በአማራ ክልል ከ10 ሚሊዮን በላይ የትምህርት መጽሐፍት ቢታተሙም የተሰራጨው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ ብቻ ነው

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ ክልሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በአጠቃላይ 10 ሚሊዮን 33 ሺህ 366 ሚሊዮን የአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት መጽሐፍት አሳትሟል። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ማሰራጨት የተቻለው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮኑን ብቻ ነው።

የታተሙት መጽሐፍት ቁጥርና የተሰራጨው ልዩነት የተፈጠረው እንደሀገር በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በውጭ ሀገር የታተሙትን መጽሐፍት ማስገባት ባለመቻሉና በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፣ እስካሁን በውጭ ሀገር 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን መጽሐፍት እንዲሁም አንድ ሚሊዮን 233 ሺህ 366 መጽሐፍት በሀገር ውስጥ አሳትሟል፣ ከዚህ ውስጥም ለየትምህርት ቤቶቹ ማዳረስ የተቻለው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብቻ ነው።

በውጭ ሀገር ከታተመው ውስጥም ቢሮው ባገኘው የውጭ ምንዛሪ ወደ አንድ ሚሊዮን 425 ሺህ 502 መጽሐፍትን አምጥተን አሰራጭተናል ብለዋል።

የመጽሐፍ ሕትመት ዝግጅቱ በ2014 ዓ.ም መጠናቀቁን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ ለሕትመት የ500 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት እንደነበር አመላክተዋል።

ለሕትመት ከተያዘው በጀት አኳያ በአጭር ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ከባድ በመሆኑ መጽሐፍቱ ተደራሽ የሚሆኑበትን አማራጭ በመጠቀም ወደ ማሳተም ሂደት ተገብቶ ነበር ያሉት ኃላፊው፣ ያሉትን አማራጮች ተጠቅመን በሶፍት ኮፒ ለትምህርት ቤቶች በማዳረስ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስቀጥለናል ብለዋል።

በእስካሁኑ ሂደት በመጀመሪያው ዙር በሀገር ውሰጥ 944 ሺህ 882 መጽሐፍትን አሳትመናል። በ2ኛው ዙር 288ሺህ 484 መጽሐፍትን አሳትመን ለትምህርት ቤቶች አከፋፍለናል ሲሉ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹን መጽሐፍት ከታተሙበት ሀገር ለማምጣት ከ90 በመቶ በላይ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ የውጭ ምንዛሪው ተገኝቶ መጽሐፍቱን እንደመጡ ወደየትምህርት ቤቶች የሚሰራጩ ይሆናል ብለዋል።

ሙሳ ሙሐመድ

አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe