በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና መፈናቀል የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሄዱ

ትናንት በደብረ ማርቆስና በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ሰልፍ መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

ሰልፈኞቹ ማንነትን መሰረት አድርገው በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸሙ ግድያ እና መፈናቀሎች እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡

በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና መፈናቀል እንዲሁም እንግልት የሚያወግዙ ሰልፎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እና ከተሞች ተካሄዱ፡፡

ሰልፎቹ ዛሬ በወልዲያ፣ በኮምቦልቻ፣ በባህርዳር እና በደብረ ማርቆስ ከተሞች ተካሂደዋል፡፡

ትናንት በደሴ እና በደብረ ማርቆስ በተመሳሳይ መልኩ ግድያዎቹን የሚያወግዙ ሰልፎች መካሄዳቸው የሚታወስ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙት የደብረ ማርቆስ እና የደብረ ብርሃን እንዲሁም የሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችም ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገዶች አሰምተዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ ከተሞች በተካሄዱት እና በርካቶች በተሳተፉባቸው ሰልፎች ማንነትን መሰረት ያደረገው ግድያ እና ሞት መፈናቀሉም ጭምር ተወግዟል፡፡

በሰልፎቹ ድርጊቱን ከማውገዝም ባሻገር እንዲቆም ወንጀለኞችም ለህግ እንዲቀርቡ የሚያጠይቁ መልክዕቶች ተንጸባርቀዋል፡፡

የተቃውሞ ሰልፎቹ በክልሉ ሰሜን ሸዋ ያጋጠመውን ሰሞነኛ ሞትና መፈናቀል ተከትሎ የተደረጉ ናቸው፡፡

ሰልፎቹን ማን እንደሚያስተባብራቸውና በማን እንደሚመሩ በይፋ የታወቀ ነገር የለም ሆኖም በወልዲያ የተካሄደው ሰልፍ በአማራ ወጣቶች ነፃ ማህበር አስተባባሪነት መካሄዱን የከተማው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በክልሉ ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አጎራባች በሆኑ የኤፍራታ እና ግድም፣ የአንጾኪያ እና ገምዛ እንዲሁም የቀወት ወረዳ አካባቢዎች ባጋጠመው ሰሞንኛ የጸጥታ ችግር በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ የመኖሪያ ቀያቸውንም ለቀው ተሰደዋል፡፡

በጥቃቱ አጣዬ ከተማ “ሙሉ በሙሉ ወድሟል” ስለመባሉ አል ዐይን አማርኛ ትናንት የአካባቢውን ነዋሪዎችና ባለስልጣናት ዋቢ አድርጎ መዘገቡም የሚታወስ ነው፡፡

ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቀ እና በይፋ ያልተገለጸ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰደው በደጋማ የአካባቢው ስፍራዎችና ከተሞች መስፈራቸውም ተነግሯል፡፡

ሆኖም አሁን በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ የሸዋሮቢት እና የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው እየተመለሱ ነው ተብሏል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን እና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ጥቃቱን “የኦነግ ሸኔ የጥፋት ኃይል ነው ያስፈጸመውና ያስተባበረው” ማለታቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡

“ጽንፈኛ” ያሉትን ይህን ኃይል “ለመደምሰስ” ከፌዴራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር ችግሩ ባጋጠመባቸው የሰሜን ሸዋ፣የቡብ ወሎ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ ተቋማትን ያካተተ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe