን በአለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ያደርጋታል ብሏል።

ተፈናቃይ ዜጎች በተጣበበ ስፍራ፣ በትምህርት ቤቶችና በቤተ ክርተስትያናት ለመኖር ተገድደዋል የሚለው የኖርዌጂያን የስደተኞች ካውንስል ሪፖርት በርካቶች ወደ ቀያቸው የተመለሱ ቢሆንም አሁንም ግን በመመለሳቸው ደህንነት አይሰማቸውም ሲል ያትታል።

በኢትዮጲያ ውስጥ ባለፈው ዓመት ብቻ 8 ሚሊየን ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር ያለው ሪፖርቱ ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች የተገኘው እርዳታም ከተጠየቀው ግማሹ ብቻ መሆኑንም ያስታውሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ያመጡት ለውጥ፣ ከኤርትራ ጋር የፈጠሩት ሰላም በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ በሰፊው ሽፋን ቢያገኝም የእነዚህ ተፈናቃይ ወገኖች ጉዳይ ግን የመገናኛ ብዙኀኑን አይንና ጆሮ ተነፍጎ ነበር ሲል ያስረዳል።

የኖርዌጂያን የስደተኞች ካውንስል ሪፖርት እንደጠቀሰው የሰብዓዊ እርዳታ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ብቻ ቢሆንም አንዳንድ ቀውሶች ግን ከሌሎች በተለየ ትኩረትና ድጋፍ ያገኛሉ ብሏል።

በአለማችን አንድ ጥግ በሚደርስ ሰብአዊና ተፈጥሯዊ ቀውስ ምክንያት የሚጎዱ ሰዎች ትኩረት አግኝተው የተለያዩ እርዳታና ድጋፎች ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ ዞር ብሎ የሚያያቸው የማያገኙበት ምክንያት ምንድነው ሲል ይጠይቃል።

ምናልባት ከጂኦ ፖለቲካዊ ፍላጎት የተነሳ ሊሆን ይችላል በማለት ግምቱን ያስቀመጠው ሪፖርቱ ምናልባትም ተጎጂዎች የሚገኙበት ስፍራ የራቀ መሆንና ተጎጂዎችን ለመለየት አዳጋች ሆኖ ሊሆን ይችላል ሲል መላምቱን ያስቀምጣል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ይህንን የሀገራት ዝርዝር ያዘጋጀበትን ምክንያት ሲጠቅስ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን ትኩረት እምብዛም ትኩረት ያልሳቡት መፈናቀሎች ላይ፣ ፖለቲከኞች የዘነጓቸው ወይንም ትኩረት የነፈጓቸውን፣ የሚያስፈልጋቸውን ጥበቃ እና ድጋፍ ያላገኙ ሰዎች ላይ ብርሀን ለመፈንጠቅ እንደሆነ ያትታል።

ለውጥ ለማምጣት ስለእነዚህ ሰዎችና ስለ ደረሰው ቀውስ በቂ መረጃ መኖር አስፈላጊ ነው ያለው ሪፖርቱ፣ ይህንን ጥናት ለማዘጋጀት ሶስት ማዕቀፎች ላይ መመስረቱን ያስረዳል።

የፖለቲካ ፈቃደኝነት አለመኖር፣ የመገናኛ ብዙኀን ትኩረት ማጣትና የኢኮኖሚ ድረጋፍ አለማግኘት የሪፖርቱ ማዕቀፎች ሆነው ተቀምጠዋል።

ሪፖርቱ የፖለቲካ ፈቃደኝነት ሲል የተፈናቃይ ዜጎች ደህንነትንና መብት በማስጠበቅ ረገድ የፀጥታ ኃይሉ ተነሳሽነት ማጣት እንደምክንያት ተጠቅሷል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብም ለእነዚህ ወገኖች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የነበረውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት አናሳ እንደነበር ያስቀምጣል።

ሌላው የተፈናቃይ ወገኖች ያገኙት የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን በተለያየ ምክንያት እንዳነሰ የጠቀሰው ሪፖርቱ ሽፋኑ በቀውሱ ስፋት ልክ አይደለም ብሏል። መገናኛ ብዙኃን ግጭቶችን ሲዘግቡ እንኳን ስለጦር ስልት፣ የፖለቲካ ጥምረቶችና በአማፂያን መካከል በሚደረጉ ግጭቶች ዜናው ይሸፈናል ሲል ሪፖርቱ ያትታል።

በሶስተኛ መስፈርትነት የቀረበው የተባበሩት መንግሥታት እና ሰብአዊ እርዳታ አጋሮቹ በሀገራት ለሚደርሱና ለደረሱ ቀውሶች የጠየቁትን ድጋፍ ነው።

እነዚህ ጥያቄዎች ምን ያህሉ ፈጣን ምላሽ አገኙ የሚለው ከመስፈርቶቹ መካከል ነው።

በኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ እና ኤርትራ መጥተው የተጠለሉ 900 ሺህ ስደተኞች ይገኛሉ።

Source: BBC Amharic

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe