በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወጪ ለሚ ናሽናል የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን፥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርና የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የሲሚንቶ ፋብሪካው በለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ የሚገነባ ሲሆን 270 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡
ፋብሪካው በመጀመሪያው ዙር ግንባታው 10 ሺህ ቶን ሲሚንቶ ያመርታል ተብሏል፡፡
ፋብሪካው በኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ እና በቻይናው ዌስት ቻይና ሲሜንት ኩባንያዎች ሽርክና የሚገነባ ሲሆን ግንባታው በ18 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክሱ ከሲሚንቶ ፋብሪካው በተጨማሪ የመስታወት፣ የጂፕሰም ቦርድና ሌሎች ምርቶችን የሚያመርቱ ግዙፍ ፋብሪካዎችን ያካትታል ተብሏል።
የፋብሪካዎቹ ግንባታ እስከ 10 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም በግንባታው ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍና የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑ ተገልጿል፡፡